(ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን በጨለንቆ በደረሰው ግጭት የ16 ዜጎች ህይወት ማለፉን የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዪኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሀላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገልፀዋል።

ዶክተር ነገሪ በፋና ቴሌቪዥን ከፋና 90 ጋር በነበራቸው ቆይታም ይህ ሁኔታ በፌደራል መንግስቱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው እና ግጭቶች ሲከሰቱ ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ በመውሰድ የሰው ህይወት እንዳያልፍ የፀጥታ አካላት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው ያመለከቱት።

ስለተከሰተው ግጭትም የብሄራዊ የፀጥታ ምክር ቤቱ አጣርቶ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

መንግስት በጠፋው ህይወት የተሰማውንም ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል።

በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይከሰቱ ግጭቶች ሲኖሩ ዜጎች ከስሜት ነፃ ሆነው ሀሳባቸውን እንዲገልፁ፤ የፀጥታ አካላት ደግሞ የማይመለሰው የሰው ህይወት እንዳያልፍ ቅድሚያ ሰጥተው ችግሮችን እንዲፈቱ ነው ያሳሰቡት።

መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ህገመንግስታዊ ሀላፊነቱን ይወጣል ያሉት ሚኒስትሩ፥ በተለይም በተቋቋመው የፀጥታ ምክር ቤት በጥልቀት በመመርመር አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

ሚኒሰትሩ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች የተከሰተው ሁኔታ ቀደም ሲል በተማሪዎች ሲነሳ ከነበረው ጥያቄ ጋር የማይገናኝ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም በወልዲያ ከስፖርት ሁነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ነገር ተከትሎ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ከዚያም ቀጥሎ በወለጋ እና በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ብሄርን ማዕከል ባደረገ መልኩ በተፈፀመ ጥቃት የተማሪዎቻች ህይወት አልፏል ነው ያሉት።

በዚህም መንግስት የተሰማውን ሀዘን ይገልፃል ያሉት ዶክተር ነገሪ፥ ይህ መቆም ስላለበት የተማሪዎች ደህንነት እንዲጠበቅ የፌደራል መንግስቱ ከክልሎች ጋር እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በአሁኑ ሰዓት መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጦባቸው በነበረባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የተሻለ ሁኔታ እንዳለ ነው የጠቆሙት።

የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥልም የትምህርት ሚኒስቴር ከክልሎች እና ከአካባቢ ማህበረሰቦች ጋር ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ በሀገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ላይ መሆኑን አንስተዋል።

ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣትም በግለሰቦችም ሆነ በተቋም ደረጃ መስተካከል ያለባቸውን ስራዎች ለመስራት የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይኖራሉ ብለዋል።

እነዚህም ውሳኔዎች ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here