በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተካሄደው የድንበር ጦርነት ካበቃ ከ15 ዓመታት በላይ ሆኖታል። አሁን ያለውን “ሰላምም ጦርነትም የለሽ” ሁኔታን ለማስተካከል በተለያዩ ወገኖች የተደረገው ጥረት ውጤት አላስገኘም።

ይህ ችግር ሙሉ በሙሉ እንኳ ባይሆን በተወሰነ መልኩ ተፈቶ ህዝባዊ ግንኙነት የሚያጠናክር ሰላማዊ ሁኔታ ይፈጠር ዘንድ የተለያዩ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ወጣቶች በዚህ ጉዳይ ላይ በማሕበራዊ ድረ-ገጾች ሲያደርጉት የቆየው ውይይት የምሁራንን ትኩረት ያገኝ ዘንድ እየተንቀሳቀሰ ነዉ።

እንዴት ሆነ?

በሁለቱ አገራት ዜጎች መካከል ወደፊት ሰላም ለመፍጠር የሚያስችል አስተሳሰብ የሚፈጥሩበት የውይይት መድረክ ተጀምሯል።

ኤርትራዊው የሰላምና የሽምግልና ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ይስሃቅ ዮሴፍ ሰላም ለመፍጠር ይህ እንቅስቃሴ የህዝቡን ግንዛቤ በማሳደግ በሁለቱ አገራት መካከል ያለዉ መሰረታዊ ችግርን የሚገነዘብ ማህበረሰብ መፍጠር ነዉ ይላሉ።

“በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረዉ ለመግባባት ታሪካዊ ዳራዉ ምን እንደሆነ የሚያስረዱ ምሁራንና ወጣቶች የሚሳተፉባቸዉ መድረኮች ተጀምረዋል። ከሁሉም በላይ ህዝባዊ መሰረት ያለው መግባባት መፈጠር አለበት፤ ለዚህም ህዝብን ትኩረት ያደረገ ሥራ ይሰራል” ይላሉ።

በመንግስታት መሃል የተፈጠረዉ ችግር ለህዝቡ፤ በተለይ ደግሞ በድንበር አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብን እንደጎዳው የገለጹት አቶ ይስሃቅ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት መንግሥታትም ሆኑ የዓለም ማህበረሰብ ያደረጉት ጥረት ውጤት ማምጣትና መሳካት እንዳልቻለ ይናገራሉ።

ህዝብ ለህዝብ ማቀራረብ የመድረኩ አላማ ነዉ የሚሉት ፕሮፌሰር መድሃኒዬ ታደሰ ደግሞ፤ የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነትን ወደ ቦታዉ መመለስ ግባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

“ሰላም ከሁሉም በላይ ነዉ። አሁን እየገፉ የሚመጡት ስጋቶች እንዳይጥሉን ህዝቡን በማቀራረብ ሰላም መፍጠር አስፈላጊ ነዉ” ይላሉ ፕሮፌሰር መድሃንዬ።

መንግሥታት ጥል ላይ እያሉ እርቅ?

“ሁለቱም ህዝቦች ችግር ላይ ነዉ ያሉት” የሚሉት የታሪክ ምሁር አቶ ገብረኪዳን ደስታ ጥል የሌለበት ህዝብ በፖለቲካዊ ጉዳይ መታሰር የለበትም ይላሉ።

“አለመግባባት ፖለቲከኞች መሃል ነዉ ያለዉ። ህዝብ ሰላም አግኝቶ በማህበራዊም ኢኮኖሚያዊም ጉዳዮች ላይ መገናኘት አለበት። የሰላም ዋጋ ውድ ስለሆነ ቂም የሚይዝ መንግሥት መኖር የለበት” ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላዉ ቀርቶ በባህል፣ ድንበርና ታሪክ የሚገናኙ ግን ማዶ ለማዶ የሚተያዩ ህዝቦች ሆኖዉ መቅረት የለባቸዉም በሚል ብዙዎች ይስማማሉ። ይህን ችግር ለመፍታት የአቅማቸዉ ለማበርከት እየተንቀሳቀሱ ያሉት የሁለቱም አገራት ዜጎች መንግሥታት ቢስተካከሉ ሁሉ ነገር ሊፈጥን ይችላል ይላሉ።

ፕሮፌሰር መድሃንዬ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። መንግሥታት የህዝብ ግንኙነትን ችላ ብለው ችግሩን ለመፍታት ከደከሙ የህዝብ ዲፕሎማሲ ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ያስቀምጣሉ።

“የንግድ ግንኙነት፣ የሙዚቃና ስፖርት ዝግጅቶች ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ይገለጽባቸዋል። ስፖርት ትልቅ አብነት ነዉ። በትላልቅ የስፖርት ውድድር መድረኮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሲንጸባረቅ ነዉ የምናየዉ። በእኛ መሃል ይህ ነዉ የሌለዉ” ይላሉ።

የሁለቱ አገራት መንግሥታት የገቡበትን ጦርነት ተከትሎ ኩሪፊያ ላይ መሆናቸዉ ዓለም ያወቀው እዉነታ ነዉ የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ዘሪሁን ተሾመ፤ አሁን ግን “ኩርፊያዉ ራሱ ወደ ማኩረፍ እየተቀየረ ያለ ይመስላል” ይላሉ።

“ኩርፊያ ይዘህ የህዝብ እጣ ፈንታ መወሰንና ማስቀጠል አዋጪ ስላልሆነ የህዝብ ግፊት ካለ መንግስታት ቆም ብለው እንዲያስቡ ይረዳል። በተለይ ድንበር አካባቢ የሚኖረው ህዝብ ሃዘኑ፣ ደስታውና ሌሎች ጉዳዮችን እየተካፈለ አይደለም። ህዝብ በኩርፊያ ታስሮ ሊኖር ስለማይገባው ኩርፊያው ይበቃል ሊባል ይገባል” ይላሉ።

ስጋቶቹ ምንድ ናቸ?

እነዚህ አገራት የገቡበት ጦርነት ቋሟል ቢባልም መንግሥታቱ ተፋጠው ነዉ ያሉት። ይህ ሁኔታ ደግሞ ህዝቡን ፍራቻና ጭንቀት ላይ ጥሏል ይባላል።

እኛ የሚያገናኘን አጀንዳ አለ ነው የምንለው የሚሉት ፕሮፌሰር መድሃንዬ፤ እየተንሰራፉ ያሉት አደጋዎች ሳይበሉን የህዝቡ ግንኙነት ወደ ነበረበት መመለስና ሰላም መውረድ አለበት የሚል እምነት አለባቸው።

“ከባድ አደጋዎች እየመጡብን ነዉ። እንዲህ ብለን መቀጠል የለብንም። ሲጀመር ጀምሮም አሁን ያለንበት ደረጃ መድረስ አልነበረብንም የሚል መግባባት ይዘን ወደ ህዝብ እንቀርባለን።”

ምሥራቅ አፍሪካ ለብዙ ዓመታት የቆዩ ስጋቶች በአካባቢው እንዳሉ ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ ህዝቡ የአከባቢው ባህር፣ ውሃ፣ ብሄር፣ ድንበር፣ ታሪክ፣ ባህልና ጂኦግራፊ እስረኛ ነው ይላሉ።

“ለብዙ ሺ ዓመታት ተደምረው የመጡ የጸጥታ፣ የከባቢ አየር፣ ሽብርተኝነትና የአክራሪነት ችግሮች ቀጠናው ላይ አሉ። እነዚህ በአንድ መንግሥት ወይም ትውልድ የሚፈቱ አይደሉም። ቢሆንም አሁን አካባቢውን በተለየ መንገድ ሊያጠፉት የሚችሉ ችግሮች አሉ። የእነዚህ አገራት ችግር ካልተፈታ ደግሞ የከፋ ይሆናል” ይላሉ።

ከዚህ ባለፈ ይላሉ ምሁሩ ”አሁን በቀጠናው የውጭ ኃይሎች እንቅስቃሴ ጎልቶ እየታየ ነው። ይህ የሁለቱንም ህዝብ አቅም በማዳካም፤ ህዝቦቹ በመጻኢ እድላቸው ላይ የማይወሱንበትን ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል” የሚል ስጋት አላባቸው።

ለምን አሁን?

ይህ እንቅስቃሴ ቀደም ብሎ ሊጀመር ይገባ ነበር የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ ሁለቱ አገራት ያሉበት ”ሰላም የለሽ ጦርነት የለሽ” ሁኔታ ለህዝብ እንዳልጠቀመ በመግለጽ “በዓለም እያደገ የመጣው ቀኝ ዘመም ፖለቲካ የሚፈጥረው የስበት አቅም በቀጠናው የራሳችንን እጣ እራሳችን እንድናይ አስገድዶናል” ይላሉ።

በሌላ በኩል ፕሮፌሰር መድሃንዬ “መንግሥታት እና ችግሩን ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለበት የዓለም ማህበረሰብ አካሄዳቸው ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጥቷል። ትላልቅ አገራት የሁለቱንም ችግር ለመፍታት ያላቸው አቅምና ፍላጎት እየሞተ፣ ህዝብ ሊያጠፋ የሚችል ፖለቲካዊ ችግር እየተፈጠረ ስለመጣ፣ አሁን እንዳለፉት ጊዜያት መንግሥታትን አንጠብቅም” ሲሉ ለምን አሁን የሚለዉን ያብራራሉ።

“አደጋው ከባድ ነው። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ የሚያገናኛቸውን ጉዳይ ፈትሾ ችግሩ በመፍታት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር ካልተቻለ ፈተና ይገጥማቸዋል። ስለሆነም ህዝብ ችግሩን ፈትቶ ወደ ፊት የሚጓዝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት” ይላሉ ፕሮፌሰር መድሃንዬ።

ይህ ችግር የህዝቡን ግንኙነት ከመጉዳቱ በላይ ሊገኝ ይችል የነበረን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አሳጥቷል የሚሉት አቶ ዘሪሁን፤ “የቀጥታ የንግድ ግንኙነት እና በአዋሳኝ አካባቢዎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ምክንያት በመሆኑ ህዝብ ተጎድቷል። ይሄንን ተሸክመን መቀጠል ስለሌለብን መንግሥታት ይሄን ተገንዝበው ወደ አቅም አጎልባች ስምምነት መምጣት አለባቸው” ይላሉ።

መግባባትን መፍጠር

አቶ ይስሃቅ “በቀጣይ ህዝብ የእኔ ነው ብሎ በሚያካሄዱ መድረኮች መሳተፍ አለበት። ህዝብ መሪ ሆኖ ከመጣ መንግሥት የህዝቡን ድምጽ የማይሰማበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም” ይላሉ።

ህዝብን ያማከለ ድምጽ ሲቀርብ መንግሥታት የማይቀበሉበት እድል እንደሌለ በመግለጽ የአስተሳሰብ አንድነትና ጥንካሬ መፈጠር እንዳለበት ገልጸዋል።

“መንግሥታት ሃላፊ ናቸዉ፤ ህዝብና አገር ግን ይቀጥላሉ። ስለሆነም መኮራረፉንና ቂምን ማብቃት አለብን። መጪውን እጣችን የሚያበላሹ ችግሮችን በመፍታት የአገራት ግንኙነት መቀየር አለብን” ሲሉ አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር መድሃንዬ በዚህ ዙርያ ያላቸዉ አስተያየትን ሲያጠቃልሉ “በግድ የለሽነትና ስትራቴጂካዊ አስተሳሰብ ባለመኖሩ ብዙ ስልጣኔ ጠፍቷል። ከአሁን በኋላ ህዝብ ኢኮኖሚው፣ ባህሉ፣ ታሪኩና መሪነቱን መጠበቅ ይገባል” ይላሉ።

BBC AMHARIC NEWS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here