ሲያምኑ እንደ አብርሃም ነው፣ ሲሠሩ እንደ ላሊበላ፡፡ ሲያስተምሩ እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፣ ሲተጉ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ፤ ከቆረጡ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው፣ ከሞገቱ እንደ ሳዊሮስ፡፡
ከመረቁ የሚጠቅሙትን ያህል ከረገሙም ይጎዳሉ፤ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ከሆነባቸው ክብር፣ ፕሮቶኮል፣ ስምና ዝና አይገድባቸውም፡፡ ከቀበሌ እስከ ቤተ መንግሥት ይሞግታሉ፤ በፍትሕ አደባባይ መፍትሔ ካጡ ‹ይግባኝ ለክርስቶስ‹ ብለው ለሰማያዊው ፍርድ ቤት ያቀርባሉ፡፡
አረጋዊ ናቸው፣ ግን እንደ ወጣት ይሠራሉ፤ ሊቀ ጳጳስ ናቸው ነገር ግን እንደ ሰንበት ተማሪ ይሮጣሉ፣ የአንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፣ ግን በሁሉም ይወደዳሉ፤ ትምህርታቸው ከሰው ልብ ዕንባቸው መንበረ ጸባዖት ይደርሳል፡፡ በርሳቸው ዘንድ ትንሽ የለም፣ ትልቅም የለም፡፡
የርሳቸውን ስም የያዘው ቅዱስ የዛሬ 700 ዓመት እንዲሁ እንደርሳቸው ነበር፡፡ ቅዱሱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሲሆን ያስተምራል፣ ገዳማትን ይተክላል፣ ደቀ መዛሙርትን ያፈራል፣ ነገሥታትን ይገሥጻል፣ ለእምነቱ ጥብቅና ይቆማል፣ ግፍንና በደልን ይጸየፋል፡፡ ቅዱስ ቀውስጦስ ዘመሐግል፡፡
በሰማዕትነትም ያረፈው ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ከክርስትናው ወጥቶ ሁለት ሚስት አግብቶ፣ የተቃወሙትን ቅዱሳን በግፍ ባሳደደ ጊዜ ነው፡፡ በንጉሡ ፊት እውነቱን ተናግሮ፣ ስሕተቱን ገልጦ በተናገረ ጊዜ ከቤተ መንግሥቱ አውጥተው በጨለማ ቤት አሠሩት፣ በኋላም ከጨለማው እሥር ቤት አውጥተው ዛሬ በሰሜን ሸዋ እንሣሮ በሚባለው ቦታ ወስደው በግፍ ገደሉት፡፡ እርሳቸውም ስሙን ብቻ ሳይሆን ግብሩንም ወርሰውታል፡፡

ከዐሥራ አምስት ዓመታት በፊት፡፡ ትጉኁ ብጹዕ አቡነ ናትናኤል፣ መዶሻው ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ሐዋርያዊው ብጹዕ አቡነ ኤልያስ አንድ ሆነው ወደ ሐረር ዘምተው ነበር፡፡ መልአከ ሰላም ኃይለ ኢየሱስም አጅበዋል፡፡ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤልና የታእካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራንም ሐረር ከትመዋል፡፡ ቀሲስ ደጀኔ ሊቀ መዘምራን ኪነ ጥበብ ተከትለዋል፡፡

እኔም እድል ገጥሞኝ በቦታው ነበርኩ፡፡ ተሐድሶ ሐረርጌን ከምዕራብ በአስበ ተፈሪ፣ ከምሥራቅ በሐረር በኩል ሠንጎ ይዟታል፡፡ አቡነ ቀውስጦስ የሐረር ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ እርሳቸው እቴ በሃይማኖት ድርድር አያውቁም፣ ግዴለሽነት አያጠቃቸውም፣ ኖላዊነታቸውን ለአፍታም አይዘነጉት፡፡

በረከታቸው ይደርብንና አቡነ ናትናኤል ‹የሐረርጌ መሬት› በሚል ርእስ ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ ሰምቼው የማላውቅ ድንቅ ትምህርት አስተማሩ፤ ‹የሐረርጌን መሬት ጠይቁት፤ ይመስክር፤ እስኪ ቆፍሩና ጠይቁት፣ ካህኑ ታቦቱን እንደያዘ ዐጽሙን ታገኙታላችሁ፤ መሬቱኮ ክርስቲያን ነው፡፡ አባቶቻችን የተጋደሉበት ነው› አሉ ትጉኁ አቡነ ናትናኤል፡፡

መዶሻው ቄርሎስም ‹ምንጊዜም አዲስ የሆነው እምነታችን ምኑ ይታደሳል? ማንስ ችሎ ያድሰዋል?› የተሰኘውን ትምህርት አወረዱት፡፡ መዝሙርን ከትምህርት የሚያስተጋብሩት አቡነ ኤልያስም በረከታቸው ይደርብንና፡-
መጀመሪያ
ኢኮነ ነግደ ወፈላሴ
ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን አትዮጵያ
ሀገሪቶሙ ለቅዱሳን ምድረ ሐረርጌ
የተሰኘውን መዝሙር፣ ቀጥለውም
አደሬ ጢቆ ሥላሴ
እኔ እወድሻለሁ እስኪወጣ ነፍሴ
የተሰኘውን መዝሙር አሸበሸቡት፡፡
ቅዱስ ያሬድን በአካል ያላየን ሰዎች አቡነ ኤልያስን አይተናልና አይቆጨንም፤ ሕዝቡ ያለበትን ቦታ እስኪረሳ ድረስ፣ ከምድር ክንድ ስንዝር ከፍ ያለ እስኪመስል ድረስ አብሯቸው ዘመረ፡፡ ይሄኔ አቡነ ቀውስጦስ መልአኩ ከመንበሩ ተነሡ፡፡
ከቤተ ክርስቲያን በላይ ምን ክብር አለ፣ ከሃይማኖትም በላይ ምን ታላቅነት አለ፣ ከክርስቶስም በላይ ምን ፕሮቶኮል አለ፡፡ መስቀላቸውን ይዘው በዚያ እንደ መላእክት በተመስጦ በተነጠቀው የሐረር ሕዝብ መካከል እያሸበሸቡ ገቡ፡፡
ሕዝቡ ምድሪቱን ለቀቀ፡፡ ሄደ ወደ አርያም፤ የታእካ ነገሥትና የቅዱስ ዑራኤል ሰንበት ተማሪዎች እንደ ቅዱስ ያሬድ እግራቸውን ቢወጉት እንኳን አይሰሙም ነበር፡፡ አቡነ ቄርሎስና አቡነ ኤልያስ ያለቅሳሉ፡፡ አቡነ ናትናኤል ምድር ላይ የሉም፡፡ መልአከ ሰላም ኃይለ ኢየሱስ መድረክ ላይ መሆናቸው ረስተውታል፤ እያሸበሸቡ ከሕዝቡ ጋር ሄደዋል፡፡ መላእክት በዲበ ምድር፡፡
እንደ አባ ቀውስጦስ የዘመረ፣ እንደ እርሳቸውም ያሸበሸበ፣ እንደ እርሳቸውም ለሰማያዊ ክብር ሲል ምድራዊውን ክብር የዘነጋ፣ እንደ እርሳቸውም በሃይማኖት ይህንን ያህል የሚደሰት፣ እንደ እርሳቸውም ኑፋቄን የሚጸየፍ፣ እንደ እርሳቸውም ለወንጌል የሚተጋ ከዚያም ወዲህ አላየሁም፡፡
እኒህን አባት የሚያውቅ ሰው ታላቅ ሰው ነው፡፡ የሚንቅ ደግሞ ራሱን የናቀ፡፡ እንደ ጻድቁ ቀውስጦስ የሚያምኑ ብቻ አይደሉም፡፡ እንደ መልአኩ ቀውስጦስ የሚቀስፉም ናቸው፡፡ ዕንባቸው ከባድ ነው፣ ጸሎታቸው ሥሙር፣ ቃላቸው ሰይፍ ነው፣ መሐላቸው ክቡር፤ ከጀመሩ ሳይጨርሱ፣ ካነሱ ሳያደርሱ፣ ከጨበጡ ሳያጠብቁ፣ ከወረወሩ ሳያርቁ አይመለሱም፡፡

በለገ ጣፎ ከተማ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ተሠራ፡፡ ሰውን የማያፍሩ ፈጣሪን የማይፈሩ ባለ ሥልጣናት ተነሡና አፈራረሱት፡፤ ንዋያተ ቅድሳቱንም ወረወሩ፡፡ አላወቁትም እንጂ በጉዳዩ ላይ ሁለት ቆራጦች ተሰልፈውበት ነበር፡፡

በሰማይ ሄሮድስን ያልፈራው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ፣ በምድር ‹ይድረስ ለክርስቶስ› ብለው የሚሞግቱት ቆራጡ አቡነ ቀውስጦስ፡፡ በእነዚህ በሁለቱ እጅ የተያዘ ጉዳይ በስተመጨረሻው በለማ መሬት ላይ መውደቁ አይቀሬ ነበረና፡፡ በለማው ለማ እጅ ወደቀ፡፡
እነሆ እንደ እከ የማይተኙት፣ ላይጨርሱ የማይጀምሩት፣ ላያጸኑ የማይገነቡት አቡነ ቀውስጦስ በትምህርትም፣ በሙግትም፣ በጸሎትም፣ በጥብዐትም፣ በዕንባም ታግለው ለፍሬ አደረሱት፡፡

አባታችን፣
‹ረድኤቴ ከወዴት ይመጣልኛል?› እያለ ምእመናኑ በተሥፋ ሰማዩን በሚያይበት በዚህ ዘመን፣ እንዲህ እንደርስዎ የልብ መጠጊያ የሚሆን አባት ማግኘት መታደልም፣ መመረጥም ነው፡፡

እንዲ ቤተ ክህነታችን በሙስና፣ በዘረኛነት፣ በአስተዳደር ልምሾ ናውዞ ምእመናኑ የመከራ ወሬ በሚሰሙበት ዘመን፣ እንደ እርስዎ ተአምር የሚነግር አባት ማግኘት በበረሓ እንደተገኘ ምንጭ ነው፡፡
እንኳን በዓይን አየንዎት፤ እንኳን በታሪክ አልሰማንዎት፡፡ ለልጆቻችን የምንተርከው ታሪክ ሰጥተውናል፡፡ የአባቶቻችን አምላክ ዛሬም ከእኛ ጋራ መሆኑን የሰማነውን አሳይተውናል፡፡

ኑሩልን አባታችን፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here