ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተከሰተው ቀውስ የሟቾች ቁጥር 28 መድረሱን ፖሊስ ገልጿል።

ቀውሱንም ተከትሎ በአዲስ አበባ የተለያዩ መጠጥ ቤቶችን ጨምሮ የመዝናኛ ቦታዎች ወደ ሦስት ሺ ሁለት መቶ የሚሆኑ ሰዎች በጅምላ እንደታሰሩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ አስታውቋል።

ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልፆው መቶ ሰባ አራት ለፍርድ እንደሚቀርቡ እንዲሁም አንድ ሺ ሁለት መቶ አራት ሰዎችን ለማነፅና ለማስተማር በሚል ወደ ጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ለተሐድሶ ስልጠና ተልከዋል።

ጅምላ እሥር በአዲስ አበባ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩትን እንዳሰረ ቢገልፅም አምነስቲ በበኩሉ እስሩን አውግዞ በአሁኑ ሰዓት እየታዩ ያሉ ለውጦችን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው ብሏል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች አዲስ አበባ ላይ መታስራቸው በተለይም ከሺሻ ቤቶችና ጫት ቤቶች መወሰዳቸው ጋር ተያይዞ ሺሻ ህገ ወጥ ነው?

ከሆነስ ግለሰቦቹ ወደ ፍርድ ቤት ለምን አልቀረቡም? ወደ ተሐድሶ ካምፕ ለምንድን ነው? የሚላኩት የሚሉ ክርክሮች መነሳት ጀምረዋል።

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ባለስልጣን የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ መጋቢት ወር 2007 ዓ.ም ያወጣ ሲሆን፤

በመመሪያውም መሰረት የትምባሆ ምርቶች በማለት የሚዘረዝራቸው በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ከትምባሆ ቅጠል የተዘጋጁ በማጨስ፣ በመሳብ፣ በማኘክ፣ በማሽተት

ወይም በሌላ መንገድ የሚወሰድ ማንኛውም ንጥረ ነገር ሆኖ የጋያ ወይም የሺሻ ትምባሆን፣ የኤሌክትሮኒክ ኒኮቲን ይጨምራል።

የመመሪያው ዓላማም በዝርዝር የተቀመጠ ሲሆን ትምባሆን በመጠቀምና ለትምባሆ ጢስ በመጋለጥ በማህበረሰቡ ላይ የሚደርሰውን የጤና፣ የማህበራዊ፣

ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ጉዳቶችን ለመከላከልና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመማቻቸውን የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽንም ለማስፈፀም ነው።

በእርጥብ ሳርና ቅጠል ጥቃትን ያስቆሙ አባቶች

መመሪያው ከባለስልጣኑ ፈቃድ ሳያገኝ የትምባሆ ምርትን ለንግድ ተግባር ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት፣ ማከፋፈል ወይም በጅምላ መሸጥ እንደማይቻል ያስቀመጠ ሲሆን፤

የትምባሆ ምርትን ማስተዋወቅና ስፖንሰር ማድረግ በፍፁም የተከለከለ እንደሆነ በግልፅ አስቀምጧል።

በዚህም መሰረት ማጨስ የተከለከለባቸው ቦታዎች ተብለው የተቀመጡት፤ በህዝብ መጓጓዣዎች፣ በጤናና በትምህርት ተቋማት፣ በምግብ ቤቶች፣

በመዝናኛ ቦታዎች፣ በአውሮፕላን ማረፊያ፣ በፋብሪካዎችና በህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾች ናቸው።

ምንም እንኳን በነዚህ ቦታዎች ቢከለከልም ከትምህርት ተቋማት፣ ከመንግሥት መስሪያ ቤትና ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ውጭ

ለማጨስ የተከለለ ወይም የተሰየመ ክፍል ለብቻው የአየር ማናፈሻ ( ventilation) የተገጠመለት ከሆነ በሌሎቹ ቦታዎች ማጨስ እንደሚቻል ተቀምጧል።

በዩኒቨርስቲ፣ በኮሌጅና በሌሎች ተቋማት የተከለለ ክፍል ካለ ትምባሆንም ሆነ የትምባሆን ምርት መገልገል እንደሚቻልም መመሪያው ያትታል።

ጅምላ እሥር በአዲስ አበባImage copyrightMAHEDER HAILESELASSIE TADESE

ካለፉት አስር ዓመት ሺሻ ቤቶች ህገ-ወጥ ተብለው ሲታሸጉና እቃዎችም የተወሰዱ ሲሆን፤

በተመሳሳይም ጫት ቤቶችንም ጫት መሸጥ ነው እንጂ የማስቃም ፈቃድ የላችሁም በሚል ሲዘጉ እንደነበር የህግ ባለሙያና ጠበቃ የሆኑት አቶ ታምራት ኪዳነ ማርያም ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ብዙዎቹ ንግድ ቤቶች ፍቃድ አግኝተው በዛ መሰረት እየሰሩ ያሉ ሲሆን፤

“ሁልጊዜም የሚነሳው ጭቅጭቅ እንዲሸጡ ነው እንጂ እንዲያስቅሙ አልተፈቀደላቸውም” የሚል እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ።

“ትምባሆ ማጨስ የተፈቀዱባቸው ቦታዎች በመመሪያው በግልፅ የተቀመጡ ሲሆን፤ ስለ ጫት ግን የት መቃም እንደማይቻል የተደነገገ ደንብ የለም” ይላሉ።

ምናልባትም ነጋዴ የተሰጠው ፈቃድ ለመቸርቸር ከሆነ ሰዎችን ሰብስቦ የሚያስቅም ከሆነ የተሰጠውን ፈቃድ በመተላለፍ ሊጠየቅ ይችላል።

የደንብ መተላለፍ ወንጀሎች ቀላል ሲሆኑ ለምሳሌ ትምባሆ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ማጨስ አብዛኛውን ጊዜ በገንዘብ ቅጣት የሚታለፉ ናቸው።

የንግድ ቤቶቹ ግን ህገ-ወጥ (ከተፈቀደው ውጭ) ተግባር በማከናወን ጠንከር ያሉ ቅጣት ሊጣልባቸው ይችላል።

ስለተፈፀመው ጥቃት እስካሁን የምናውቀው

እነዚህን ደንቦች ካልተከተሉ ከአስተዳደራዊ እርምጃ ጀምሮ፣ ከንግድ ፍቃድ መሰረዝ በወንጀል ተጠያቂ እስከማድረግ መመሪያው የሚጠቅስ ሲሆን፤

ተጠቃሚዎች ደንቡን ተላልፈው ቢገኙ ወይም ስለ ተጠቃሚዎች መመሪያው የሚያትተው ነገር የለም።

መመሪያው ተጠቃሚዎችን ምንም ካላለ በምን የህግ ማዕቀፍ ነው የታሰሩትስ ወይም ተጠያቂ የሚሆኑት?

ሰሞኑን አዲስ አበባ የታፈሱ ሰዎች ከሺሻ ማጨስ ጋር መያያዙንም አስመልክቶ ባለሙያው “ተጠቃሚዎቹ በምን አግባብ ነው የሚታሰሩት፤

ባለቤቶቹን በህገ-ወጥ (ያለ ፈቃድ) መነገድ በሚል ተጠያቂ ሊሆኑ ይችል ይሆናል” የሚሉት የህግ ባለሙያው “ተጠቃሚዎችን አጭሳችኋል ብሎ ለመያዝ በጣም ከባድ ነው” ይላሉ።

በተከለከለ ቦታ ትምባሆ አጭሳችኋል በሚል ከሆነ በገንዘብ ቅጣት ወይም በመደበኛ ፍርድ ቤት ሳይሆን በከተማው ፍርድ ቤት ደንብን በመተላለፍ ሊጠየቁ እንደሚችሉም ይናገራሉ።

“ለማፈስና ወስዶ ለማሰር ምንም መሰረት የለውም፤ ደንብ ተላልፈዋል የሚል አግባብ ካለ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርባቸዋል።

ከከተማ አርቆ ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ የሚያስችል ህግ የለም፤ ከፀጥታ ጋር የሚገናኝ ወይም ሌላ የፖለቲካ ምክንያት ከሌለው እንዲህ አይነት ህግ የለም” ይላሉ ባለሙያው።

ለማነፅ፣ ለማስተማር የሚባለው ሃሳብ ባለሙያው እንደ በጎ ቢያዩትም ይህንን ለማድረግ ህግ ያስፈልጋል ማስተማርና መመለስ የሚችለው ፍርድ ቤት እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

“ጥፋተኛ ብሎ ቀጥቶ፤ በዚህ አይነት መልኩ ይታረሙ የሚል የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ፍርድ ቤት ማዘዝ ይኖርበታል።

ነገር ግን አስፈፃሚው አካል (መንግሥት) ፍርድ ቤቱ እንዲህ አይነት ውሳኔ ሳይወስን በራሱ ጊዜ ባለስልጣናት ተነስተው እነዚህን ልጆች እናርማቸው፣ እንኮትኩታቸው ብሎ ወስዶ ለማረም መሞከር ትክክል አይደለም። ህጋዊም አይደለም።”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here