“ነገር ሁሉ ለበጎ ነው! ”

እመኑኝ ይሄን ጽሑፍ ካነበባችሁ በኋላ የሆነ ስሜት ይሰማችኋል።

በአንድ ወቅት አንድ አባት ከነበሩበት ቦታ ወደ በረሃ መሰደድ ግድ ሆነባቸው። ከመጽሐፋቸው ሌላ ሦስት ነገሮች ነበሯቸው።

እነሱም፦ መጽሐፉን በጨለማ ወቅት ለማንበብ የሚጠቅማቸው ቀንዲል (ኩራዝ)፣ ጎህ ከመቅደዱ በፊት ከእንቅልፍ የሚቀሰቅሳቸው አንድ አውራ ዶሮ እና ለመጓጓዣነት የሚገለገሉበት አንድ አህያ ነበሩ።

አንድ ቀን ምሽት ከጉዞ የተነሣ በጣም ስለ ደከሙ እኚህ አባት ወደ አንድ መንደር ቀርበው ማደሪያ ቢጠይቁም መንደርተኛው ፈቃደኛ ባለመሆኑ ማንም አልፈቀደላቸውም።

ስለዚህም ከመንደሩ አቅራቢያ አንድ ጉድጓድ ያገኙና በዚያ ውስጥ ገብቶ ለማደር በመወሰን ገብተው አደሩ።

እንደ ወትሮው መጽሐፋቸውን ለማንበብ ቀንዲላቸውን ቢለኩሱትም የነበረው ብርቱ ነፋስ አጠፋባቸው።

ለመተኛት ጋደም እንዳሉ ተኩላ መጥቶ አውራ ዶሮዋቸውን፣ አንበሳም አህያቸውን በሉባቸው።

የተደራረበ ጉዳት ስለደረሰባቸው ሽማግሌው እርዳታን በመሻት ወደዚያ መንደር ቢመለሱ ዘራፊ ሽፍታዎች የመንደሩን ነዋሪዎች በሙሉ ገድለው ንብረት ዘርፈው ባዶ መንደር ሆኖ አገኙት።

ሽማግሌው ይህን ሁሉ ባጤኑ ጊዜ ፈጣሪ ምን ያህል መልካም ነገርን እንዳሰበላቸው አስተዋሉ።

በዚያች ምሽት በመንደርተኞቹ በአንዱ ቤት ቢያድሩ ኖሮ የዘራፊዎች ሰለባ ሆነው ሊገደሉ በቻሉ ነበር።

ቀንዲላቸውንም ነፋስ ባያጠፋው የብርሃኑ ወጋገን እዚህ ጋር ሰው አለ በማለት ለሽፍታዎቹ ያሳብቅ ነበር።

አውራ ዶሮአቸውና አህያቸውም ባይበሉ ኖሮ ከሽፍታዎቹ ተደብቀው ማደር ባልቻሉ ነበር።” እግዚአብሔር ከክፉ ነገሮች ውስጥ መልካም ነገር ማውጣት የሚችል አምላክ ነው።”

ስለዚህ እንዲህ በሉ፦ “የሚደርስብኝ ችግር፤ የሚገጥመኝ ፈተናና መከራ ሁሉ አምላኬ ሆይ ለበጎ ታደርግልኛለህና አመሰግንሐለሁ” አሜን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here