OLYMPUS DIGITAL CAMERA

በዓለም  ካሉት 700 አይነት የባህር ዛፍ ዝርያዎች  ውስጥ 15ቱ ከአውስትራሊያ ውጭ በተፈጥሮ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ በተለይ የታወቁት ነጭ ባሕር ዛፍና ቀይ ባሕር ዛፍ ናቸው።

የኢትዮጵያ ከተማነት ታሪክ በሠፈረበት ‹‹History of Ethiopian Urbanization›› እንደተገለጸው፣ ዳግማዊ ምኒልክ የባሕር ዛፍ ፍሬ አስመጥተው በአዲስ አበባ ከተማ ካስተከሉ በኋላ ይሄ አዲስ ዕጽ አየሩ ተስማምቶት ለከተማዋ የአረንጓዴ መቀነት ይመስል በጥቂት ዓመታት አሸበረቃት።

በ1940ዎቹ ይሄ መቀነት እስከ አርባ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት በመያዙ ‹‹የባሕር ዛፍ ከተማ›› – ኢካሊፐቶፖሊስ (Eucalyptopolis) የተባለ ቅጽል ስምን አትርፎላት ነበር፡፡

በመዝገበ ጥበባት እንደሠፈረው፣ በአሁኑ ወቅት ባሕር ዛፍ ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት ያገኘው  ቶሎ በማደግ አስፈላጊ እንጨት በመስጠቱ፣ የዛፉ ዘይት ለጽዳትና እንዲሁም በራሪ ትንኞችን ለማባረር እንዲሁም ለመግደል መርዳቱ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ለወባ ትንኝ ማደግ ምቹ የሆኑ አረንቋዎችን ለማድረቅ መርዳቱም ይጠቀሳል፡፡

ሆኖም ግን ባህር ዛፍ ከላይ ለተጠቀሱት ዓላማዎች ቢያገለግልም ትልቁ ችግሩ ውሃ በጣም ይወዳል። ስለሆንም እርሱ በተተከለበት ሌሎች አትክልት የማደግ ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ኢትዮጵያም ውስጥ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ምንጮችን እንዳደረቀ መረጃ አለ።

ፕሮፌሰር አማረ ጌታሁን ስለ ኢትዮጵያ ባህላዊ መድኃኒቶች በጻፉት “SOME COMMON MEDICINAL AND POISONOUS PLANTS USED IN ETHIOPIAN FOLK MEDICINE” ድርሳን ውስጥ እንደተጠቀሰው፣ ከባሕር ዛፍ ቅጠሉ የሚገኘው ዘይት ለጉንፋን ፈውስ ይሆናል። ትንኞችንም ለማባረር ይረዳል። ቅጠሎቹ በወለሎች ላይ ለማንጠፍ ያገለግላሉ፡፡

በአውስትራሊያ የሚገኝ የ‹‹ንቁ!›› ዘጋቢ ባሕር ዛፍ ምን ያህል ጠቃሚ ነው? (2001) በሚል ርዕስ በጻፈው ሐተታ እንደገለጸው፣ በ1880ዎቹ ዳግማዊ ምኒልክ ደረቅ በሆነችው በአዲሷ ዋና ከተማቸው በአዲስ አበባ ለጥላነትና ለማገዶነት የሚያገለግሉ ዛፎች ለመትከል ፈልገዋል።

ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ ለተካሄደበት ለዚህ አካባቢ ተስማሚ የሆነ አፍሪካ በቀል ዛፍ ማግኘት ባለመቻሉ የንጉሠ ነገሥቱ ጠበብት ቢያንስ ቢያንስ በአገራቸው ያለውን ሐሩር ተቋቁሞ ማደግ የሚችል ዛፍ በሌሎች ቦታዎች ማፈላለግ ያዙ።

‹‹አዲስ አበባ›› የሚለው የከተማዋ መጠሪያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ሚና ለመጫወት የበቃውንና ከባሕር ማዶ የመጣውን ባሕር ዛፍ ከፍ አድርገው በመመልከት ያወጡት ስያሜ ሊሆን ይችላል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here