የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል የሆነው የ #ትራንስኔሽንኤርዌይስ ንብረት የሆነ ሄሊኮፕተር ሚያዚያ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ባጋጠመው ችግር ሳቢያ በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ በወደቀበት ወቅት በሥፍራው የነበሩ የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶች የአደጋው ሰለባ ሆነው ነበር፡፡

ከዚህም አንጻር የትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ(TNA) በሄሊኮፕተሩ መውደቅ ምክንያት መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸውን መኖሪያ ቤቶች ለባለቤቶቹ የጥገና ሥራ አከናውኗል፡፡ ሙሉ በሙሉ የፈረሰውን የአቶ ጥላሁን ወንድማገኘሁ መኖሪያ ቤት ደግሞ በአዲስ መልክ በብር 496,568 ገንብቶላቸዋል፡፡ እንዲሁም ግለሰቡ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የሚጠቀሙበትን ቁሳቁሶችም በብር 82,272 ገዝቶላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከቤቱ ጋር በተያያዘ ብር 578,840 ወጪ ተደርጓል፡፡

ኩባንያው በአዲስ መልክ ገንብቶ የሠራው መኖሪያ ቤት ከነሙሉ ቁሳቁሱ የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ዛሬ ጰጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. የቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 ዋና ስራ አስፍፃሚ አቶ ዲሮ ደሜ የአካባቢ መስተዳድር ኃላፊዎችና በአካባቢው የሚኖሩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

አዲስ የተሠራውን መኖሪያ ቤት ቁልፍ ለቤቱ ባለቤት ለአቶ ጥላሁን ወንድማገኘሁ ያስረከቡት ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ ለአቶ ጥላሁን ወንድማገኘሁ ካደረገው የአዲስ ቤት ግንባታና መኖሪያ ቤት ቁሳቁስ ግዥ ወጪ ሌላም በፈረሰው ቤት ውስጥ ለተዝካርና ጾም ፍቺ ለነበሩ ዝግጅቶች ወጪ ተደርጎ ነበር የተባለውን የገንዘብ ወጪ ብር 34,100 ኩባንያው ተክቶላቸዋል፡፡ እንዲሁም በአካባቢው ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን በዓል መዋያ የሚሆን ሰንጋ ግዥ ብር 22,500 ወጪ አድርጓል፡፡

ትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ በሄሊኮፕተሩ ሳቢያ መኖሪያ ቤት በመፍረሱ በቤተሰብ ላይ ተከስቶ የነበረውን ችግር ከፍ ሲል በተገለጸው መሠረት ያስወገደ ሲሆን ከተገነባው አዲስ መኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ ኩባንያው ያወጣቸው የገንዘብ ወጪዎች በሄሊኮፕተሩ ላይ ለደረሰው አደጋ ኢንሹራንስ ድርጅት ለኩባንያው ከሚከፍለው ክፍያ ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑ ታውቋል፡፡

ይህ ተግባር በልዩ ፈቃድ የተደረገ የበጎ አድራጐት ሲሆን ቀደም ሲል ኩባንያው ኢንሹራንስ የገባ በመሆኑ በፓሊሲው መሠረት ጉዳት ለደረሰባቸው ቤቶች እና ንብረቶች እንዲሁም ከጥቅም ወጪ ለሆነው ሄሊኮፕተር ክፍያው በቅርብ ጊዜ በኢንሹራንስ ኩባንያው በኩል የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል፡፡

የትራንስ ኔሽን ኤርዌይስ ሄሊኮፕተር በገጠመው ችግር ሳቢያ በወደቀበት ጊዜ በውስጡ የነበሩ ሁለት አብራሪዎች እና አምስት ተሳፋሪዎች እንዲሁም በወደቀበት ቤት ላይ ምንም በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት እንዳልነበረ ይታወሳል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here