በሱማሌ ክልል ተከስቶ የነበረውን ግጭት አነሳስተዋል በሚል እና በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙት

የቀድሞ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አብዲ መሀመድ ኡመርን ጨምሮ በ4ቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ለተጨማሪ ምርመራ ፖሊስ የጠየቀው 1ዐ ቀን ተፈቀደ፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት ከዚህ በፊት በተፈቀደለት 1ዐ ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ዘርዝሯል፡፡

በግጭቱም ህይወታቸው የጠፋ ሰዎች የተቀበሩበት የጅምላ የመቃብር ስፍራ በማግኘት ለምርመራ መላኩንና

በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውንና በህክምና ተቋማት ውስጥ የነበሩ 62 ሰዎች የህክምና ማስረጃ የማስተርጎም ከተከናወኑ የምርመራ ስራ ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል፡፡

የ11 ምስክሮች ቃል መቀበሉንና 14 ተንቀሳቃሽ ስልኮች 1ዐ ሲም ካርዶችን መያዙንም የምርመራ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡

ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን፣ ፖሊስ 1ዐ ተጨማሪ ቀን ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ለቡድኑ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ አዳዲስ ስራዎችን እያቀረበ አይደለም

እንዲሁም አቤቱታው ግልፅነት እንደሚጎድለው በመግለፅ ሌሎች ምክንያቶችን በመጥቀስ የተጠየቀው የምርመራ ጊዜ ውድቅ እንዲደረግ አመልክተዋል፡፡

ግራቀኙን የመረመረው ችሎቱ ተጨማሪ ምርመራ መኖሩን በመገንዘብ ፖሊስ የጠየቀውን 1ዐ ቀን ፈቅዷል፡፡ ውጤቱን ለመጠባበቅም ለጥቅምት 29/ 2ዐ11 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ችሎቱ አያይዞም ሂጎ እየተባለ የሚጠራውን ቡድን ተቀላቅለው ጥቃት ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙት ጉሌድ አበል ዳውድ እና ወርሰቤ ሸክ አብዲ ሸሂድ ጉዳይንም ተመልክቷል፡፡

በተለይም ወርሳቬ የተባለው ተጠርጣሪ 14 ዓመት መሆኑን በመጥቀስ የመብት ጥያቄ ማንሳቱን ተከትሎ የቅዱስ ጳውሎስ ሚኒሊየም ሆስፒታል የግለሰቡን እድሜ ሁኔታ በተመለከተ የላከውን ማረጋገጫ ተመልክቷል፡፡

በዚህ መሰረት ችሎቱ የህክምና ማስረጃ ዋቢ በማድረግ የተጠርጣሪውን ዕድሜ ከ18 እስከ 2ዐ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በዚሁ ፍርድ ቤት እንዲታይ እና የምርመራ ውጤቱ ከነአብዲ መሀመድ ኡመር መዝገብ ጋር ለማየት ለጥቅምት 29/2ዐ11 ቀጥሯል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here