ኤፍቢአይ የፍሎሪዳውን ግድያ በተመለከተ የደረሰውን ማስጠንቀቂያ እንዴት እንደተመለከተው ራሱ ላይ ምርመራ እያደረገ ነው።

ረቡዕ እለት ግድያውን የፈፀመው የ19 ዓመቱ ኒኮላስ ክሩዝ ሆን ብሎ 17 ሰዎችን በመግደል ተወንጅሎ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ግድያው እንደ አውሮፓውያኑ ከ2012 ወዲህ በአሜሪካ አስከፊው ሰዎች ህይወታቸውን ያጡበት አጋጣሚ ነው።

ወጣቱ ባለፈው ዓመት በዩቲዩብ ላይ ስልጡን የትምህርት ቤት ተኳሽ እንደሚሆን አስተያየቱን አስፍሮ ነበር።

ይህን አስተያየት የተመለከቱ ሰዎችም በወቅቱ የፀጥታ ሃይሎችን እንዳስጠነቀቁ ኤፍቢአይ አምኗል።

ይማርበት በነበረው ትምህርት ቤት ቅጥር የጀርባ ቦርሳ እንዳይዝ ክሩዝ ተከልክሎ ነበር።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ደግሞ መምህራኑም ስለ ወጣቱ አደገኛነት ማስጠንቀቂያ ደርሷቸው ነበር።

ኤፍ ቢአይ የዩቲዩቡን መልዕክት ቢመረምረውም አስተያየቱ የማን እንደሆነ ማለትም ማን እንደለጠፈው መሉ ለሙሉ መለየት አለመቻሉን አስታውቋል።

ጥቃቱ የተፈፀመው ፍሎሪዳ ፓርክላንድ ውስጥ በሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን 17 ሰዎች ሲገደሉ 14 ቆስለዋል።ከነዚህ ሶስቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

ሃሙሰ እለት ለመርማሪዎች ቃሉን የሰጠው ክሩዝ ጥቃቱን እንደፈፀመ በማመን የጀርባ ቦርሳውም በጥይት የተሞላ እንደነበር ተናግሯል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here