Home እንግዳ “ሌሎች ሴቶች ላይ የአሲድ ጥቃት ሳይ ይረብሸኛል፤ ህመሜን ያስታውሰኛል” ካሚላት መህዲ –...

“ሌሎች ሴቶች ላይ የአሲድ ጥቃት ሳይ ይረብሸኛል፤ ህመሜን ያስታውሰኛል” ካሚላት መህዲ – BBC News

1513
0

ካሚላት መህዲ በ1999 ዓ.ም የገና ዋዜማ ከእህቶቿ ጋር ከምትሰራበት ሱቅ አምሽታ ወደ ቤቷ ስትሄድ አንድ ሰው ወደ አጠገባቸው መጥቶ አሲድ ፊቷ ላይ ደፍቶ መሰወሩን በወቅቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበውታል።

ካሚላት በወቅቱ በደረሰባት የፊት መቃጠል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና ቢደረግላትም ቃጠሎው ከፍተኛ ስለነበር ከሀገር ወጥታ መታከም እንዳለበት ተገለፀ።

ጥቃቱን የፈፀመውም ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ከዚያ በኋላ ካሚላት በሼህ መሀመድ አሊ አላሙዲ ድጋፍ በፈረንሳይ ሀገር ሕክምና ለማግኘት ሄደች።

ከዚህ የህክምና ጉዞ በኋላ አልፎ አልፎ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ስለእርሷ ቢሰማም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ታይታ አታውቅም።

በዚህ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ፈረንሳይ ባመሩበት ወቅት በአየር መንገድ በመገኘት አቀባበል ካደረጉት የተለያዩ ሰዎች ምስል መካከል የካሚላትም አብሮ ታየ።

ይሄኔ የካሚላት ጉዳይ ለማህበራዊ ሚዲያው መነጋገሪያ ሆነ።

ካሚላት ፈረንሳይ ጠቅልላ መኖር ከጀመረች ስድስት ዓመት ሆኗታል። ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናትም ሆናለች።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ፈረንሳይ እንደሚመጡ ስትሰሚ ምን ተሰማሽ?

ካሚላት ፡ ደስ የሚል ስሜት ነው የተሰማኝ። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንድ ቅን የሆነ መንግሥት ወዳለህበት ሊያይህ ሲመጣ የሚሰማህ ስሜት ነው የተሰማኝ።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ አየር መንገድ አቀባበል ከሚያደርጉት ሰዎች መካከል እንድትሆኚ እንዴት ተመረጥሽ?

ካሚላት ፡ እዚህ ለእርሳቸው አቀባበል የተቋቋመ ጊዜያዊ ኮሚቴ ነበር።

ዲያስፖራው ከኤምባሲው ጋር በመሆን ማለት ነው። እዛ ላይ ነው የመረጡኝ። እና ተመርጠሻል ሲሉኝ በደስታ ተቀበልኩኝ።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ለኤምባሲው ቅርብ ነሽ ማለት ነው።

ካሚላት ፡ ማለት ሁላችንም እዚህ ያለን ኢትዮጵያዊ ኤምባሲ የሚያስፈልገን ሲኖር እንሄዳለን፤ እንጠይቃለን።

ከኤምባሲው በተሻለ እዚህ ካሉ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ጥሩ ቦታ አለኝ። እኔም ለሰዉ ያለኝ አመለካከት ተመሳሳይ ነው።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አየር መንገድ ሲያገኙሽ ምን አሉ?

ካሚላት ፡ በጊዜው ሰላምታ ብቻ ነው የተለዋወጥነው። በጣም እንደተሰማቸው ያስታውቅ ነበር።

እዛ ሰዓት ላይ ግን ምንም መነጋገር አትችልም ነበር። ይበርድ ነበር።ጊዜውም አጭር ነበር። ሰላምታ ብቻ ነው የተለዋወጥነው።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ከዛ በኋላ የማውራት ጊዜ አላገኛችሁም።

ካሚላት

ካሚላት ፡ አላገኘንም።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ፈረንሳይ ኑሮሽን አድርገሻል። ሰዎች ሲያዩሽ ምን ሆነሽ ነው ብለው አይጠይቁም።

ካሚላት ፡ ይጠይቃሉ። መጀመሪያ ፊታቸው ላይ የምታየው ነገር ይኖራል። ከዛ በትህትና ይጠይቁሃል። እና እነግራቸዋለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ሁሌ መጠየቅ አይረብሽሽም?

ካሚላት ፡ አይረብሸኝም አልልህም ይረብሻል።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ አሁን አግብተሻል ወልደሻል ኑሮ እንዴት ነው?

ካሚላት ፡ ማግባት፣ መውለድ በጣም ደስ ይላል። ድርብ ኃላፊነት ነው። ኢትዮጵያ መጥቼ ካገባሁ በኋላ ልጄን እዚህ ፈረንሳይ ተመልሼ ነው የወለድኩት።

ባለቤቴ ግን አሁንም ኢትዮጵያ ነው ያለው አልመጣም። እና ልጄን ብቻዬን ነው የማሳድገው።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ልጅሽ ወንድ ነው ሴት

ካሚላት- ወንድ ልጅ ነው፤ አራት ዓመት ሞልቶታል።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ እና ፈረንሳይ ሕይወት እንዴት ነው?

ካሚላት- ደስ ይላል ጥሩ ነው። በርግጥ እንደ ኢትዮጵያ አይደለም። ልጅ ስታሳድግ ብቻህን ነው። የምሄድበት ሁሉ ይዤው ነው የምዞረው።

በተጨማሪም ባለቤቴ እዚህ ስላልሆነ የሕክምናዬን ነገር ለጊዜው ገታ አድርጌ ልጄን ማሳደግ ላይ አተኩሬያለሁ። ያው እርሱ ሲመጣ ወደ ሕክምናዬ ተመልሼ እገባለሁ።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ሕክምናው አላለቀም ማለት ነው?

ካሚላት ፡ አላለቀም እንዳየኸኝ ነው አይደል ያለሁት፤ ስለዚህ አላለቀም።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ሕክምናው ረዥም ጊዜ ይፈጃል ማለት ነው?

ካሚላት ፡ አዎ

ቢቢሲ አማርኛ ፡ አሁንም ወጪውን ማን ነው የሚሸፍነው?

ካሚላት ፡ በፊት በነበረው ሁኔታ ለአንድ ዓመት በሼክ መሀመድ አሊ አላሙዲ ወጪ ስታከም ነው የነበረው። እዚህ ጠቅልዬ ከመጣሁ በኋላ የፈረንሳይ መንግስት ነው የሕክምና ወጪዬን የሚሸፍነው።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ልጅሽ ግን ይጠይቅሻል ምን እንደደረሰብሽ?

ካሚላት ፡ (ፈገግታ) እርሱ ነገር ትንሽ ከባድ ነው። ገና መጠየቅ አልጀመረም። ያው እናት እናት ናት ታውቃለህ። ወደፊት ሳስብ ግን ትንሽ የሚያስጨንቀኝ እርሱ ነው።

በምን መልኩ ላስረዳው እንደምችል አላውቅም። ትንሽ ይከብዳል። በፊት ያለኝ ስሜትና አሁን ልጅ ሲኖረኝ ያለኝ ስሜት የተለያየ ነው።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ሴት ልጅ ብወልድ እንዲህ አይነት ጥቃት ሊደርስባት ይችላል ብለሽ ትሰጊያለሽ?

ካሚላት ፡ አይ ስለነገ አላህ ነው የሚያውቀው። እንደዛ ብዬ ማሰብ አልፈልግም። በአሁኑ ሰዓት የሚጠቃው ወንዱም ሴቱም ነው። ስጋቱ ጾታ ለይቶ ብቻ ሳይሆን የትኛውም ጾታ ላይ ስጋት ይኖርሃል።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ በወቅቱ አንቺ ላይ ጥቃት ሲደርስ እህትሽም ላይ ነበር ጥቃት የደረሰው አሁን በምን ሁኔታ ላይ ነች?

ካሚላት ፡ አንዷ ብቻ ሳትሆን ሁለት ናቸው ከኔ ጋር ሆነው ጥቃት የደረሰባቸው።

በጊዜው ሕክምና አድርገዋል።አሁን የየራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ነው።

ቤተሰቤ አዲስ አበባ ነው ያለው። ቤተሰብ ሁል ጊዜ ሲያዝን ሲሰጋ ነው የሚኖረው።ስጋት ስልህ ከመፍራት አንፃር ሳይሆን ለኔ ይኼ ነገር ባይደርስ ይመርጣሉ።

የትም ቦታ ሲያዩህ ከአንተ የበለጠ እነርሱ ናቸው ልባቸው የሚሰበረው። በርግጥ የኔ ማግባት መውለድ እናት አባቴን ቀና ሊያደርግ ይችላል።

ምንም ቢሆን ግን ቤተሰብ ናቸውና ሁል ጊዜ አንደተጎዱ ነው። የእነርሱን ጉዳት መቀየር ብችል ደስ ይለኛል።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን አየር መንገድ ስትቀበይ ሲያዩሽ የድሮውን ምስልሽን አውጥተው ማጋራት ጀመሩ።

ቤተሰቦችሽ ጋር የድሮ ፎቶዎችሽ አልበሙ ውስጥ አለ። ቤት ውስጥ ያንን ምስል እያዩስ የመረበሽ ነገር አለ?

ካሚላት ፡ ቤተሰቦቼ እነዛን ፎቶዎች እንዳያቸው አይፈልጉም። እነርሱም እንዲረበሹበት አናደርግም። በርግጥ እንደዚህ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያጋሩት ይረብሻል።

ለቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም። እነዛ ፎቶዎች ለትውስታ መውጣታቸው ጥሩ ቢመስልም እኛ ቤተሰብ ጋር ግን ሁሌ ረብሻ ይፈጥራል።

አሁን ደግሞ ልጅ አለኝ። ልጄ ላይ ወደፊት ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ አንቺ ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የተለያዩ ሴቶች ላይ ጥቃት ደርሶ ሰምተናል ፤ አንቺ እነዚህን ነገሮች ስትሰሚ የሚፈጥርብሽ ነገር ምንድን ነው?

ካሚላት ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍራንክፈርት በአውሮጳ የምንገኝ ኢትዮጵያውያንን ሰብስበው ሲያናግሩ ጥያቄ ያቀረብኩት ይህንን የሚመለከት ነው።

የኔ ጥቃት እንደ ዋዛ እንደ ተራ ነገር ሆኖ ለሌሎቹ መጥፎ ምሳሌ ሆኗል። አሁን አሲድ ጥቃት እንደ ፌዝ ነገር ሆኖ የአይን ብርሀንን እስከማጥፋት ደርሷል።

ያንን ሳይ የበለጠ በጣም ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም አንተ ላይ ሲሆን የሚሰማህን ስሜት ትቀበለዋለህ። ሌሎች ላይ ሆኖ ሳየው ግን ወደ ስሜቴ እመለሳለሁ።

ሕመሜን መልሶ እንዳስታውሰው ያደርገኛል። ይህ በጣም ነው የሚረብሸኝ። ከዚህ አንፃር ነበር ጥያቄ ያነሳሁት።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሾመዋል። ለኢትዮጵያ ሴቶች ፍትህን በማግኘት ረገድ ለውጥ ይኖራል ብለሽ ተስፋ ታደርጊያለሽ?

ካሚላት ፡ ኢንሻ አላህ። 10 ሴት ሚኒስትሮች አሉን። ፕሬዝዳንታችን ሴት ናቸው። አሁን ደግሞ ሴት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አግኝተናል።

በጣም የሚያስደስት ነው።ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ሁሉም ሰው ለውጥ የሚፈልግ ይመስለኛል። ተስፋ አደርጋለሁም ብዙ እጠብቃለሁም።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ አንቺ ላይ ለደረሰው ጥቃት የተሰጠው ፍርድ አነስተኛ ነው በማለት ተሰምቶሽ ያውቃል?

ካሚላት ፡ አዎ በርግጥ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ድምፅ ተረባርቦልኛል። የተለመደ አይነት ጥቃትም ስላልነበር ሁሉም ሰው ተረባርቧል። ከኔ የበለጠ ሰዉ ነበር ሆ ብሎ የወጣው። ፍርዱ ራሱ ከፍ ያለ ነበር የተሰጠው። የሞት ፍርድ። በኋላ ላይ ነው በይግባኝ የተቀነሰው።

እንደገና የሴቶች ጉዳይ አቤት ብሎ ነው እድሜ ልክ ወይንም 25 ዓመት የሆነው። እኔ የማየው ይህ ነገር በሰዓቱ የማያዳግም ውሳኔ ቢወሰን ኖሮ ዛሬ በአሲድ የተጠቃን ሴቶች አንበረክትም ነበር እላለሁ።

ለኔ ብቻ ሳይሆን ለሕብረተሰባችን ብሎ ነበር ፍርድ መሰጠት የነበረበት። አሁንም የማያዳግም ቅጣት እስካልተወሰነ ድረስ ይህ ነገር መቀጠሉ አይቀርም።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ የሴቶች ጥቃትን ለማስቆም የሚሰራ ትምህርት የሚሰጥ ተቋም የመመስረት ሀሳብ የለሽም?

ካሚላት ፡ አለኝ። አሁን ራሱ እዚህ ፈረንሳይ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ሉሲ ወይም ድንቅነሽ የሚሰኝ ማህበር አቋቁመን እየተንቀሳቀስን ነው።

ቢቢሲ አማርኛ ፡ መቼ ነው ወደ ኢትዮጵያ የምትመጪው?

ካሚላት ፡ ኢንሻ አላህ! እኔ ከምመጣ የባለቤቴ መምጫ ቢፈጥንልኝ ይሻላል̈ (ሳቅ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here