በአዲስ አበባ ዙሪያ ባለው አዋሳኝ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማ በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው መረጋጋት በአዲስ አበባ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ከነበሩ 15 ሺህ 86 ያህል ተፈናቃይ ዜጎች መካከል 1 ሺህ 786 ያህል ወደመጡበት የመኖሪያ ቀያቸው ተመልሰዋል፡፡

በመሆኑም በዛሬው እለት ቅዳሜ መስከረም 12 /2011 አ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ተፈናቃይ ዜጎች ቁጥር 13 ሺህ 300 ደርሷል፡፡

አስተዳደሩ ከ13 ሺህ 300 ተፈናቃዮች ዘጠኝ ሺህ ያህሉን ጊዜው የትምህርት ቤት መከፈቻ ወቅት ከመሆኑ አንጻር በመጪው ሰኞ እለትም መስከረም 14 ቀን 2011 አ.ም የትምህርት ቤቶች የ2011 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ እለት በመሆኑ ከነበሩባቸው ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች ተፈናቃዮችን ወደ ሌላ ቦታ ማሸጋሸግ በማስፈለጉ ይህንኑ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ ይገኛል ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በአሁን ወቅት በስድስቱ ክፍለ ከተሞች ባሉት ሃያ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ላሉት 13300 ያህል ተፈናቃዮች በቀጣይ ወደ ነበሩበት ቀዬ ተመልሰው የተረጋጋ ኑሮአቸውን በዘላቂነት እስከ ሚቀጥሉ ድረስ ባለፈው ቅዳሜ አመሻሽ መስከረም 05/2011 ዓ.ም ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ አስከ አሁን ድረስ 20000000 / ሃያ ሚሊዮን /ብር በላይ በሆነ ወጪ መሰረታዊ የሆኑ የምግብ ፣ ውሃ አልባሳትና መሰል እርዳታዎችንና የጤና አገልግሎትን ማቅረቡን ቀጥሏል ፡፡

አስተዳደሩ ለተፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎቻችን ካቀረባቸው የምግብና የውሃ አቅርቦቶች በተጨማሪ ፍራሽ 4069 ፣ ብርድ ልብስ 4000 አንሶላ 4500 እንዲሁም በርካታ የመመገቢያ ሳህኖች ኩባያዎችና የንጽህና መጠበቂያ ማቴሪያሎች ያልሚ ምግቦችና አልባሳት እንዲቀርብላቸው ተደርጓል ፡፡

እነዚህ ዜጎቻችን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻርም በገቡባቸው የመጠለያ ጣቢያዎች 47 በላይ የጤና ባለሙያዎች ተመድበው የበሽታ መከላከል ፣ ተንቀሳቃሽ ጤና አቅርቦትና የአስቸኳይ ጊዜ የጤና አገልግሎት የንጽህና ቁጥጥር ፣ የጤና ሎጂስቲክ አቅርቦቶችና በየጣቢያው ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ጣቢያዎች ተደራጅተው የህክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ፡፡

ተንቀሳቃሽ የህክምና ቡድኑ በየጣቢያዎቹ የመድሃኒት አቀርቦት በማሟላት ተጨማሪ የሪፈር ስርዓት ለሚፈልጉት ደግሞ ከ ዘጠኝ ሆስፒታሎች ጋር በማስተሳሰር ህክምና እየሰጡ ይገኛሉ ፡፡

በሁሉም ጣቢያዎች የጽዳት መጠበቂያ ገንዳዎች ፣ የጽዳት አገልገሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ተመድበው የደረቅና ፍሳሽ ማስወገድ አገልግሎትን እያከናወኑ ነው ፡፡ ለንህጽና አገልግሎት የሚውል የውሃ አቅርቦት በበቂ እንዲኖር ከማድረግ በተጨማሪ የውሃ ቦቴዎችና የፍሳሽ ማስወገድ ተሸከርካሪዎች ተመድበው አስፈላጊ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ፡፡

ተጎጂዎችም ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ ስፍራ የሚያመላልስ የትራንስፖርት ስምሪት እንዲኖር የተደረገ ሲሆን ሰብዓዊ እርዳታዎችን እያቀረቡ ይገኛሉ።

በየመጠለያ ጣቢያዎቹ ለተፈናቃዮቹ ሁሉን አቀፍ አገልግሎትና መረጃ የሚሰጡ ከጤና ፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ፣ ከፖሊስ ፣ ከአዲስ አበባ ስራ አስኪያጅ እና ከኮሙኒኬሽን የተውጣጡ አባላትን ያቀፈ የጣቢያ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየመጠለያ ጣቢያዎቹ አስፈላጊውን አገልገሎት በቅርበት እንዲሰጡ ተቋቁመዋል ፡፡

የከተማችን ነዋሪ እንደ ወትሮ ሁሉ ችግሩ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከአስተዳደራችን ጎን በመቆም ለተፈናቃይ ወገኖች የዕለት እርዳታ በዓይነት ከማቅረብ ጀምሮ በማስተባበር እንዲሁም የስነ ልቦና መረጋጋት እንዲኖር ሰብዓዊና የሞራል ድጋፍ በማድረግ ላሳየሁ ወገናዊነትና ቅንነት የተሞላ ተግባር አስተዳደሩ በድጋሚ የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል ፡፡

በአሁን ወቅት ህዝባችን ተፈናቃዮቹን በገንዘብ ለመደገፍ እያሳየ ያለው ፍላጎት እና ተነሳሽነት እየጨመረ በመምጣቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት የማቋቋም ሃላፊነት ካለበት የቡራዩ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ የተወያዬ ስለሆነ በተደራጀ መንገድ ገቢ የሚሰባሰብበትን ይፋዊ አካውንት በመገናኛ ብዙሃን በኩል የቡራዩ ከተማ አስተዳደር እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል ፡፡

የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መስከረም 12 /2011 ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here