‘አቀመስከኝ አሉ መድኃኒት በጠላ፣
ፕሬዝዳንት ነህ ማን ካንተ ሊጣላ’
ጋምቢያዊው ላሚን ሲሴ፣ የዛሬ 18 ዓመት ‘በእኔ ይብቃ ትውልድ ይዳን…’ ብሎ በደሙ ውስጥ ኤች አይ ቪ እንደሚገኝ በአደባባይ ሲናገር በሐገር ቤትም በውጪም ያሉ በርካቶች ጀግንነቱን፣ አርአያነቱን አድንቀዋል፡፡ በጋምቢያ በደሙ ውስጥ ቫይረሱ መኖሩን የተናገረ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡
መገለሉ በከፋበት በዛን ወቅት ይህን ማድረግ ትልቅ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ በቀጠሉት ዓመታትም ሲሴ በኤች አይ ቪ ዙሪያ የሚሰራ ድርጅት አቋቁሞ ወገኖቹን ለመርዳት ላይ ታች ብሏል፡፡

ከ7 ዓመት በኋላ እ.ጎ.አ በ2007 ግን እንድ ወሬ ተሰማ – በ1994 በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ላይ የወጡት የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜ ኤች አይ ቪ/ኤድስን እና መሃንነትን የሚፈውስ ተዐምራዊ መድሃኒት አገኘሁ አሉ፡፡

ዓለም ተሳለቀ – እሳቸው ግን የዚህን ‘እምነተ ቢስ’ ዓለም ስላቅ ወዲያ ብለው ላሚን ሲሴ ለሚመራው በኤች አይ ቪ ዙሪያ ለሚሰራው ማህበር ቀጭን ትዕዛዝ ያዘለ ደብዳቤ ላኩ፡፡

ደብዳቤው፣ ፕሬዝዳንቱ ያገኙትን መድኃኒት ወስደው ይፈወሱ ዘንድ 10 ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን የማህበሩን አባላት በአስቸኳይ እንዲልክ ያዛል፡፡

ሲሴ አሁን ላይ ያን ወቅት አስታውሶ ለቢቢሲው ኮሊን ፍሪማን ሲናገር ደነገጥኩ ይላል፡፡ እንዲያውም ሌሎች የማህበሩ አባላትን መላክ ሁሉ አስቦ ነበር – ግን ደግሞ እሱ ቀርቶ ሌላ ሰው ቢልክ የሚደርስበትን ሲያስብ ፈራ፡፡ ምን ይሻላል ? ግን ደግሞ ብፈወስስ አለ፡፡ ምን ይታወቃል ! መሞከር ነው፡፡ ምን ይመጣል ? አለ፡፡

በመጨረሻ ከሚስቱ እና ከሌሎች የማህበሩ አባላት ጋር የፕሬዝዳንቱን የኤች አይ ቪ/ኤድስ ተዐምራዊ ህክምና ለመውሰድ በፕሬዝደንቱ መኖሪያ ጊቢ ውስጥ እንደነገሩ ወደተቋቋመው ክሊኒክ አመራ፡፡

ክሊኒኩ እንደደረሱ ሕክምናው 6 ወራት እንደሚፈጅና በሕክምናው ወቅት ማድረግ የሌለባቸው ነገሮች ተነገራቸው፡፡ ሲጋራ ማጨስ፣ ሻይም ሆነ ቡና መጠጣት፣ ወሲብ መፈፀም አይቻልም፡፡

የፀረ-ኤች አይ ቪ ቫይረስም ሆነ ሌላ ዘመናዊ መድሃኒት መውሰድም ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ እናም ደግሞ … አዎን …

እናም ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ከሥራ ሥር እና ቅጠላቅጠል የቀመሙትና ከመንፈሳዊ የፈውስ ሥርዓት ጋር የሚሰጠው ተዐምራዊው መድሃኒት’ በሁሉም የሳምንቱ ቀናት ሳይሆን በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ነው የሚሰራው!

ማን ይሆኑ እነዚህ መድሃኒቱ የሚሰራባቸው ሁለቱ የሳምንቱ ቀናት ?
ሰኞ እና ሐሙስ !!!

እነሲሴ ወደ ክሊኒኩ እንደገቡ ሕክምናው እስኪጠናቀቅ ድረስ ላሉት 6 ወራት ያለ ፕሬዝደንቱ ፍቃድ ከክሊኒኩ ውልፍት ማለት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል፡፡ አሁን ሀሳብን ለውጦ ወደ ቤት መመለስ የለም፡፡

ክሊኒኩ በር ላይ ክላሽንኮቭ ጠመንጃቸውን ያነገቡ የያህያ ጃሜ ወይም በሙሉ ሥማቸው ‘የተከበሩ ሼክ ፕሮፌሰር አልሃጂ ዶክተር ያህያ አጅ ጃሜህ ባቢላ ማንሳ’ ወታደሮች በተጠንቀቅ ቆመው ማንም ታካሚ ሳይስፈቅድ ከክሊኒኩ ለቅቆ እንዳይወጣ ይጠብቃሉ፡፡

በነገራችን ላይ … የረጅሙ በማዕረግ የተንቆጠቆጠው ሥማቸው መጨረሻ ላይ ያለው ‘ባቢላ ማንሳ’ የሚለው ማዕረግ ኋላ የተጨመረ ነው – “ዋናው ድልድይ ሰሪ” ወይም “ወንዞችን ያስገበረ” ማለት ነው – ያህያ ጃሜ በጋምቢያ እሳቸው ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ በርካታ ድልድዮችን አሰርቻለሁ ብለው ነው ይባላል ይህን ማዕረግ ለራሳቸው የሸለሙት፡፡

ከዚያ እንግዲህ ፕሬዝደንቱ ‘ተዐምራዊ’ ያሉትን ሕክምና መስጠት ጀመሩ፡፡ ሁሌ ማለዳ ፀሎት እያነበነቡ የበሽተኞቹን ገላ ምንነቱ ባልታወቀው የተጨቀጨቀ አረንጓዴ የቅጠላቅጠልና የሥራ ሥር ውህድ ያሻሉ፡፡ በቀን ሁለቴ ደግሞ በሽተኞቹ በጠርሙስ ውስጥ ካለ ሚስጥራዊ ቢጫ ፈሳሽ እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የወጣው የቢቢሲ ዘገባ እንደሚለው፣ ጃሜ፣ ‘እውን ኤች አይ ቪ/ኤድስን የሚያድን መድሃኒት ካገኙ በእርስዎ ሳቢያ ሐገርዎም በአንድ ቅፅበት ሐብታም ትሆናለች፤ ምን አለበት መድሃኒቱ በገለልተኛ አካል እንዲፈተሽ ቢያደርጉ’ ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡
ጃሜ በእጄ አላሉም፡፡

ፕሬዝደንቱ አገኘሁት ያሉትን ተዐምራዊ ፈውስ የሚጠራጠር ወይም የሚቃወም ብርቱ ቅጣት እንደሚጠብቀው ስለሚያውቅ ሁሉም ፀጥ አለ፡፡ በሕክምናው ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ያሰሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የጤና ጉዳይ ኤክስፐርትም ውለው ሳያድሩ ወዲያው ከጋምቢያ ተባረሩ

ሕክምናውን የሚከታተለው ሲሴ ተቅማጥ ያዘው፡፡ አብሮት ካለ ሌላ በሽተኛ ደግሞ ቲቢ ተጋባበት፡፡ በጣም ሲዳከም ከቤተ መንግሥቱ ውጪ ወዳለ ሆስፒታል ተዛወረ፡፡ ምርመራ ሲደረግለት በደሙ ውስጥ ያለው የቫይረስ መጠን ጣራ ነክቷል – እንደገና ፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት መውሰድ ጀመረ፡፡

ቢሆንም ግን ሲሴ እድለኛ ሳይሆን አይቀርም – ሚስቱን ጨምሮ በርካቶች በዚህ ጃሜ ተዐምራዊ ባሉት ሕክምና ሳቢያ ሞተዋል፡፡ በዓመታት ውስጥ በጃሜ ህክምና አበሳቸውን ካዩ 9 ሺ ያህል ሰዎች መካከል ምን ያህሉ በዚሁ ሳቢያ እንደሞቱ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም የቢቢሰው ኮሊን ፍሪማን እንደሚለው ‘ጃሜ ተዐምራዊ ያሉት ሕክምና ብቸኛው ተዐምሩ ሳይሞቱ መትረፍ ነው’፡፡

ከያህያ ጃሜ ተዐምራዊ የኤች አይ ቪ/ኤድስ የፈውስ ሕክምና ከተረፉት መካከል አንዱ ከእንግሊዙ ሊድስ ዩኒቨርሲቲ በፐብሊክ ሔልዝ ዲግሪ ያለው ኡስማን ሶዌ ነው፡፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖረውን ሶዌን በሕክምናቸው ውስጥ እንዲካተት ማድረግ የምዕራባውያን ጋዜጠኞችን አፍ ያስይዝልኛል ብለው የገመቱት ጃሜህ ወዲያው ነበር የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ሕክምናቸው ግንባር ቀደም ሰውና ቃለ አቀባይ ያደረጉት፡፡

እምቢ ማለት ትርፉ እስርቤት መወርወር መሆኑን የሚያውቀው ሶዌ ከሌሎች ታካሚዎች ጋር ሆኖ ስለሕክምናው ውጤታማነት በጋምቢያ ቴሌቪቭን የአድናቆት መዝሙር ዘምሯል፡፡ ለአንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛም በህክምናው ውጤታማነት ላይ 100 % እርግጠኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡

እርግጥ ነው ይሄን በተናገረበት ወቅት የፀረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒቱን መውሰድ አቁሞ ስለነበር አቅሙ በጣም ተዳክሞ ደረጃ እንኳ የሚወጣው የደረጃውን መደገፊያ ብረት ይዞ ቁና ቁና እየተነፈሰ ነበር ይላል ዘገባው፡፡

‘እንደተማረ ሰው … ነገሩ ተራ ውሸት መሆኑን አውቃለሁ” የሚለው ሶዌ፣ “ቢሆንም ግን ምን ማድረግ እችላለሁ ? ሰዎች እየሞቱ ቢሆንም ደፍሬ ተቃውሞዬን ማሰማት አልቻልኩም’ ይላል፡፡

እግዜር ካለ ቢሊየን ዓመት ብገዛስ ምን ይለኛል ብለው የነበሩት ያያህ ጃሜ የዛሬ ዓመት ግድም ነበር ከ22 ዓመት የስልጣን ዘመን ቆይታ በኋላ በምርጫ ተሸንፈው ስልጣን ላለመልቀቅ ካንገራገሩ በኋላ 50 ሚሊየን ዶላር ዘርፈው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ የኮበለሉት…

አሁን፣ ሶዌ፣ አብረውት በያህያ ጃሜ ህክምና ሳቢያ መከራቸውን አይተው ከሞት ከተረፉት ወዳጆቹ ጋር እና Aids-Free World ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን በተዐምራዊ ተብዬው ሕክምና ሰበብ ለተፈፀመ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሸሽተው ኢኳቶሪያል ጊኒ በተሸሸጉት ያህያ ጃሜ ላይ ክስ ለመመስረት እየጣረ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here