ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ሲሠራ ዓመታት ያስቆጠረው እንድሪያስ ጌታቸው ካሳዬ በውስጡ ታምቆ የቆየው የፀሃፊነት፣ ፊልም ሥራ ላይ የመሰማራትና ለተለያዩ ጥበባት ያለው ፍቅር ‘ብሪዝ ኢን ዘ ሩትስ’ የተሰኘውን ጥናታዊ ፊልም እንዲሠራ ገፋፍቶታል።

‘ብሪዝ ኢን ዘ ሩትስ’ የተሰኘው ጥናታዊ ፊልም ባለፈው ሳምንት በፈረንጆቹ የመጋቢት ወር መግቢያ ላይ ጀምሮ ከመጋቢት አጋማሽ በኋላ በተጠናቀቀው የኒው አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ እጩ ሆኖ ቀርቦ ነበር።

ይህ የእንድሪያስ ‘ብሪዝ ኢን ዘ ሩትስ’ የተሰኘው ፊልም በፌስቲቫሉ ሲታጭ የመጀሪያው ኢትዯጵያዊው ሲኒማ ባይሆንም ይህ ፊልም እውነተኛ ክንውኖችን ማሳየቱ የተለየ ያደርገዋል።

ፊልሙ ክሪስተን ታይሮን ጆዜፍ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ ማንነቱን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ አምርቶ ያደረገውን ጉዞ የሚያስቃኝ ነሥ።

ክሪስ በመጀመሪያ ወደ አፍሪካ ሄዶ ማንነቱንና አመጣጡን ለማግኘት በፈለገ ጊዜ ወደየትኛው ሃገር እንደሚያመራ እርግጠኛ አልነበረም።

ነገር ግን ወደ ሠር-መሠረቱ የመመለስ ፍላጎቱ በሕልም ተገልጾለት ወደ ላሊበላ መጓዝ እንደነበረበት ከተረዳ በኋላ ነበር ይህ መንፈሳዊ ጉዞው ሊጀመር የቻለው።

ክሪስተን ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት እቅዱን ለእንደሪያስ ሲያማክረው፤ እንድሪያስም ሃሳቡን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ አብሮት የሚጓዝ የቀረፃ ቡድን አብሮት እንዲጓዝ በጠየቀው መሰረት በመስማማቱ ሥራው ተጀመረ።

ይህንን የክሪስ ጉዞ አስደናቂ የተለየ የሚያደርገው እንደማንኛውም ሰው በመኪና ወይም በአውሮፕላን የተደረገ አለመሆኑ ነው።

”ክሪስ ‘እግዚአብሔር በሠራው እንሰሳና በእግሬ ብቻ ነው ወደ ላሊበላ የምጓዘው’ ሲለኝ ደስ ነበር ያለኝ” ሲል እንደሪያስ ያስታውሳል።

ጉዞው በአጠቃላይ 45 ቀናት እንደፈጀ የሚናገረው እንድሪያስ፤ የክሪስን ጉዞ ሲያስረዳ ብዙ ነገሮች እንደተቀያየሩ በተለይ ክሪስ በብዙ መልኩ እንደተለወጠ ይናገራል።

ይህ ጉዞ በአውሮፓውያኑ 2012 ይጀመር እንጂ እስከ ዛሬ እንደቀጠለ ነው። ይህም ማለት በጉዞው ሂደት የተጀመሩት ለውጦች በክሪስ ህይወት ውስጥ ሳይቆሙ መቀጠላቸው ነው።

ምንም እንኳን ክሪስ ከአንድ ወር በላይ የፈጀ ጉዞ ያድርግ እንጂ የፊልሙ ሥራ አራት ዓመታት ያህልን ፈጅቷል። ወደ ሰፊው መድረክ ለመድረስ ደግሞ ተጨማሪ 2 ዓመታት እንደጠየቀ እንድሪያስ ያስረዳል።

እንድሪያስ ”ይህ ሥራ ይህን ያህል ገንዘብ ፈጅቷል ለማለት ይከብደኛል። ምክንያቱም ካወጣው ወጪ በላይ የሚያስተላልፈው መልዕክት በገንዘብ ሊተመን የማይችል እንደሆነ ነው” ይላል።

እንድሪያስ ይህንን ፊልም ለመስራት እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቅሰው ተማሪ በነበረበት ጊዜ የገጠመው ነገር ነው።

ይህም የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በአሜሪካ በሚከታተልበተ ወቅት ኢትዮጵያ በአስከፊው የ1977ቱ ድርቅ ተመትታ ችግሩ የሃገሪቱ መለያ እስከመሆን ደርሶ ነበር።

በዚህም ምክንያት በሚማርበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሁለት ጥቁር አሜሪካውያን ተጣልተው ሲሰዳቡ ‘አንተ ኢትዯጵያዊ’ ይሉ ነበር። ይህም ‘አንተ ድሃ ለማለት’ እንደማለት ነበር።

”በዚህ በጣም ልቤ ያዝን ነበር። ምክንያቱም የኢትዮጵያን ታሪክ በትክክል ቢያውቁት ኖሮ ይህች ሃገር የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ኩራት መሆኗን ይገነዘቡ ነበር” ብሎ እንዲያስብ አደረገው።

”ፀሐፊና በመገናኛ ብዙሃን ውስጥ የምሠራ ሰው እንደመሆኔ ሁሌም እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ላላቸው ሰዎች እንዴት ብዬ ኢትዯጵያን ላስተዋውቃቸው እችላለሁ ብዬ አስብ ነበር” ይላል።

አንድሪያስ ክሪስተን ታይሮን ጆዜፍ ወደ ቢሮው መጥቶ ስለጉዞው ያለውን ሃሳብና ዕቅድ ሲያካፍለው ለዓመታት በውስጡ ለነበረው ፍላጎትና ምኞት ያገኘው ምላሽ እንደሆነ ነበር የቆጠረው።

”ከእኔ ይበልጥ እራሳቸውን የሚመስሉ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ቢነግሯቸው ይሻላል” የሚለው እንድሪያስ በዚህ በፊልም ላይ የሚትታየው ኢትዮጵያ የተሳሳተውን አመለካከት ለመቀየርና እውነታውን ለማሳየት ጠቃሚ ነው ብሎ ያምናል።

እንድሪያስ በኒው አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ በ’ብሪዝ ኢን ዘ ሩትስ’ ሥራው መታጨቱ በጣም እንዳስደሰተውና እንዳኮራው ገልጿል።

በተለይ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ የፊልም ሠሪዎችና የፊልም ውጤቶች እኩል መድረክ ላይ መቅረቡ ትልቅ ነገር እንደሆነም ይናገራል።

አብረውት የሠሩትና ለሥራው የተባበሩትን ባልደረቦቹን አመስግኖ፤ ፊልሙ በሁሉም ዘንድ ያለው ቦታ ትልቅ እንደሆነ እንድርያስ ይጠቅሳል።

”ፊልሙን እንዲመለከቱ የጋበዝኳቸው ሰዎችም ስሜታቸውን ሲኣካፍሉ፤ እነሱም የጉዞው ተሳታፊ የሆኑ ያህል እንደተሰማቸው ይናገራሉ።”

ሲጨምርም ”ብዙዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ረዥም ዓመታት ሆኗቸው ስለነበር ሃገራቸው ምን ያህል እንደናፈቃቸው ታውቋቸው ነበር።

ብዙዎቹም እኛም መቼ ይሆን እንደ ክሪስ አየሯን የምንተነፍሰው?” ብለው እራሳቸውን ይጠይቁ እንደነበር ያስታውሳል።

ይህ ፊልም ከበርካታ ፊልሞች መካከል ተመርጦ በኒው አፍሪካን ፊልም ፌስቲቫል ላይ ቀርቧል። የ’ብሪዝ ኢን ዘ ሩትስ’ን ቅንጫቢ ከዚህ በታች ይመልከቱ የተወሰደውም ከጆቢራው ፊልም ፕሮዳክሽን ነው።

‘ብሪዝ ኢን ዘ ሩትስ’ የተሰኘው ጥናታዊ ፊልም ክሪስተን ታይሮን ከአዲስ አበባ ወደ ላሊበላ በእግሩ የተጓዘውን መንገድ የሚሸፍን ነው።

BBC AMHARIC NEWS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here