ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ዘጠኝ ትልልቅ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች መካከል የሶስቱ መገኛ የአማራ ክልል ነው፤

በዩኔስኮ ከተመዘገቡት ቅርሶች በተጨማሪ የቱሪስቱን ቀልብ በመሳብ ጉልህ ሚና ያላቸው ተጨማሪ ባህላዊና ታሪካዊ ሃብቶች ባለቤት ነው፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ ከዕለት ወደ ዕለት በከፍተኛ የዕድገት ጎዳና በመገስገስ ላይ የምትገኘው የባህር ዳር ከተማ አነሳሷ ከምንም ነው ይባላል፡፡

ደቡባዊውን የጣና ጫፍ የሙጥኝ ብላ በጣት በሚቆጠሩት የሳር ጎጆዎች አማካኝነት የተቆረቆረችው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ አምደፅዬን ጊዜ ነበር፡፡

የከተማ ባህሪ መያዝ ከጀመረችበት ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ የዕድሜ ባለፀጋ የሆነችው ይህችው የክልሉ ርዕሰ መዲና ከአዲስ አበባ በ563 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ናት፡፡

በከተማዋ መካከል ቀጥ ብለው በተለያዩ አቅጣጫዎች በተዘረጉት መስቀለኛ መንገዶች ግራና ቀኝ የሚታዩት የዘንባባ ተክሎች፣ በመንትያ መንገዶች መካከል በቅለው የሚገኙት

የተለያዩ ዕፅዋቶችና አበቦች ወደ ቆላነት የሚጠጋው የአየር ፀባይዋና ከጣና ሐይቅ የሚነሳው ቀዝቃዛ አዘል ነፋስ፤

የተፈጥሮ ቃናን በውል ሊያጣጥሙ የሚችሉባቸው መዝናኛ እና መናፈሻ ቦታዎች ባለቤት ናት ባህር ዳር፡፡

ጣና ሐይቅ የራሱ የሆነ ከርሠ-ምድራዊ አፈጣጠር ሂደት ውጤት ነው፡፡

የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ለጣና ሐይቅ መፈጠር የሚያቀርቡት ምክንያት በአንድ ወቅት ከብዙ ሽህ ዓመታት በፊት የተከሰተ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታን እንደሆነ ፅፈዋል ፡፡

ሐይቁ ከሰሜን ደቡብ ሰባ አምስት ኪሎ ሜትር፤ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ደግሞ 60 ኪሎ ሜትር አካባቢ እንደሚረዝም የሚነገርለት የጣና ሐይቅ 3600 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ይዟል፡፡

በግዝፈቱ በኢትዮጵያ አንደኛ በአፍሪካ ደግሞ ከቪክቶሪያና ከታንጋኒካ ሃይቆች ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ይዟል፡፡

ከባህር ጠለል በላይ የ1830 ሜትር ከፍታ፣ጥልቀቱ በአማካይ 9 ሜትር ይሆናል፡፡ ጣና ሐይቅ በውስጡ 37 ደሴቶችን አቅፎ ይዟል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በ13ቱ ደሴቶች በውስጣቸው ከ30 በላይ እድሜ ጠገብ የሆኑ ገዳማትን፣ አብያተክርስቲያናትንና የተለያዩ ብዝሃ ሕይወቶችን አቅፎ ይዟል፡፡

የባህር ዳር ከተማ የተመሰረተችበትን ትክክለኛ ወቅት ለይቶ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም ከ1928 ዓ.ም በፊት መንደር እንደነበረች የሚነገር ሲሆን

ከ1928-1935 ዓ.ም በነበረው የጣሊያን ወረራ ጋር በተያያዘ የከተማነት ቅርጽ መያዟን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከተማዋ በአማካይ ሙቀቷ 19 0c ነው፡፡

ከተማዋን ከሁለት በመክፈል ረጅሙን ጉዞውን ወደ ሜዲትራኒያንን ባህር የሚጀምረው የታላቁ ጥቁር አባይ ወንዝ መገኛም ባህር ዳር ናት፡፡

ከከተማዋ ዕምብርት ምስራቃዊ አቅጣጫ ወደ 5ኪሎ ሜትር የሚጠጋውን እና ግራቀኙን በለመለሙ ዛፎች ያጌጠውን

በቀኝ በኩል በቅርብ ርቀት በአባይ ወንዝ እየታጀበ ሽቅብ እያቀና የሚሄደውን መንገድ በመኪና፣ በእግር ወይም በብስክሌት ተጉዘው

ቤዛዊት ኮረብታ ሲደርሱ የባህር ዳርን ከተማ ሙሉ በሙሉ ለማየት ከማስቻሉ በተጨማሪ በጣና ሐይቅ እና ዙሪያው የሚገኙትን ደሴቶች፣

የጥቁር አባይ ወንዝ ከጣና ሐይቅ እንደወጣ የራሱን ልዩ ትርኢት ፈጥሮ በመሰናበት ላይ መሆኑን፣ የተለያዩ አዕዋፋት እና ጉማሬዎችን የሚመለከቱበት ብቸኛው ማራኪ የተፈጥሮ ማማ ነው፡፡


ቤዛዊት ኮረብታ ላይ አፄ ኃይለሥላሴ በ1959 ዓ.ም ያሰሩት የቤዛዊት ቤተ-መንግስትም ይገኛል፡፡

ቤተ-መንግስቱን በአሁኑ ወቅት ለጉብኝት ክፍት ለማድረግ፤የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች እየተሰሩለት ይገኛል፡፡

የክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር አለም-ዓቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የ24 ሰአት መብራት አገልግሎት፣ የፋይናንስ እና የመድህን ተቋማት፣

ደረጃቸውን የጠበቁ የግል እና የመንግስት የህክምና ተቋማት፣ አለም-ዓቀፍ የፖስታ አገልግሎት፣ የኢንተርኔት፣ የሞባይል ፣ የመደበኛ ስልክና መገናኛ፣

ምቹ የየብስ እና በጣና ጣይቅ የውኃ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ፤ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ሎጅዎች፤መናፈሻዎች እና መዝናኛዎች፣ የባህል ምሽት ቤቶች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ባህላዊ ዕደ-ጥበብ ውጤቶች መሸጫ ተቋማትና

እንዲሁም አስጐብኝዎችና የጉዞ ወኪል ድርጅቶ ያሏት የበርካታ ሰውሰራሽ እና ተፈጥሯዊ መስህብ ሃብት ባለቤት ናት ባህር ዳር፡፡

ከባህር ዳር በ30 ኪ.ሜ እርቀት ላይ በጢስ-ዓባይ ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኘውና በ400 ሜትር ስፋት ከ40 እስከ 50 ሜትር ጥልቀት ወዳለው ገደል

በተለይም ከሀምሌ እስከ ጥቅም ት ባሉት ወራት የሚወረወረው እጅግ አስገራሚው የጢስ-ዓባይ ፏፏቴም የሚገኘው በዚችው በባህር ዳር ከተማ ነው፡፡

ወደ ቤዛዊት ቤተመንግስት በሚወስደው መንገድ የቅርብ ዘመን የኪነ-ጥበብ አሻራ ውጤት የሆነው የአማራ ሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልትም ይገኛል፡፡

የአማራ ሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት ጽ/ቤት የሙዚየም፣የመዝናኛ፣ የፎቶ ጋለሪ፣ የአምፊ ቴአትር፣ የዘመናዊ ቤተ-መጻሕፍት እና የተለያዩ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡

የሙሉዓለም የባህል ማዕከልም በርካታ የኪነ-ጥበብ ስራዎች መፍለቂያ፤የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት እውን ያደረጉ ባህላዊ ክንዋኔዎች፤የሙዚቃ እና ትያትሮችን በማዘጋጀት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ምንጭ፡- Amhara culture& tourism

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here