የኢትዮጵያ ባለሀብቶች በፋይናንስ እጥረት የውጭ አጋሮችን ለመጠበቅ ተገደዋል

ዋና መሥሪያ ቤቱን በናይጄሪያ ሌጎስ ያደረገውና፣ በየዓመቱ የየአገሮችን የሆቴል፣ የቱሪዝምና የመዝናኛ አገልግሎቶችን በተመለከተ ሪፖርት የሚያዘጋጀው፣ ደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ፣ በዘንድሮው ሪፖርቱ ኢትዮጵያን በሆቴሎች ግንባታና ኢንቨስትመንት ከአሥር ዋና ዋና አፍሪካ አገሮች ውስጥ ሦስተኛዋ እንደሆነች ይፋ አደረገ፡፡

በሆቴልና ቱሪዝም መስክ በማማከር ሥራ የሚታወቀው ደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 በአፍሪካ በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙና ስምምነት ተደርጎባቸው ወደ ግንባታ እንደሚገቡ የሚታሰቡ ሆቴሎችን ከክፍሎቻቸው ብዛት ጋር በማነፃፀር ባቀረበው ትንታኔ መሠረት ኢትዮጵያ በ31 ሆቴሎችና በ5,717 ክፍሎች ብዛት ከአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡

በአንፃሩ ግብፅና ናይጄሪያ ቀዳሚዎቹን ተርታዎች ተቆናጠዋል፡፡ ግብፅ በ43 ሆቴሎችና በ13,636 ክፍሎች ብዛት ቀዳሚ ስትሆን፣ ናይጄሪያ በበኩሏ በ57 ሆቴሎችና በ9,603 ክፍሎች ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ የሆቴል ፕሮጀክት የተስፋፋባት አገር ተብላለች፡፡

ምንም እንኳ ናይጄሪያ በሆቴል ብዛት ቀዳሚ ብትሆንም በክፍሎች ብዛት ከግብፅ ዝቅ ብላለች፡፡ ኢትዮጵያም ብትሆን በሆቴል ብዛት በሞሮኮ መበለጧ አልቀረም፡፡

ሞሮኮ 33 ሆቴሎች እየገነባች ወይም ለመገንባት እየተዘጋጀች ብትገኝም፣ የሆቴሎቿ ክፍሎች ብዛት ግን ከኢትዮጵያ ያነሱ ናቸው፡፡

በመሆኑም በአፍሪካ ደረጃ እየተካሄዱ ከሚገኙ የሆቴል ግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ በሁለት ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ ዕድገት በማሳየት ከፍተኛ የሚባል ለውጥ ማሳየቷን ሪፖርቱ ይተነትናል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2018 ብቻ 20 ሆቴሎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙና ለግንባታ መታቀዳቸው ተጠቁሟል፡፡

ይህ ሁሉ ግን የአገር ውስጥ ብራንዶችን ሳይጨምር ነው፡፡ በሪፖርቱ መሥፈርት መሠረት አገሮች የሚወዳደሩት፣ ከአንድ በላይ አገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ሆቴሎቻቸው ብዛትና ባላቸው የክፍሎች ብዛት ቢሆንም፣ ዓለም አቀፍ ስም ያላቸው የሆቴል ብራንዶች ግን ዋናዎቹ ተዋናዮች ናቸው፡፡

በአፍሪካ ከፍተኛ ተስፋፊ በመሆን ከሚጠቀሱት ግንባር ቀደም ሆኖ የተቀመጠውን ራዲሰን ብሉ ሆቴል እንደሆነ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡

በሆቴል ግንባታ ከሚጠቀሱ አሥር የአፍሪካ አገሮች

በዘንድሮው ሪፖርት ውስጥ 41 የዓለም አቀፍ ሆቴል አስተዳዳሪዎች መረጃዎችን በመስጠት እንደተሳተፉ ሲገለጽ፣ እነዚህ ኩባንያዎችም በመላው አፍሪካ 418 ሆቴሎችና ከ76 ሺሕ በላይ ክፍሎች ያሏቸው ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር ስምምነት የፈረሙ ስለመሆናቸው ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

አምስት የሰሜን አፍሪካና 49 ከሰሃራ በታች እንዲሁም የህንድ ውቅያኖስ ደሴቶችን ያካተተው ይህ ሪፖርት፣ በ2018 በአፍሪካ የ14 በመቶ የሆቴል ፕሮጀክቶች ዕድገት መመዝገቡን አስፍሯል፡፡

41 ኩባንያዎች በ41 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሆቴል ግንባታ ፕሮጀክቶች ስምምነት መፈራረማቸውም ታውቋል፡፡

ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ውስጥ 14 ሺሕ ክፍሎች ያሏቸው ሆቴሎች ወደ ፊት ወደ ገበያው እንደሚቀላቀሉ ሲጠበቅ፣ የአንበሳውን ድርሻ ከያዙት አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያና ኬንያ ይጠቀሳሉ፡፡

ኬንያ በ20 ሆቴሎችና በ3,444 ክፍሎች በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያን ትከተላለች፡፡ ታንዛንያም በ15 ሆቴሎች ግንባታ ሒደት ላይ እንደምትገኝ ተጠቅሷል፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከተፈራረመቻቸው 20 የሆቴል ግንባታ ፕሮጀክቶች አንፃር ዘንድሮ ወደ 31 ያሻቀበ ቁጥር በማስመዝገብ በአፍሪካ ከትልልቆቹ አገሮች ተርታ ስትመደብ፣ እንደ አኮር ሆቴሎችና ሒልተን ሆቴል ያሉት ብራንዶች የተፈራረሟቸው ስምምነቶች ለዚህ ተጠቃሾች ሆነዋል፡፡

ምንም እንኳ በርካታ የሆቴል ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ ብትሠለፍም፣ በአንፃሩ የሆቴሎቹ ባለንብረቶች በፋይናንስ እጥረት ፕሮጀክቶቻቸውን በሚፈለገው ደረጃ መገንባት እንዳልቻሉ እየተገለጸ ነው፡፡

የደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ትሬቨር ዋርድ፣ ስለዚሁ ጉዳይ ከሪፖርተር በኢሜይል ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ባለሀብቶቹ የሆቴል ግንባታ ሥራውን ቢጀምሩም ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የፋይናንስ እጥረት ሲገጥማቸው ይታያል፡፡ በአብዛኛው ወደ ግንባታ የሚገቡት ለሥራው የሚያስፈልገውን ወጪ እጅግ አሳንሰው ስለሚመለከቱት ነው፡፡

ከአገር ውስጥ ምንጮች ለግንባታ የሚያስፈልጋቸውን ያህል ገንዘብ ማግኘት ስለሚቸግራቸው የውጭ አገሮችን ይፈልጋሉ፤›› በማለት በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንቨስትመንት ሒደት ውስጥ ስለሚታየው ችግር ሚስተር ዋርድ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ይህም ሆኖ እንደ የአፍሪካ የንግድና የልማት ባንክ (በቀድሞ መጠሪያው ፒቲኤ ባንክ) ያሉ ተቋማት ለኢትዮጵያ ሆቴል ፕሮጀክቶች ብድር የመስጠት ፍላጎት እንዳላቸው ታይቷል፡፡

ባንኩ ከዚህ ቀደም አኮር ግሩፕ በኢትዮጵያ ለማስተዳደር ከእንይ ጄኔራል ቢዝነስ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ለሚገነባው የፑልማን ብራንድ ሆቴል ግንባታ ያውለው ዘንድ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብድር መፍቀዱን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት በአዲስ አበባ የተስተናገደውና በእንግሊዙ ኩባንያ ቤንች ኤቨንትስ አማካይነት በየዓመቱ የሚሰናዳው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ ዘንድሮ በኬንያ ሊካሄድ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

ይህ ኮንፈረንስ የዓለም የሆቴልና የቱሪዝም ተዋናዮች የሚገናኙበት ሲሆን፣ ኬንያ እ.ኤ.አ. ከኦክቶበር 2 እስከ 4 ቀን 2018 ለሦስተኛ ጊዜ እንደምታስተናግደው ታውቋል፡፡

ይህ ጉባዔ ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ዕድል አለው ወይ ተብለው የተጠቁት የቤንች ኤቨንትስ የሚዲያ ግንኙነት ኃላፊና የሆቴልና ቱሪዝም መስክ አማካሪው ዴቪድ ታርሽ፣ ጉባዔውን ለማስተናገድና ስፖንሰር ለማድረግ ከኢትዮጵያ ጥያቄ አለመቅረቡን፣ ኩባንያውም እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ አለማሰቡን ለሪፖርተር በኢሜይል ገልጸዋል፡፡

ቤንች ኤቨንትስ በሞሮኮ ተመሳሳይ የሆቴልና ቱሪዝም ኮንፈረንስ ጉባዔ ማዘጋጀት እንደጀመረም ይፋ አድርጓል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here