‹‹ለኢንቨስትመንት በሚል ሰበብ አርሶ አደሩን በማደህየት ኢንቨስትመንቱን ማሳደግ አይቻልም፤መሬታቸው የሚወሰድባቸው አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ካሳ ማግኘት አለባቸው፡፡››ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው

የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ በ2011 በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ፣በህግ ማዕቀፎች እና አሰራሮች ላይ ሲሰጥ የነበረውን ክልላዊ የምክክር መድረክ ዛሬ አጠናቅቋል፡፡

አቶ ገዱ ለኢንቨስትመንት በሚል ሰበብ ብዙ አርሶ አደሮች መብታቸው ተጥሶ እንደነበር በመጥቀስ አርሶ አደሩን በማደህየት ኢንቨስትመንቱን ማሳደግ አይቻልም፤መሬት የሚወሰድባቸው አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ካሳ ማግኘት አለባቸው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ቀደም ሲል ካሳ የማያገኙበት ህግ የነበረ ቢሆንም ህጉን የማስተካከል እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል፡፡

አርሶ አደሮች እና የነባር ይዞታ ባለቤቶች መሬታቸውን ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲጠቀሙ መደረጉ ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት ከማገዙም በላይ ህብረተሰቡ ተረጋግቶ እንዲሰራ ያደርገዋል፡፡

በመሆኑም አርሶ አደሩን ከአላስፈላጊ እንግልት የምናድንበት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል፡፡

አርሶ አደሮች በጉልበተኛ ጥቅማቸውን የሚያጡበት ፍትሃዊ ያልሆነ አሰራር ካለ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ ህዝባዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ጠንክሮ መስራት እና የፍትህ ስርዓቱን ማስከበር ይጠበቅበታልም ነው ያሉት፡፡

ህገወጥ የመሬት ወረራን በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

በተለይ የወል መሬቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ግለሰቦች ይዞታ ስር እየገቡ በመሆኑ በፍጥነት መግታት ካልተቻለ ስር እየሰደደ ሄዶ ግለሰቦች ላይ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀር አስገንዝበዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ አካላት በባለቤትነት ይዞ በመንቀሳቀስ ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ለተከታታይ አምስት ቀናት የቆየውን የምክክር መድረክ የተካፈሉ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው በሚችሉት አቅም ሁሉ ህብረተሰቡን ለማገልገል ፍቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ወዳጅ ምስክር ከሰሜን ወሎ ዞን ፣ወይዘሮ በላይነሽ አሻግሬ ደግሞ ከደቡብ ጎንደር ፋርጣ ወረዳ በምክክር መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ናቸው፡፡ ከውይይቱ በቂ ግብዓት እንዳገኙ ነግረውናል፡፡

ተሳታፊዎቹ እንደነገሩን ወቅቱን መሰረት ያደረገ የገጠር መሬት አጠቃቀም ስልጠና መውሰዳቸው ለቀጣይ የተጣለባቸውን የህዝብ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ዝግጁ እንደሚያደርጋቸው አረጋግጠውልናል፡፡

በመዝጊያ ሰነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም ቢሮ ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ስራውን በአግባቡ ለመወጣት ጥረት እያደረገ ያለ ተቋም ነው ፡፡

መሬት ሀብት እና የማንነት መገለጫ መሆኑን በመረዳት የኃላፊነት ስሜት በተሞላበት መንገድ ሲንቀሳቀስ ለቆየው ለተቋሙ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ስራው አድካሚ መሆኑን በመጥቀስ ወደ ዘመናዊ የመረጃ ቋት ለማስገባት ተቋሙ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ከገጠር መሬት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ማንኛውም ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚችለው በመድረኩ ላይ የተሳተፈው ባለሙያ ነው፤

በተለይ በምዕራብ ቆላማው የክልሉ አካባቢዎች ለበርካታ ዘመናት ጥሩ አሰራር ያልነበረባቸውን ቦታዎች በዚሁ ተቋም ውስጥ በተሰማሩ ሙያተኞች እና አመራሮች አማካኝነት ውጤታማ በሆነ መንገድ ማስተካከል ተችሏል ብለዋል፡፡

በከተሞች ዙሪያ የሚኖሩና ትኩረት የማያገኙ አርሶ አደሮች ጥቅማቸው እና መብታቸው እንዲከበር በማድረግ በኩል ትልቅ ስራ ተሰርቷል፤ ተገፍተው ለነበሩ አርሶ አደሮች በተገቢው መንገድ ካሳ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡

(አብመድ)-ደጀኔ በቀለ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here