ሲም ካርድ

ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

ብዙጊዜ ሕይወታችን ሙት የሚሆነው በነገሮች ውድ መሆን ሳይሆን፣ ርካሽ ነገሮችን በሚገባ ለመጠቀም ባለመቻላችን ነው።

አንድ ጓደኛዬ ቢሮ መጣ፡፡ በመንገዱ መጨናነቅ ምክንያት አርፍዷል፡፡ ስልክ ስላልነበረው መንገድ ላይ ለመደወል አልቻለም፡፡

የተቀጣጠርነው በወንድሙ ስልክ ነው፡፡ ቢሮ ሲደርስ ደግሞ አሣንሰሩ አይሠራም፡፡ በእግሩ ነው አምስት ፎቅ የወጣው፡፡ ቢሮ ደረሰና ‹እፎይ› ብሎ ወንበሩ ላይ ተዘረጋ፡፡ ስልኩ ከኪሱ ወደቀ፡፡

‹ይህን የመሰለ ስልክ እያለህ ነው የማትደውለው?› አልኩት፡፡

‹ምን ዋጋ አለው፡፡ ሲም ካርድ ከሌለው› አለኝ፡፡

የያዘው ስልክ በኢትዮጵያ ብር ከ30 ሺ ብር በላይ ያወጣል፡፡ የ15 ብር ሲም ካርድ አጥቶ ነው መከራ የሚያየው፡፡

‹ሲም ካርድ ለምን አላወጣህም?› አልኩት፡፡

‹ሁለት ቦታ ሄጄ የለንም አሉኝ፡፡ ቴሌ ስሄድ ደግሞ የፓስፖርት
ፎቶ ኮፒ ጠየቁኝ፤ መብራት ስለሌለ ፎቶ ኮፒ አይሠራም› አለኝ፡፡

የ30 ሺ ብር ስልክ የ15 ብር ሲም ካርድ አጥታ በድን ሆነች፡፡

ስልክ ምን ውድ ዋጋ ቢያወጣ ሲም ካርድ ከሌለው ለካስ ሕይወት አይኖረውም፡፡

ሲም ካርድ (subscriber identification module) ዋጋዋ በጣም ትንሽ ነው፡፡

ለትልቁ ስልክ ሕይወት የምትሰጠው ግን እርሷ ናት፡፡ ሲም ካርድ የሌለው ስልክ ካሜራ ይሆናል እንጂ ስልክ አይሆንም፡፡

በሕይወታችንም ውስጥ እንዲሁ ነው፡፡ ለሕይወት ጣዕም የሚሰጧት ነገሮች በጣም ርካሾች ናቸው፡፡

ውዱን ሕይወት ጣዕም የሚሰጡት እንደ ሲም ካርድ ጠቃሚ ግን ርካሽ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡

ለአምስት ደቂቃ መጸለይ አምስት ደቂቃ በስልክ ከማውራት ይልቅ በጣም ርካሽ ነው፡፡

ግን ውሏችንን ጣዕም እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡

አምስት ሰዓት ከጓደኞቻችን ጋር አምሽተን ብንመጣ ከምናወጣው ወጭ አንጻር አንድ ሰዓት ከትዳር አጋራችንና ከልጆቻችን ጋር ማሳለፍ እጅግ ርካሽ ነው፡፡

ቢበዛ ቡናና ፈንድሻ ቢጠይቀን ነው፡፡ ነገር ግን ትዳራችን ጣዕም እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡

በሥራችን መካከል ለአምስት ደቂቃ ያህል ተነሥተን ብንንቀሳቀስ በሰውነታችን የደም ዝውውርና በአካላችን መፍታታት ላይ የሚያመጣው ውጤት ተአምራዊ ነው፡፡

በታክሲ ወይም በአውቶቡስ ስንጓዝ ፌስቡክ ከምንጎረጉር ይልቅ መጽሐፍ ብናነብ በጣም ርካሽ ነው፡፡

በገንዘብ የማይገዛውን አእምሯችንን ሕይወት እንዲኖረው እናደርግበታለን፡፡

ለደቂቃ ረጋ ብሎ መመሪያዎችን ማንበብ በጣም ቀላል ነገር ነው፤ ነገር ግን ውድ የሆነውን ሕይወት ለአደጋ ከመጣል ይታደገናል፡፡

ጾም ርካሽ ነው፡፡ ምን ወጭ የሌለው፡፡ ምግብ ከጾም ይልቅ ውድ ነው፡፡

ኪስ ይነካል፤ ጤናንም ያናጋል፡፡ ርካሽ የሆነውን ጾም በመጾም ውድ ለሆነው ጤናም ሆነ ክቡር ለሆነው የዘላለም ሕይወት መብቃት ግን ይቻላል፡፡

ብዙ ጊዜ ሕይወታችን ሙት የሚሆነው በነገሮች ውድ መሆን አይደለም፡፡ ርካሽ ነገሮችን በሚገባ ለመጠቀም ባለመቻላችን እንጂ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here