በሀዋሳ ከተማ አሮጌ ገበያ ሰሞኑን በተከሰተ የእሳት ቃጠሎ ወቅት እንደተዘረፉ የጠረጠራቸውን የተለያዩ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን በሲዳማ ዞን የቦርቻ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

ከንብረቶቹ በተጨማሪ 19 ተጠርጣሪዎችን ጭነው ያጓጉዙ የነበሩ አንድ አይሱዙ የጭነት መኪናና ሁለት ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

በሲዳማ ዞን የቦርቻ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አዛዥ ዋና ሳጅን አለማየሁ አሰፋ እንደገለፁት ፥ ዕቃዎቹ የተያዙት በሃዋሳ ከተማ አሮጌው ገበያ ባለፈው ማክሰኞ የእሳት ቃጠሎ በተነሳበት ወቅት ተዘርፈው ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ነው።

በጥርጣሬ ንብረቶቹን በወረዳው ለማስተላለፍ ሲሞከር ንብረቶቹን ከተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከሃዋሳ ከተማ ተነስተው መድረሻቸውን ሶዶ ከተማ ያደረጉት ተጠርጣሪዎች ላሌ እና ይርባ በሚባሉ ቦታዎች ላይ በተደረገ ድንገተኛ የኬላ ፍተሻ ከነዕቃው መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

ዋና ሳጅን አለማየሁ እንዳሉት፥ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ዕቃዎች መካከል ጫማዎች፣ ሞባይል ስልኮች፣ የተለያዩ የወንድና የሴት ልብሶች፣ የሞተር ሳይክል መለዋወጫዎችና ጌጣጌጦች ይገኙበታል፡፡

በተሽከርካሪዎቹ ሲጓጓዝ የነበረው ዕቃ የተለያየ መሆኑ፣ የተያዙት ግለሰቦች ለንብረቱ የተገዛበትን ደረሰኝ አለማቅረባቸው፣ ከየት እንደገዙና የንብረቱን ባለቤት መናገር አለመቻላቸው ጥርጣሬያቸውን ይበልጥ እንዳሳደገው ተናግረዋል።

በወረዳው ፖሊስ የተያዘው ዕቃ የተዘረፈ ስለመሆኑ እርግጠኛ ባይኮንም፥ሰሞኑን የሃዋሳ ከተማ አሮጌ ገበያ ከደረሰው ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ቅኝትና ክትትል ሲያደርግ ዕቃዎቹን በጥርጣሬ መያዙንም ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዎች የዕቃዎቹን ባለቤትነት የሚያሳይ መረጃ እንዲያቀርቡ በማድረግ ጭምር ፖሊስ ምርመራ እያከናወነ ሲሆን ምርመራው እንዳለቀ ውጤቱን ለህዝብ እንደሚገለጽ አመልክተዋል፡፡

ምንጭ ፦ ኢዜአ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here