በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የትግራይ አክቲቪስቱ ናሀሰናይ በላይ “ምናለበት ከህልሜ ባልነቃ ኖሮ” እያለ ነው…እስኪ ህልሙን ስሙት እና ሃሳባችሁን ወርዉሩ

“ትላንት ያየሁት #ህልም “ለምን ነቃሁ?” የሚያስብል ሆኖ አገኘሁት። በህልሜ ነው እንግዲህ:

ጠዋት ፌስቡኬን ስከፍት እነዛ “ግፋ በለው፣ ይታያል ዘንድሮ፣ የት አባታቹህ፣ እነተዋወቃለን በሚለው መለያቸው የማዉቃቸው የሁሉም ጎራ ፌስቡከሮች፣

ከጣና ልጆች በኩል “ትግራይ መሄድ አለብን፣ ፅዮንን ተሳልሜ፣ ጏደኛየ ደግሞ ሶላቱን ዉቅሮ ነጋሽ አድርሶ፤

ዓዲግራት ጥሕሎ በልተን አዳራችን የገራዓልታ ተራሮች ስር ለማድረግ አስበናል: ዓደይ መዓረይ፣ ህዝበይ ሽኮረይ እየመጣን ነው” የሚል ለጥፈው አየሁዋቸው።

ከመቐለው እንዳየሱስ ተራራ ስር ልጆች ደግሞ “ፋሲልን ጎብኝተን፣ ባህርዳር ጎራ ብለን የአቅማችንን እምቦጭ ነቅለን፣ ትኩስ ኮቴለትን ተቋድሰን አዳራችን ከፍቅር መንደር ደሴ ልናደርግ ነው” የሚል ፖስተው አየሁዋቸው።

በዚህ ተገርሜ ሳልጨርስ ቲቪው ስከፍተው “አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉና ዶክተር ደብረፅየን በ 7 ቢልየን ብር ለሚገነባው የተቀናጀ የጋራ ልማት ኮሪደር መሰረተ ድንጋይ አስቀመጡ” የሚል ዜና ሰማሁ።

በቲቪው የማየው ነገር ልቤን በሃሴት ሞላው “የሁለቱም መሪዎች ፈገግታ ሌላ ነገር ነው፣ ገዱ አዉርስ ሲጨፍር የተምቤን ሰዉን ያስንቃል፣ ደብረፅየን ጎጃምኛው ሲያስነካው ይሁኔን ያስከነዳል።

ዜናው ቀጠለ “ሁለቱም ህዝቦች የልማት ቀጠና እንጂ የጦርነት ቀጠና እንዲፈጠር በፍፁም እንደማይፈቅዱ ገልፀዋል፤

ይህ ለ 80 ሺ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥረው ፕሮጀክት ትንሹና የመጀመርያ የጋራ ፕሮጀክት እንደሆነ ለማወቅ ተችልዋል።” ይላል::

በዚህ ሰዓት ነብስያየ ተመንጥቃ ሰማይ ነክታለች። በህልሜ ዉስጥ ሆኜም ሌላ ህልም ዉስጥ ያለሁ መሰለኝ።

በፅንፈኝነት የምናዉቃቸው የሁለቱም ፌስቡከሮች ዜናዉን እየደጋገሙ ዘገቡት። ይህንን ተከትሎ በሁለቱም ክልሎች የድጋፍ ሰልፍና ፍንጠዝያ ሆነ።

አብርሃም ገብረመድህን እና ራሄል ሃይለ በባህርዳር ያዘጋጁት ኮንሰርት ጎጃምን በፍቅር አጋላት፣ ይደገም ይደገም ብቻ ሆነ።

ይሁኔ በላይናና አቢ ላቀው በመቐለ ያዘጋጁት ኮንሰርት መቐለን ክንድዋ እስኪዝል አስጨፈራት፣ ዘለለች አበደች፣ እዚህም ይደገም ይደገም እየተባለ እንደ ባህርዳሩ ሌሊቱ ነጋ።

በዚህ ሁሉ ነገር ተገርሜ፣ ህልሜ ካልዲስ ካፌ ቦሌ ወሰደኝና ጋዜጣ አዟሪው ዓብደላ የሆነ ጋዜጣ አቀበለኝ። ፊት ለፊት ገፁ ላይ “የትግራይና የአማራ ባለሃብቶች የጋራ የምክክር ፎረም መሰረቱ” ይላል።

ከዉስጥ ዘልቄ ሳየዉም ሌላ መልካም ነገር ገጠመኝ “ከሁለቱ ክልሎች የተዉጣጡ ሙሁራን የኢትዮጵያ ብልፅግና ዩኒቨርሲቲ የተባለ በልማትና በጋራ ሰላም የሚያተኩር ዩኒቨርሲቲ መስርተው በሚቀጥለው ሳምንት በሽረና በ ደብረብርሃን የመስረተ ድንጋይ ያስቀምጣሉ” ይላል።

በዚች ቅፅበት የተሰማኝ ሀሴት የምገልፅበት ቃል የለኝም። ምሳ ሰዓት ደርሶ ከባልደረቦቼ ጋር ጋር ስታፍ ላዉንጅ ገባን።

የሰዉ ሁሉ ፊት የፈካ፣ የደመቀ በተስፋ የተሞላ ብቻ ነው።

ያ ትልቁ ቲቪ የሰባት ሰዓት ዜና እያሰማ ነው። “የፌዴራል መንግስት የትግራይና የአማራ ህዝብና መንግስት ግንኙነት ሰንዶ ለዓለም ማስተማርያ ይሆን ዘንድ እየሰራ መሆኑ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ” ይላል።

በክልላዊ ዜናችን በሚል ስር ደግሞ “ትላንት በቢሾፍቱ በተደረገው ዉይይት ኦቦ ዳዉድ ኢብሳና ኦቦ ለማ መገርሳ የኦሮምያን ወጣቶች የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፈጠና ክህሎት ላይ የሚያተኩር ስምምነት ፈፀሙ” ይላል።

በዝርዝር ሀተታውም “በክልሉ የሚገኙ አስር ዞኖች ላይ የመጀመርያ ዙር ተግባራዊ የሚደረግ ይህ ፕሮጀክት 1.3 ሚልየን ወጣቶች የእዉቀት፣ የክህሎትና የስራ ፈጠራ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመስጠት እንደሚያስችል በጥናት ተረጋግጧል።” ይላል።

አሁን አገሬ ገነት መሰለችኝ። በየጣብያው ከየክልሉ ከየቦታው የምሰማው ወሬ የልማት፣ የትብብር፣ የአብሮ ማደግ፣ የስራ ፈጠራ፣ የሰላም ብቻ ሆነ። ሰው እንዴት ከዚህ ህልም ይነቃል? አላሳዝንም?

ስነቃ

ህልሜ በቀን የምመኛቸዉን ነገሮች አሳየኝ፤ ፍሮይድ ህልም ተፈፃሚ ያልሆኑ የቀን ምኞቶች ናቸው ይላል።

በኔ አረዳድ ሰላም፣ ልማት፣ እድገት፣ ዴሞክራሲ ህልም ሆነው የሚቀሩ ነገሮች አይደሉም።

በጎ ህሊና ካለ፣ ህዝብን ማእከል አድርጎ አመራር የሚሰጥ ካለ፣ ከግዝያዊ ስሜት ልቆ ለነገው ትዉልድ ስልጡንና የበለፀገች አገር ማስረከብ የሚመኝ አይምሮ በህልሜ የታዩኝ ነገሮች በጥረት ማሳካት ይችላል።

ትንሽ መነጋገር ጠፍቶ ትላልቅ ስህተቶች ሲፈፀሙ አይተናል፣ በትንሽ መነጋገር ትላልቅ ቁምነገሮች ሲሰሩም አይተናል።

እናማ ወንድም እህቶቼ አይደለም ኢትዮጵያዉያን መላው አፍሪካ ችግሩ ተመሳሳይ ነው፤ ድህነት፣ ኃላቀርነት፣ ሁከት፣ አስቸጋሪና አጭር ሂወት ነው።

የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞና የጋምቢያ ገበሬዎች ጭንቃቸው በዋናነት ምርታማነት፣ ገበያና የሚያደምጣቸው አስተዳደር ነው።

ባህርዳርና መቐለ ያለው ነጋዴም፣ ሙሁሩም፣ ስራ አጡም ችግራቸው ተመሳሳይ ናቸው።

እናማ ከነገ ወድያ የሚቆጨን ነገር ዛሬ አናድርግ፣ የፉክክር ነጥቦቻችን ገልብጠን የትብብር ማእከላት እናድርጋቸው፣ መሞትም መግደልም የሚጠየፍ ትዉልድ እንገንባ፣ ህልማችንን ዳግም እንቃኘው።

ጥቂት በጥባጮችን ሳይሆን ዝምታን የመረጠው ሰፊው ህዝብ እናንቃው። የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሙሁራን፣ ነጋዴዎች፣ ተማሪዎች ከፍ ላለ ህልም እንጣር።

የመንግስት ስልጣን ይዘው ቁማር ዉስጥ የገቡትንም አደብ ግዙ እንበላቸው። መንግስት ማለት ምን ምን መስራት እንደሆነ እየደጋገምን እንንገራቸው።

በሰላም ወጥቶ መግባት መብታችን እንደሆነና መንግስትም ይህን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት እናስታዉሰው።

በምቾት ቀጠና ሆነው፣ የማይለበልባቸው እሳት የሚጭሩ ብልጣ ብልጦችን አንስማ። ፍላጎትህ በታላቅ ህልም፣ በጋራ ጥረት እና በመልካም ልቦና እንጂ በግጭት እንደማይሳካ ተገንዘብ።

የምንሰማዉን ሳይሆን በሚዛናዊ አይምሮ የምንደርስበትን ዉሳኔ እንመን።

የወንድምህን ሂወት ላንት ተጨማሪ ሂወት ነው። ጥላቻን እንጠየፍ፣ ጥላቻዉን ስንጠየፍ ግን በሌላ ጥላቻ አለመዘፈቃችን እርግጠኛ እንሁን።

በኛ ፀብ የሚሸፈን የመንግስት ድክመት እንዳይኖር እንጠንቀቅ። በህልሜ መጨረሻ የሰማሁትን ነግርያቹህ ልሰናበት

“ኢትዮጵያ በቅርቡ ያቋቋመችው የሰላም ሚኒስቴር በሃገሪቱ በሰፈነው ዘላቂ ሰላም ምክንያት ሚኒስቴር መስርያ ቤቱ ከዛሬ ጀምሮ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር በመሆን ለደቡብ ሱዳን፣ ለሱማልያ፣ ለኮንጎና ሰላም ለተጠሙ ህዝቦች ስላም አምጪ ዳይሬክቶሬት ሆኖ እንደ አዲስ ተዋቅሯል”

የምኖረው ህልሜን እዉን ለማድረግ ነው!!!

ወንድማቹህ ናሁሰናይ በላይ

ከተመቻቹህ ሼር አድርጉት”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here