በኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞን ቀስቅሶ የነበረው አዲስ አበባን በዙሪያዋ ካሉ የኦሮሚያ ከተሞች ጋር ያስተሳስራል የተባለው ማስተር ፕላን ተራማጅና

አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣል ብለው እንደሚያስቡ ኦህዴድ ሊቀ መንበር እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ኩማ ደመቅሳ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ባለፈው ሳምንት ኦዴፓ (የቀድሞው ኦህዴድ) በጅማ ከተማ ድርጅታዊ ጉባኤውን ባደረገበት ወቅት ተሳታፊ የነበሩት አቶ ኩማ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት አጭር ቆይታ

አወዛጋቢ ስለነበሩና እርሳቸው በከፍተኛ የስልጣን ሃላፊነት ላይ በነበሩበት ጊዜ ስለታቀዱና ተግባራዊ ስለተደረጉ ጉዳዮች ምላሽ ሰጥተዋል።

«ኦሮሞ እና አማራን የሚነጣጥሉ አይሳካላቸውም»

በተለይ በኦሮሚያ ውስጥ ተቀስቅሶ ለረጅም ጊዜ ለዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለትና ከ2006 ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ

የነበረው የአዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት እንዳለ ተናግረዋል።

ጉዳዩ ከመፈናቀል ጋር አብሮ ስለመጣ እንጂ «ተራማጅ አስተሳሰብ ነው ብዬ አስባለሁ» በማለት የሚናገሩት አቶ ኩማ፤

ጊዜ ሊወስድ ይችላል እንጂ ማስተር ፕላኑ አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣል ብለው እንደሚያስቡ ገልፀዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በተመሳሳይ ኦሮሚያ ውስጥ ለጠንካራ ጥያቄና ተቃውሞ ምክያት የነበረው የአዳማ ከተማን የኦሮሚያ ክልል መዲና እንድትሆንና የክልሉ መስሪያ ቤቶች ወደዚያው እንዲዘዋወሩ መደረጋቸው ይጠቀሳል።

ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ኩማ ውሳኔው ስህተት እነደሌለበት ያምናሉ።

አሁንም ወደኋላ መለስ ብለው ሲመለከቱ «አሁንም ያኔ የነበረኝ አቋም ስህተት ነው ብዬ አላምንም» ካሉ በኋላ፤ «አዳማ የክልሉ ዋና ከተማ ሆና እንደተቀየረች ብትዘልቅ ኖሮ ከተማዋ ታድግ እንደነበር» ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም ዋና ከተማን በመምረጥ ረገድ ሁሉንም እንቅስቃሴ ተቆጣጥሮ ሥራ ለማከናወን የተሻለው እንደሚመረጥ ጠቁመዋል።

በውሳኔው ውስጥም ግፊት እንዳልተደረገባቸው ሲያስረዱም «ያኔ ይህንን ያደረገው ሌላ ኃይል ነው የተባለው ውሸት ነው። ውሳኔውን የወሰነው እኔና ከእኔ ጎን የነበሩት ናቸው» ብለዋል።

ይህም ሆኖ የኦሮሞ ህዝብን መብት የሚነካ ውሳኔ አስተላልፈው እንደማያውቁ «በግሌ የኦሮሞ ህዝብ ፋይዳና መብት ላይ ተደራድሬ አላውቅም» በማለት አስረግጠዋል ተናግረዋል።

ከሰው የሚያገኙትን የድጋፍ ወይም የነቀፋ ምላሽ እንደማያስቡ ተናግረው «የኦሮሞን ህዝብ የሚጠቅም ሀሳብ ሁሌም አራምዳለሁ» ብለዋል።

አቶ ኩማ ደመቅሳ የቀድሞው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ያሁኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በክብር ካሰናበታቸው መስራችና ነባር አባላቱ መካከል አንዱ ሲሆኑ፤

በእሳቸው እይታ ትግል የሚካሄደው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ሆኖ ብቻ ስላልሆነ፤ ከኮሚቴው መሸኘታቸው ከትግል እንደማያግዳቸው «ትግል በተለያየ ደረጃ ይካሄዳል» በማለት ገልጸዋል።

የስንብት ሥነ ሥርዓቱ ሲካሄድ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው የሚናገሩት አቶ ኩማ፤

ለረዥም ጊዜ የቆዩበትን የትግል ጊዜ በማስታወስ «ከእኛ ጎን የነበሩና የተሰዉ ሰዎች ይህንን እድል አላገኙም። እኔ ይህንን እድል ስላገኘሁ ደስታዬ ወሰን የለውም» ብለዋል።

አቶ ኩማ ደመቅሳ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም በተለያዩ የፌደራልና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ለረጅም ጊዜ ሰርተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here