በአላማጣ ከተማ በማንነት ስም በሚንቀሳቀሱ አካላት እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የትግራይ ክልል የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ባወጣው የክልሉ መንግስት መግለጫ በተፈጠረው አለመግባባት ከሞቱት በተጨማሪ በፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት መድረሱንም ጠቅሷል።

የህዝብን የማንነት ጥያቄ በማስመሰል ሌላ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተደረገ ያለው ሩጫ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል።

ቢሮው በመግለጫው የዜጎች ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነትን ለመጠበቅ ከተሰማራ የፀጥታ መዋቅር ጋር መጋጨትና አነሳስቶ እርምጃ እንዲወስድ መገፋፋት መደገም የሌለበት ተግባር መሆኑንም አንስቷል።

በተፈጠረው አለመግባባትም የሶስት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፥ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም የተሰማውን ሐዘን እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ተመኝቷል።

ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካልም ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄውን ማቅረብና መልስ ማግኘት እንደሚችል ያነሳው መግለጫው፥

ፍላጎትን በኃይል ለማስፈፀም መንቀሳቀስ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት መሆኑን ገልጿል።

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ እንደሚያደርግም በመግለጫው አስታውሷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here