ከአንድ ሁለት ቀናት በፊት እዚሁ አዲስአበባ መኪናዬን እያሽከረከርኩበት ባለሁበት መንገድ ላይ ሦስቴ ፍተሻ አጋጥሞኛል።

የፍተሻው መንስኤ ከሕገ ወጥ የጦር መሣርያ ዝወውር ጋር የሚገናኝ እንደሆነም ከአንዱ ፈታሽ ተነግሮኛል።

ቆይቶም ወደ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ሥር የዋለ የነፍስ ወከፍ የጦር መሣርያ ፍተሻውን ተከትሎ እንደተደረሰበትም ሲወራ ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት በተለይም ወደ መዲናይቱ በሕገወጥ መንገድ ሊገባ ሲል በሕዝብ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር የዋለ የጦር መሣርያ መዳፉ ውስጥ እንደገባ በተደጋጋሚ እያስደመጠን ነው።

ሁለት ጥያቄዎችን ላንሳ፦

1. ይህ የሕገወጥ የመሣርያ ዝውውር ቀድሞም የነበረ ነገር ግን አሁን ለውጡን ተከትሎ እየተደረገ ባለው ጥብቅ ቁጥጥር የተደረሰበት ነው?

ነገሩ እንደዚህ ከሆነ የለውጥ አመራሩ ምሥጋና ሊቸር ዘንድ ይገባዋል።

2. የሕገወጥ መሣርያ ዝውውሩ ለውጡን ተከትሎ ከተፈጠሩ ቀውሶች የተነሳ እየመነደገ ይሆን?

ማለትም መንግስት ዜጎችን ከሥርዓት አልበኞች መጠበቅ ስለተሳነው ዜጎች ራሳቸውን ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ በመጀመራቸው የነፍስ ወከፍ የጦር መሣርያ ፍላጎቱ ጨምሮ ይሆን?

መልሱ “አዎን” ከሆነ (የኔ አዎን ነው) መንግስት… “ይህን ያህል ሕገ ወጥ የጦር መሣርያ ወደ አዲስ አበባ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ሥር ዋለ”… እያለ የሚነግረንን ዜና እንደ “የምስራች” ሳይሆን እንደ “መርዶ” ሊያስደምጠን ዘንድ ይገባዋል፣

ለሕገ ወጥ መሣርያ ዝውውሩ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ተጠያቂው ራሱ መንግስት ስለመሆኑ ልብ ሊል ዘንድ ይገባዋል።

የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ ስለተሳነው ዜጎች ራሳቸውን ለመጠበቅ የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ በመጀመራቸው መንግስት በዜናው ሊሸማቀቅበትና ሊያፍርበት ዘንድ ይገባል።

ሌላው የገረመኝ በተደጋጋሚ መሣርያዎቹ በድብቅ ሊገቡ ሲል እንደተደረሰባቸው የሚነገረን ወደ አዲስ አበባ ነው።

ይህ ምን ማለት ነው? ገጠሬውና ሌላው ከተሜው ትጥቁን አደራጅቶ የቀረችው አዲስ አበባ ነች ማለት ነው?

ወይስ መሣርያው ከአዲስአበባ ተነስቶ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ይሰራጫል?

በሌሎች የክልል ከተሞችና በገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍሎች የሕገወጥ የጦር መሣርያ ስርጭት ቁጥጥር እየተደረገ ይሆን?

ለምሳሌ ወደ አዋሳ፣ ወደ መቀሌ፣ ወደ ባሕርዳር አሊያም ወደ ሌሎቹ የሀገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ሕገወጥ የጦር መሣርያ ሊገባ ሲል ተያዘ የሚለው ዜና እንደ አዲስ አበባው አይደመጥም።

ያም ሆነ ይህ መንግስት “ሕገወጥ የጦር መሣርያን በቁጥጥሬ ሥር አደረኩ” የሚለውን ዜና ሰርክ ከማስደመጥ ባለፈ የዝውውሩን መነሻ ሰበዞችን እየመዘዘ ዘለቂ መፍትሄ ቢሰጥ ይመረጣል የሚል አቋም አለኝ።

ከሁሉም በላይ አደናጋሪ የሆነው በሕገወጥ መሣርያ ዝውውር ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ወንጀለኞች ምን ዓይነት የፍርድ ቅጣት እንዳገኙ መንግስት ይፋ ከማድረግ መቆጠቡ ነው።

የሕገወጥ መሣርያ ዝውውሩ ዲዛይነሮች እነማን ናቸው? ሰንሰለቱስ ምን ይመስላል?

መነሻውና መድረሻውስ? እነማንስ በቁጥጥር ሥር ዋሉ? ምንስ ተፈረደባቸው?

በዚህ ረገድ ከመንግስት ምንም ዓይነት መረጃ ይፋ ሲሆን አናስተውልም። መንግስት ወንጀለኛ መያዙን ብቻ ይነግረንና ቀጣዩን ሂደት በዝምታ ያልፋል።

በነባር ወንጀለኞች ላይ ተገቢ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶ ይፋ ያለመሆን ለአዳዲስ ወንጀለኞች ማቆጥቆጥ በር ይከፍታል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት ከሚስተዋለው እንደ እግር ኳሱ ቀርፋፋ የ”Replay” ዓይነት የፍርድ አሰጣጥ ጉዞ ታቅቦ ቀልጣፋ አሰራርን ማስፈን ይጠበቅበታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here