“መቀመጥ መቆመጥ” ይባላል – አሁን አሁን ደግሞ ሳይንቲስቶች በተመሳሳይ ድምፀት “መቀመጥ እንደ ማጨስ ነው” እያሉ ነው፡፡ ረጅም ሰዓት አንድ ቦታ ተቀምጠው ሥራ የሚሰሩ ከሆነ ልክ ሲጋራ እንደሚያጨሱ ያህል ጤናዎትን እየጎዱት ነው ነው ነገሩ፡፡

ሰሞኑን ኒውዩርክ ታይምስ ይዞት የወጣው የሳይንስ መረጃ ረጅም ሰዓት ተቀምጠው የሚሰሩ ሰዎች የልባቸውን ጤና እየጎዱት ነው ይላል፡፡ የጥናት ውጤቱ እንደሚለው ረጅም ሰዓት ተቀምጦ መስራት የልብ ጡንቻዎች እንዲዳከሙና ጉዳት እንዲደርስባቸው ያደርጋል ይህም ውሎ አድሮ ለልብ ሕመም አጋላጭ ነው፡፡

ዘገባው እንደሚለው በቀን ውስጥ ከ9 ወይም 10 ሰዓታት በላይ ተቀምጠው የሚሰሩ ሰዎች ለስኳር በሽታ፣ ለልብ ሕመም እና ለሌሎች የጤና ችግሮች የተጋለጡ ናቸው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የወጣ ሌላ ጤና ነክ የሳይንስ መረጃ ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ይመለከታል፡፡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለመላ የሰውነት ክፍል የጤና በረከት እንደሚችር ቢታወቅም ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ግን ሳይንቲስቶች እስካሁን የሚያውቁት ነገር የለም –

አሁን ግን ሳይንቲስቶች በዚህ አቅጣጫ አንዳች ብርሃን ፈንጣቂ እውነት ላይ ሳንደርስ አልቀረንም እያሉ ነው፡፡

በጥናት ተደረሰበት የተባለው እውነታ እንደሚለው፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወቅት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች መካከል በህዋሳት ደረጃ የሚደረገው የእርስ በርስ ግንኙነት እጅጉን ይጨምራል፡፡

ይህ ግንኙነት የሚካሄደው ውስጣቸው መልዕክት ባዘሉ ፊኛ መሰል ቅንጣቶች ሲሆን እነዚህ ቅንጣቶች በደም ውስጥ ከአንዱ የሰውነት ክፍል ወደሌላኛው እንደሚሄዱ ማወቅ ተችሏል፡፡

በአጠቃላይ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወቅት ሁሉም የሰውነት ክፍሎቻችን እጅግ ተራርቀው የሚገኙትም ጭምር እርስ በርስ ይንሾካሾካሉ፣ ያወራሉ፣ ይነጋገራሉ ያሉት አንድ የጥናት ቡድኑ አባል ሁሉም የሰውነት ክፍሎች ደግሞ በጋራ ከጉበት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ሲፈጥሩ አስተውለናል ብለዋል፡፡

ይህ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወቅት በሰውነት ክፍሎች መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የሚካሄድ ካሜካላዊ መስተጋብርና የመረጃ ልውውጥ፣ ስፖርት ሁለንተናዊ የአካል ጤንነትን ሊያጎናፅፍ የቻለበትን ምክንያት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ተብሏል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here