• ልዑል እግዚአብሔር አገራችንና ሕዝባችንን ሰላም ያድርግልን!
•  //የጻድቅ ሰው ጸሎት ያድናል!//

የእኛ የኢትዮጵያን አማካይ እድሜ 100 ዓመት አይደርስም፡፡ በአምላክ ፈቃድ የ100 ዓመት እድሜ ባለጸጋ የሆኑ አባት ለማግኘት ወደ ገዳማቸው አመራሁ፡፡

ዓዲ ግራት ደብረ መድኃኒት መድኃኒዓለም ካቴድራል ዘለቅሁ፡፡ ከካቴድራሉ ጀርባ ገዳም ገድመው የሚኖሩ አባት ዘንድ ደረስኩ፡፡ አንድ የእርሳቸው ተማሪ ‹‹የኔታ›› ደጅ አደረሰኝ፡፡

ከገዳሙ መግቢያ በረንዳ በስተግራ በኩል በግዕዝ ቋንቋ ይህ መልዕክት ተጽፏል፡፡

‹‹ዝንተ መምህር አባ ዮሴፍ ዘተፈነወ እምሃበ ብፅዕ አቡነ ዮሐንስ ቀዳማዊ ውሰተ ብሔር አጋመ ከመ ይስብክ መንግስተ እግዚአብሔር›› – አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ትግራይ

(ትርጉሙ – በብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ዓዲ ግራት ሄደው ወንጌል እንዲያስተምሩ መመረጣቸውን ይጠቁማል)

መምህር አእላፍ ወመምረ ትህትና መልዕአከ ፀሐይ ቆሞስ ዮሴፍ ገ/መድህን (የብሉያት፣ የሐዲሳት እና የፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ መምህር) እግር ሥር ተንበርክኬ፣ ጉልበት ስሜ ሰላምታዬን አቀረብኩ፡፡

ከእግር ሥራቸው፤ ወለሉ ላይ ተቀመጥኩ፡፡

የ100 ዓመታት እድሜ ባለጸጋ ሕይወትን በ100 ደቂቃዎች ወግ ለመጨረስ አይሞከርም፡፡ ገዳም ውስጥ በደንብ ይንቀሳቀሳሉ፤ ጆሮዎቻቸው ከመስማት፣ ዓኖቻቸው ከማየት፤ አንደበታቸው ከመናገር አልደከመም፡፡

‹‹ኦ! … አምላክ ተአምራትህ ድንቅ ነው!›› አልኩ በለሆሳስ፡፡

እነዚህ ደጋግ አበው፤ (ከኢትዮጵያ አባቶች አንዱ በብዙሃን ዘንድ ይናፈቃሉ) … እኚህ የኔታ – የሕይወታቸው ፍሬ ቅድስና፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ የዋህነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅር … ናቸው፡፡

ታላቁ አባታችን የኔታ መልአከ ፀሐይ አባ ዮሴፍ ቆመስ ሃይማኖትን በምግባር፣ ሊቅነትን በደግነት፣ ሐዋርያዊነት በጽናት ጠብቀዋል፡፡ እድሜ ልካቸውን ቤተ ክርሲቲያናቸውን ሕዝባቸውን አገልግለዋል፡፡

***
/ ከየኔታ – ከክቡር ቆመስ መልአከ ፀሐይ አባ ዮሴፍ ጋር ቃለ መጠይቅ ጀመርኩ /

ጌጡ – ሲመተ ዲቁንና በስንት ዓመትዎ ተቀበሉ?

የኔታ – ከትግራይ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ይስሃቅ ሊቀ ጳጳስ እጅ በ1922ዓ.ም. በ13 ዓመቴ ሲመተ ዲቁናን ተቀበልኩ፡፡

ጌጡ – የኔታ የዚህችን ዓለም ጣዕም ከልብ የናቁት መቼ ነው? የብትህትውና እና የምንኩስና ሕይወትዎን በምን ምክንያት ጀመሩ?

የኔታ – እግዚአብሔር መንኩስ ብለ አዘዘኝ፡፡ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በሚገኘው ቆላ ተንቤን ወረዳ – ልዩ ቦታው መነዌ በተባለ አካባቢ በሚገኘው ቅድስት ማርያም ቅኔ ተማርኩ፡፡ … መነንኩ፡፡

ጌጡ – የኔታ ምድራዊ ፈተና አልገጠሞትም? … ለምሳሌ ወላጆችዎ ከምናኔ ከገዳም ይውጡ አላሎልዎትም?

የኔታ – እናቴ ሦስት ጊዚያት መነዌ ቅድስት ማርያም አባ ሊባኖስ ገዳም መጥተው ነበር፡፡ ከምነና በኋላ እናትና አባት ብሎ ነገር የለም፡፡ እናቴ ለመኑኝ – አስለመኑኝ፡፡ ‹አርፍን ይዞ ወደኋላ የሚመለስ ሰው ማነው?› … ፈቃደ እግዚያአብሔር ሆኖ ለመመንኮስ ወሰንኩ፡፡ ይሄን በተመለከቱ ጊዜ እናቴ መርቀውኝ ተመለሱ፡፡ …

አባ ዘንድ ቀረብኩ፡፡ እኔ ልመነኩስ እፈልጋለሁና አባ እባክዎን ያመንኩስኝ ብዬ ጠየኳቸው፡፡ አባም ማኅበሩን ጠየቁ፡፡ ማኅበረ መነኮሳቱም ‹እመለኩሳለሁ ማለቱ መልካም ነው፡፡ ይሁን እንጂ ህፃን ስለሆን ትንሽ ቢቆይ ጥሩ ነው፡፡ … ባይሆን የሟቹን የአባ ኃይለማርያም ቤት ይሰጠው› ብለው ወሰኑ፡፡

ማኅበረ መነኮሳቱ በሙሉ በአበምኔቱ አማካይነት ተሰብስበው ተገቢውን ጸሎት በማድረስ ስርዓተ ምንኩስናውን ፈፀምኩ፡፡ አልባሰ ምንኩስናን አልብሰው አስኬማ መልአክትን ደፉልኝ፡፡ መነኮሳቱና የአብነት ተማሪዎች ‹‹አባ ዮሴፍ›› የሚል ስም አወጡልኝ፡፡

ጌጡ – የኔታ ከዓዲ ግራት ተነስተው የት አከባቢዎች አሰተምረዋል ?

የኔታ – ዓዲ ግራትን ማዕከል በማድረግ በእግሬ እየተጓዝኩ (እንደ አሁን መኪና አልነበረም) ከኢሮብ አስከ ቆላ ገረዓልታ፤ ከደብረዳሞ አስከ አቡነ አረጋዊ ገዳም – እስከ ደብረ ገሪዛን ጉንዳጉንዶ ቅድስት ማርያም ገዳም የአቅሜን ያህል ስበከተ ወንጌል በመንፈሳዊ ልጆቼ ላይ ዘርቻለሁ፡፡

ጌጡ – በወንጌል ስብከት ኤርትራ አልዘለቁም?

የኔታ- አስመራን ጨምሮ በኤርትራ ምድር በከረን ማኅበረ ሥላሴና በአቡነ ፎሊጶስ ገዳም ተዟዙሪያለሁ

ጌጡ – መምህር አእላፍ የኔታ መልእከ ፀሐይ አባ ዮሴፍ ፤ ጉባኤ አስፍተው፤ ወንበር ዘርግተው ማስተማር መቼ ጀመሩ?

የኔታ – በትምህርት ቤት ሳለሁ ጀምሮ አስተምር ነበር፡፡ ለምሳሌ ጸለምት አከባቢ በቆላማ ሽፍራ በሚገኝ ቤተ ክርሲቲያን ሁለት ዓመት አስተምሪያለሁ፡፡ ሃያ አምስት ልጆችን ለዲቁና አብቅቻለሁ፡፡ … / አሉና በዝምታ ተዋጡ/

//የኔታ እንደተረዳኋቸው – አስተምሪያለሁ፣ አድርጊያለሁ፣ ፈፅሚያለሁ ማለትን አይወዱም፡፡ አልፈቀዱም፡፡//

የኔታ በ1977ዓ.ም. (በዚያ ክፉ ቀን) ትልቅ ሐዋሪያ ተግባር ፈፅመዋል፡፡ (አሁን ድረስ በዚህ መንፈሳዊ ተግባራቸው ይመሰገናሉ፤ ይደነቃሉ)

የኔታ መፍቀሬ ወራዙት አጽንኦ በአታቸው በጣም ያስቀናል፡፡ ‹‹አጽንኦ በአት›› ማለት ለሥራ፣ ለብህትውና በተመረጠ በተለየ ቦታ ጸንቶ መኖር፤ ወዲህ ወዲያ አለማለት ነው፡፡

***
ኃይመተ – ዮሴፍ (የዮሴፍ አዳራሽ) የሚል ግለ ታሪካቸውን የያዘ መጽሐፍ ታትሟል፡፡ አዘጋጆቹን ለሰጧቸው ከበሬታ (ትልቅ ሥራ) ለአድናቆትም፤ ለምስጋናም እጅ እነሳለሁ፡፡

• መምህረ ትህትና መጽሐፍት የሰዎች ማስታወሻ
• መምህር በርሀ ተስፋ መስቀል
• ወንድም ፀጋይ ትካቦት … የአድናቆት እና የአክብሮት ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፡፡ (በእናንተ – በየኔታ የመንፈስ ልጆች ቀንቻለሁ)

የኔታ – የእርሳቸው እና የገዳሙ በር ሁሌም ክፍት ነው፡፡ ምክርን ሽቶ ለሚመጣ ሁሉ ችግር ፈቺ የምክር አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

//… የኔታ – የማሰረጊያ መልእክታቸውን አቀርቅሬ እያዳመጥኩ ነው… //

‹‹በል ልጄ! … አትጥፋ፡፡ እባክህን እንዲህ መጥተህ አጫውተኝ፡፡ … አደራ ልጄ … ልዑል እግዚአብሔር አገራችንና ሕዝባችንን ሰላም ያድርግልን … ልዑል እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን፡፡ …

• ልጄ ሆይ! … ስማ ጠቢብም ሁን፤ ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ! … ለታገሰ ሰው፤ እግዚአብሔር የድል ቀን አለው

***
የየኔታን ጉልበት ስሜ – ተነሳሁ፡፡


እርስዎም ለየኔታ አክብሮትን ለመግለጥ እና የየኔታን እድሜን እንዲያድለን ለበረከቱ ይህንን መልዕክት ሼር እናድርግ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here