ኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበራቸውን ለዜጎቻቸው ክፍት ካደረጉበት መስከረም 2011 ዓ.ም. የመጀመሪያ ሳምንታት ጀምሮ ባሉት ቀናት፣ 15 ሺሕ ኤርትራውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ተጠቆመ፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ አብዛኞቹ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ለመቆየት፣ ሌሎች ደግሞ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅና  ለግብይት ሲሉ ድንበር ማቋረጣቸውን አስረድቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በየቀኑ 500 ኤርትራውያን የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው እንደሚገቡም ገልጿል፡፡

የኤርትራውያኑ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ የስደተኞቹ ቁጥር 175 ሺሕ መድረሱን አመልክቷል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ሪፖርት አኃዙ ከዚህ በላይ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁሞ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኤርትራውያን ቁጥርም በዚሁ መጠን እየጨመረ እንደሚሄድ ገልጿል፡፡

በተያያዘ ዜና የሁለቱ አገሮች ድንበር ከተከፈተ በኋላ፣ በድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ከተሞች መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ከአካባቢው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

ከኢትዮጵያ በኩል እንደ ሲሚንቶ፣ ብሎኬት፣ በርበሬ፣ ጤፍና የመሳሰሉት ወደ ኤርትራ እየተላኩ ሲሆን፣ ከኤርትራ በኩል ደግሞ አልባሳትና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እየተሸጡ ነው፡፡ ከንግዱ ጋር በተያያዘም አንዱ ናቅፋ በ1 ብር ከ40 ሳንቲም እየተመነዘረ ነው፡፡

ከኤርትራ የሚመጡ ነጋዴዎች በዋጋ አዋጭነቱ ምክንያት ነዳጅ ከኢትዮጵያ ገዝተው እንደሚሄዱም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሁለቱ አገሮች በተጀመረው አዲሱ ግንኙነት መሠረት ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች የመጠቀም ሐሳብ ያላት ሲሆን፣

በቅርቡ በተከፈተ አንድ ዓለም አቀፍ የማዳበሪያ ግዥ ጨረታ አሸናፊ አቅራቢዎች የምፅዋን ወደብ እንደ አማራጭ እንዲጠቀሙ ከመንግሥት ተነግሯቸዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here