Home ማኅበራዊ ሁለት ተስፈኛ ታታሪ ኢትዮጵያውያን በግፍ እና በጭካኔ ተገደሉ። በብዙ መልኩ ከልብ ያሳዝናል!...

ሁለት ተስፈኛ ታታሪ ኢትዮጵያውያን በግፍ እና በጭካኔ ተገደሉ። በብዙ መልኩ ከልብ ያሳዝናል! – መስፍን ነጋሽ

5023
0

ይህ ግድያ ድንገት በግልፍተኝነት ወይም በግለሰብ ጠብ የተፈጠረ አይደለም።

ምክንያቱ በአካባቢው ለመጀመሪያ ጊዜ የሐሰት ወሬ መሰማቱ አይደለም።

የችግሩ ስር “ልጆች ሞቱ” የሚል የሐሰት ወሬ መናፈሱ አይደለም።

ይህን ወሬ ለግድያ የሚያነሣሣ ትልቅ ጉዳይ ያደረገው ሲነዛ የሰነበተው ቦኮ ሃራማዊ ወይም ታሊባናዊ ትርክት ነው።

ግድያው የፖለቲከኞች ቅስቀሳና ትርክት የመጨረሻው አስከፊ መገለጫ መሆኑን ልንስተው አይገባም።

የፖለቲካ ትርክቶች ዓለምን የመተርጎሚያ መነጽር ይሆናሉ።

ግድያውን የፈጸሙት ወጣቶች ክትባትን እና የጤና ባለሞያዎችን የሆነ ሴራ አስፈጻሚዎች አድርገው እንዲመለከቱና እንዲቃወሟቸው ሲማሩና ሲሰለጥኑ ሰንብተዋል።

ጊዜው ደሞ ትምህርታቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ አስቻለቸው። ይኸው ነው።

ይህ የጀርመን ድምጽ ዘገባ “ከዚህ ቀደም በወረዳው የወሊድ መከላከያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ማሪስቶፕስ የተሰኘ ድርጅት በህብረተሰቡ ተቃውሞ በአካባቢው የነበረውን ስራ እንዲያቋርጥ መደረጉን

… ከክትባት ጋር በተያያዘ በቅርቡ በባህር ዳር ላይ ደርሶ የነበረን ተመሳሳይ ችግር…” መኖሩን ያስታውሰናል።

ዝርዝሩ ሊመረመር የሚገባው ሆኖ ይህ አደገኛ አስተሳሰብ ዛሬ ብቻ የተገለጠ አለመሆኑን ይጠቁማል።

ለፖለቲከኞች ከጽንፈኛ ትርክታቸው እንዲወጡ የሚያነቃ ደውል ነው።

ለመንግሥት እና በጎ ሕሊና ላላቸው ዜጎች አስደንጋጭ መርዶ ነው። ጥፋተኞቹን በሚገባ መቅጣት ያስፈለጋል።

በቁስ ብቻ ሳይሆን በእውቀት የደኸየውን ሕዝብ ማስተማር ያስፈልጋል።

ከክትባት ርቆ፣ የሚያድነውን ገድሎ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ አያስፈልግም ተብሎ፣ በድህነቱ ላይ ያለገደብ ተራብቶ….እንዴት ይሆናል?

————————————-
አስተያየት ለሚሰጡ፤ “ደንቦችና አሠራሮች ተግባራዊ ይሆናሉ!”
ስድብ እና ከርእሰ ጉዳይ ወጥቶ መዘባረቅ ሊያስባርር ይችላል።

#Mesfin Negash

(መስፍን ነጋሽ፣)

በአማራ ክልል ሁለት ተመራማሪዎች (ዕጩ ዶክተሮች) ተገደሉ – DW + VOA

 ***

በአማራ ክልል ሁለት ተመራማሪዎች ተገደሉ -DW

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ባለፈው ማክሰኞ ለምርምር በሄዱ ግለሰቦች ላይ በደረሰ ጥቃት ሁለቱ ሲገደሉ አንደኛው በጠና መጎዳቱን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የአማራ ክልል ፖሊስ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተካሄደ ነው ብሏል።

በአማራ ክልል ሁለት ተመራማሪዎች ተገደሉ

በጎንጅ እና ቆላላ ወረዳ ለምርምር ናሙና እየሰበሰቡ ባሉበት በአካባቢው ሰዎች በደረሰባቸው ጥቃት የተገደሉት አቶ ወሰን ታፈረ እና አቶ ማንደፍሮ አቤ የተባሉ ተመራማሪዎች መሆናቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንተነህ በላይ ለDW ተናግረዋል።

ከሁለቱ ተመራማሪዎች ጋር አብረው የነበሩት እና በወረዳው ባለ ቤተሙከራ በምርመራ ባለሙያነት የሚገለግሉት አቶ ኃይለኢየሱስ ሙሉ ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

ሶስቱ ግለሰቦች ባለፈው ማክሰኞ፤ ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ ም፤ ጥቃት የደረሰባቸው በወረዳው በሚገኝ አዲስ ዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰገራ ሽንት ናሙናዎችን በመሰብሰብ ላይ እያሉ መሆኑን አቶ አንተነህ አስረድተዋል።

ተመራማሪዎቹ በድንጋይ እና በዱላ ተደብድበው የተገደሉት ለአካባቢው ህብረተሰብ በደረሰው የተሳሳተ መረጃ ነው ያሉት የጽህፈት ቤት ኃላፊው ድርጊቱ የተፈጸመው “በስሜት በመነሳሳት ነው” ብለዋል።

ዕለቱ የገበያ ቀን ስለነበር በርካታ ህዝብ በተሰበሰበበት “ክትባት እየተከተበ ልጆቻችሁ ሞቱ።

አራት ህጻናት ሞተዋል” በሚል በተሰራጨ ወሬ የአካባቢው ነዋሪ ተመራማሪዎቹ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ማድረሱን አብራርተዋል።

ተመራማሪዎቹ ከናሙና መሰብሰብ ሌላ የትራኮማ በሽታ ያለባቸውን ተማሪዎች ለመለየት የዓይን ቆባቸውን ሲመርምሩ ነበር ተብሏል።

ሟቾቹ ከጤና ጽህፈት ቤት ህጋዊ የትብብር ደብዳቤ አጽፈው ቢይዙም ለአካባቢው ህብረተሰብ ባለመነገሩ በህብረተሰቡ ዘንድየተሳሳተ ግንዛቤ መፈጠሩን የጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም በወረዳው የወሊድ መከላከያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ማሪስቶፕስ የተሰኘ ድርጅት በህብረተሰቡ ተቃውሞ በአካባቢው የነበረውን ስራ እንዲያቋርጥ መደረጉን አብራርተዋል።

ከክትባት ጋር በተያያዘ በቅርቡ በባህር ዳር ላይ ደርሶ የነበረን ተመሳሳይ ችግር የጠቀሱት አቶ አንተነህ በአካባቢያቸውም መሰል ችግር እንዳይከሰት ህብረተሰቡ “በንቃት እየጠበቀ ነበር” ብለዋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተመራማሪዎቹ ግድያ ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ለDW የገለጹት የኮሚሽኑ የመገናኛ ብዙሃን አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር መሰረት በጥቃቱ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

የግድያው መንስኤ በመጣራት ላይ መሆኑን እና ምርመራው ሲጠናቀቅ እንደሚገለጽም አክለዋል።

የጎንጅ እና ቆላላ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ከ30 በላይ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

(ከጎንጅ እና ቆላላ ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ)

አውዲዮውን ያዳምጡ። https://www.dw.com

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ

***

በምዕራብ ጎጃም ዕጩ ሁለት ዶክተሮች ተደብድበው ተገደሉ – VOA


አጥኒዎቹ በከተማው ባለው አንድ ትምሕርት ቤት ውስጥ ለምርምር የሚሆን የሽንትና የዐይነ ምድር ናሙና እየሰበሰቡ ባሉበት ወቅት፤ “ሦስት ተማሪዎች ሞቱ” የሚል ወሬ በመሰራጨቱ ተቆጥተው በመጡየአካባቢው ወጣቶች በደረሰባቸው ከፍተኛ ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ አንማው ዳኛቸው ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለቤተ ክርስቲያን ህንፃ ግንባታ ግልጋሎት የሚውል ሲሚንቶ በራሳቸው መኪና ጭነው ወደ አካባቢው ተጉዘው የነበሩ ጥንዶች ንብረትም መቃጠሉ ታውቋል።

በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩም 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግርዋል።

በተፈፀመው ድርጊት የአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ መንግሥት ማዘኑን አቶ አንማው ገልፀው በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉትን ማሰር መቀጠሉን ጠቁመዋል።

(ከኃላፊው ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

 https://amharic.voanews.com/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here