ማሰብ ችግር ነው!
መቶ እግርን ሁላችሁም ታውቁታላችሁ። እንደ ስሙ ባለ መቶ እግር ትንሽ ፍጥረት ነው።

ታዲያ ይህንን ፍጥረት ፈላስፋው እንቁራሪት አየውና ተገረመ።

ሁለት እግር እሺ፣ አራት እግርም ይሁን! ምን አይነት ፍጥረት ነው፣ መቶ እግር ኖርት፣ የትኛውን ከየትኛው እያስቀደመ ወይም እያስከተለ አውቆ የሚጓዘው።

” ግራ የሚገባ ነው” አለ ለራሱ። አግራሞቱን ለራሱ ውጦ አላስቀረም ።

ይህንኑ ጥያቄ ይዞ፣ ከመቶ እግር ዘንድ ቀረበ። እንዲህም አለ፦

” መቶ እግር ሆይ! በጣም አስደናቂ ፍጥረት ነህ! ከእግሮችህ መሐል አስቀድመህ የምትዘረጋው የትኛውን ነው? የምታስከትለውስ? ”

መቶ እግር በአድናቆቱ ተደሰተ። የተደነቀበትን ተግባር ሊከውን እግሮቹን ለማንቀሳቀስ ቢሞክር አቃተው።

ሐሳብ በአእምሮው ውስጥ ከገባ በኋላ፣ ሁሉ ነገር ከባድ ሆነ።የግራው ነው የቀኙ፣ ፊተኛው ነው ኋለኛው? የቱ ነው የሚቀድመው? ማሰብ ባይጀምር ኖሮ መልስ የማያስፈልገው ጥያቄ ነበር።

አሁን ግን አንድ ስንዝር እንኳን መራመድ አቅቶት ይንፈራፈራል።

በመጨረሻ መቶ እግር ለፈላስፋው እንቁራሪት እንዲህ አለው፦

” ፈላስፋው ሆይ! እባክህ ይህንን ጥያቄ ሁለተኛ ለሌላ መቶ እግር እንዳታቀርብ! የእኔን ህይወት እንዳበላሸህ ፣ የሌላውንም እንዳትደግም! ”

መጠየቅ የሚያስፈልግበት ግዜ አለ!

ማመን የሚያስፈልግበት ግዜ አለ!

ማሰብ የሚያስፈልግበት ግዜ አለ!

መመሰጥ የሚያስፈልግበት ግዜ አለ!

ፍልስፍና አስፈላጊ የሚሆንበት ግዜ አለ!

ሀይማኖት አስፈላጊ የሚሆንበት ግዜ አለ!

አብዛኛዎቹ ፈላስፋዎች የማያስፈልግ ጥያቄ፣ በማያስፈልግ ወቅት የሚጠይቁ ናቸው―የራሳቸውን የማሰብ ብቃት ለማሳየት ሲሉ ብቻ።

መኖር ለሁላችንም የተሰጠን ስጦታ ነው ታዲያ ህይወትን እንድንኖራት እንጂ እንድንረዳት አልተፈጠርንም ።

አሁን ይህንን ሐሳብ እዚህ ያመጣሁት ማሰብ አያስፈልግም ፣ ፍልስፍና አይረባም የሚል ሐሳብ ለማስረፅ ሳይሆን እውነት ናቸው ብለን የምናስባቸው ነገሮች ሁሉ አውዳዊ እንጂ ፍፁም አለመሆናቸውን ለማስረገጥ ነው።

ደግሞም እዚሁ መደምደሚያ ላይ የደረስነው አስበን መሆኑ ሳይዘነጋ!

ያንተ እውነት ያንተ ነው፤ የእኔ እውነት የኔ ነው! ትልቁ ስህተት የሚሆነው እንደ እኔ ሀይማኖተኛ ካልሆንክ ፤ እንደ እኔ ፈላስፋ ካልሆንክ ብሎ የራስን እውነት በግድ ሌሎች ላይ ለመጫን መሞከር ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here