ምንም እንኳ የአካባቢው ሰዎች ጉዳት እያደረሰብን ነው ብለው ቅሬታ ቢያሰሙም የሚድሮክ ለገደምቢ የወርቅ ማምረቻ የንግድ ፍቃድ እንደተደረገለት ተሰምቷል።

ይህንን ተከትሎ ነው ከሰሞኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሰሚ ያለህ ሲሉ ጩኸታቸውን ያሰሙ የቀጠሉት።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አቋም የትኛውም ኢንቨስትመንት ሕዝቡን የሚጠቅም መሆን አለበት የሚል ነው የሚሉት የክልሉ ኮሚዩኑኬሽን ኃላፊ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ናቸው።

“በምንም አይነት መልኩ ሕዝቡን የሚጎዳ ከሆነ ተቀባይነት የለውም” ሲሉም ያስረግጣሉ።

ቢቢሲ የለገደንቢ ሚድሮክ የወርቅ ማምረቻ በአካባቢው የሚኖሩ ማህበረሰቦች የጤና ጠንቅ እንደሆነባቸው የሚያትት ዘበጋ ከዚህ ቀደም ሰርቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ይህንን ጉዳይ ሕዝቡና አመራሩ በተለያየ ወቅት ያነሱ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ነገሪ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሕፃናት መወለዳቸውን እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ነፍሰጡር እናቶች ውርጃ እያጋጠማቸው እንደሆነ በምሳሌ በመጥቀስ የነገሩን ክብድት ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደም ይህንንም ችግር ለመፍታት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና ከድርጅቱ አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉንና የመፍትሔ አቅጣጫ ይሆናል ያሏቸውን ነጥቦች ማስቀመጣቸውንም ያስታውሳሉ።

“በተደረገው ውይይት ደረሰ ለተባለው የአካል ጉዳት እና ውርጃ ያሉ ማስረጃዎች ተወስደው ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎ እንዲለይ ተስማምተን ነበር” የሚሉት ዶ/ር ነገሪ ይህንን ተንተርሶም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥናት መጀመሩን አሁን በአካባቢው ያለመረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ ባደረጉት ውይይት እንደተረዱ ተናግረዋል።

“ሕዝቡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ እያነሳ ሳለ የተደረገ ጥናት ውጤትም ውይይት ሳይደረግበት የውል እድሳት መደረጉ ትክክል አይደለም” ባይ ናቸው ኃላፊው።

“ድርጅቱ ከዚህ በፊት የተለያዩ የሰው ኃይል ፍላጎቱን ለማሟላት በሌላ ስፍራ ማስታወቂያ አውጥቶ ይቀጥር እንደነበረ ያስታወሱት ዶ/ ር ነገሪ አሁን ግን መስራት ለሚችሉ አቅሙ እና ብቃቱ ላላቸው ለአካባቢው ወጣቶች እድል ለመስጠት ማስታወቂያ በስፍራው እንዲወጣና እንዲወዳደሩ ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም ይህ ጉዳይ ምን ያህል እንደተስተካከለ ግልፅ አይደለም።”

በተወሰነ ደረጃ በድርጅቱ በኩል እዚያ አካባቢ ማስታወቂያው እንዲለጠፍ ቃል የተገባ ቢሆንም ይህንን ከህዝቡ ጋር በዚህ መልኩ ተስተካክሏል በሚል ውይይት ሳይደረግበት ነው ወደ ውል እድሳት የተገባው ይላሉ።

“አካባቢው ለማዕድን ልማት በሚደረገው ቁፋሮ የተጎዳ ስለሆነ የተፈጥሮ ሃብቱን ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል የመልሶ ማልማት ስራ መሰራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር” የሚሉት ዶ/ር ነገሪ ይህም በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተሰራ አስታውሰዋል።

የሻኪሶ ከተማ

“የትኛውም ድርጅት ንብረቱን የሚጠብቅለት የፀጥታ አካል ሳይሆን ማሕበረሰቡ ነው” የሚሉት ዶ/ር ነገሪ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች መሰራት እንደሚኖርባቸው አስመረዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ድርጅቱ ገንዘብ መድቦ የተወሰኑ ስራዎች እየሰራ ነው የሚሉ ነገሮች ቢኖሩም ሕዝቡ ግን በሚፈልገው መጠን ተጠቃሚ አለመሆኑን እያነሳ ባለበት ወቅት ነው ይህ የውል እድሳት ወሬ ይፋ ባልሆነ መልኩ በአንዳንድ የግል ብዙሃን መገናኛዎች በኩል የተሰማው ይላሉ ዶ/ር ነገሪ።

“ሕዝቡን ለማረጋጋት የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። የክልሉ መንግስትም ሕዝቡን የሚጎዳ ኢንቨስትመንትን እንደማይቀበለው ልናረጋግጥ እንወዳለን፤ ይህንን ለማስተካከል ከሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር ጥብቅ ውይይት ላይ ነን። የተሰራው ስህተት ላይ ግን መግባባት ላይ ደርሰናል” ሲሉ ይገልፃሉ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ስለተፈጠረው ስህተት ሕዝቡን ይቅርታ ለመጠየቅ ወደ ስራ እንደሚገቡ የተናገሩ ሲሆን የተጠናው ጥናት ላይም ውይይት ከህዝቡ ጋር እንደሚያደርጉ ስለገለፁ የተፈጠረው ችግር በቅርቡ ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ባጫ ሩጂ የሜድሮክ ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ውል ከአንድ ወር በፊት መራዘሙን አስረግጠውልናል።

አቶ ባጫ የወርቅ ማምረቻው ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ውጤቱ ህብረተሰቡን የሚጎዳ ሆኖ ከተገኘ ውሉ እንደሚቋረጥ አስታውቀዋል።

 BBC NEWS AMHARIC

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here