የአማራ ብሔርተኝነት፣ የትግራይ ብሔርተኝነት እንዲሁም የሌሎች ብሔርተኝነት በዚህ ፈታኝ ጊዜ እንደ መፈክር (motto) ይዞ ማስተጋባት ምን ይሉታል?

በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ለውጥ ያድሳል ተብሎ የሚጠበቀው የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ጉባኤዎች መጨርሻው የምናየው ይሆናል:: ነገር ግን ካሁኑ አንድ የታዘብኩትን ላካፍላቹ እና የእናንተም ትዕዝብት እና ስጋት ከሆነ አስቡበት።

ትላንት ብአዴን ጉባኤው የጀመረበት መሰብሰብያ አዳራሽ ላይ ‹‹የአማራ ብሄርተኝነት ለዲሞክራሲ አንድነት›› የሚል ጽሑፍ በትልቁ ተለጥፎ አየሁኝ።

ከወራት በፊትም መቐለ በሚገኘው የሰማዕታት አዳራሽ ህወሓት ‹‹ብሔርተኝነት ለዲሞክራሳዊ አንድነት››  የሚል ይዘት ያለው መፈክር በትልቁ ለጥፎ አይቻለሁ።

የቋንቋ ችግር ይሆናል እንጂ ኦህዴድ (ኦዴፓ) እና ለሎቹ የኢህአዴግ እህትና አጋር ድርጅቶች እንደዚህ አይነት ሞቶ  መያዛችው አይቀርም።

ልብ በሉ ሁሉም ብሔሮች በማንነታቸው ተከብረው እና ተከባብረው መኖር አለበት ከሚለው ሐሳብ ይለያል። እኔ ለመዋጥ የተቸገርኩት እዚህ ላይ ነው።

እውነት ነው ኢትዮጵያ የየራሳቸው እንዲሁም የሚጋሩት ባህል፣ ቋንቋ፣ አልባሳት፣ ታሪክ ያለቸው የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች ሀገር ናት። ሁላችን ኢትዮጵያዊያን እኛ መርጠን የተወለድንበት ክልል ሆነ ብሔር የለንም።

መጀመርያ ሰዎች ነን ከዛ ሲቀጥል የተወልድንበት እና ያደግንበት ባህል፣ ቋንቋ፣ አልባሳት፣ ታሪክ የሚወክል ማንነት ወይም ብሔር መርጠን ወስደን ሳይሆን ተሰጠን። ሁሉም ባለው ማንነት ደስ ሊለው፣ ልንኮራበት ይችላል እንጂ ልመፃደቅበት አይገባም፤ አይችልምም።

ስለዚህ አንድ ሰውን ስናከብር እስከማንነት (full package) መሆን አለበት። ብሔርተኝነት ማለት የአንድ ግለሰብ ታማኝነት ከሁሉ ዓይነት የግል ወይንም የቡድን ፍላጎት በላይ ለብሔሩ ወይንም ለብሔረ መንግስቱ ነው የሚል ነው።

ቃሉ ወይም ርዕዮት ዓለሙ በራሱ (perse) ፍፁም መጥፎ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉ የአለማችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያራምዱት ርዕዮት ዓለም ነው። እዚህ ላይ የማነሳው የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት አይደለም።

ነገር ግን በአገራችን የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ሰበካ መሬት ላይ ሲዎርድ ግን መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ ከፍ ከፍ በማድረግ የሌሎች ዝቅ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ደግሞም እንደሱ አይነት ምልክቶች ታይተውል።

ይህ ደግሞ የህዝብ መቻቻል ይቀንሳል፣ መከባበር ያጠፋል፡፡ ከዛም አልፎ አንድ ሁለት ሲባል ጥላቻን ይወልዳል።

በተለይ በዚህ ላዕላዊነታችን ሳያስደፈሩ ከባርነት ለመታደግ አባቶቻችን የተዋደቁላት አገር የኢትዮጵያነት እና የአንድነታችን ስሜት በቀዘቀዘበት ዘመን ከሁሉም በላይ ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያዊያን በብሔራቸው ምክንያት ኢ-ሰብአዊ በሆነ መልኩ ተቀጥቅጠው፣ተወግረው በሚሞቱበት ጊዜ ሁሉም ብሔሮች መከባበር አለባቸው ብሎ እንደመሰበክ የአማራ ብሔርተኝነት፣ የትግራይ ብሔርተኝነት፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት እንዲሁም የሌሎች ብሔርተኝነት እያሉ ማስተጋባት ችግራችን መከራችን ያበዛው ይሆናል እንጂ የሚታደገው አይመስለኝም።

በእኔ እምነት ምንም ብሔር ይኑረን ሁላችን ኢትዮጵያዊያን በሰላም እንድንኖር ከተፈለገ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት መስበክ፣ ማስተጋባት ሳይሆን ልዩነታችን ጌጦቻችን እንደሆኑ ማስተማር እና እርስበርሳችን ተከባብረን ተዋደደን እንድንኖር ሁላችን የቤት ሥራችን መስራት ነው ያለብን።

አንዳንድ ሰዎች የኢትዮጵያ አንድነት (እዚህ ላይ አንድነት ሲባል ‘አንድ መሆን‘ ማለት አለመሆኑ ልብ ይለዋል) እንዲመጣ የሚያለያየን ትተን አንድ የሚያደርገን ላይ አተኩረን መስራት አለብን ይላሉ እኔ ግን እላቸዋለሁ፡፡ ዘላቂ የሆነ መከካበር እና መዋደድ እንዲኖረን ልዩነታችን ማቀፍ (embrace ማድረግ) ነው ያለብን።

ልጆቻችን የራስ ብሔር የሚወክል ብቻ ሳይሆን የሁሉም ብሔሮች ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ ማስተማር፣ አልባሳት ማልበስ እንዲሁም ቢያንስ በአመት አንዴ ከምንኖርበት ከተማ ወይም ቀዬ ወጣ ብለን ሌላ የሀገራችን ክፍል ማየት ልጆቻችን፣ ቤተሰቦቻችን ማሳየት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።

አንድ ጅማ ወይም ደብረማርቆስ ወይም ሐረር ወይም በርሐለይ ወይም ሽረ ወይም ጅግጅጋ ወይም አርባምንጭ ወይም ድሬዳዋ ወይም ጋምቤላ ወይም አሶሳ ተወልዶ ያደገ ኢትዮጵያዊ፣ ኢትዮጵያ ሲባል ወደ ጭንቅላቱ የሚመጣለት በዋናነት ተወልዶ ያደገበት ከተማ ወይም ቀዬ ብቻ ነው፡፡ ሌላው የሚያውቀው በካርታ አልያም በወሬ ስለሆነ ከbackground የዘለለ ምስል አይታየዉም።

በአንፃሩ ደግሞ አንዱ ከተማ ተወልዶ ያደገ ኢትዮጵያዊ በትምህርት፣ በስራ ወይም በጉብኝት የተቀሩት ከተሞች እና ያገራችን ክፍሎች የማየት ዕድል ያገኘ እንደሆነ ግን ኢትዮጵያ በተጠራች ወይ ባሰብ ቁጥር እነዛ ያያቸው ቦታዎችና ያቀፍዋቸው ህዝቦች በአይነ ህሊናው ይገርምማቸዋል።

እንደዚ ዓይነት ሰው ማንም ኢትዮጵያዊ ቢያገኝ እንደ ኢትዮጵያዊ እንጂ እንደ አማራ ወይም ትግራዋይ ወይም ኦሮሞ ወይም ጉራጌ ወይም ሶማሌ…. ብቻ አድርጎ አያይም። ይህ ከብዙ ጓደኖቼ እና ከራሴ ልምድ ያየሁት ነው።

እዚህ ላይ ስለነገው የምናስብ ከሆነ ወላጆች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ መምህራን በተለይ የነገው አገር ተረካቢ ልጆችን እና ወጣቶችን ስነምግባር ያላቸው፣ የሁሉም የኢትዮጵያ ታሪኮች፣ ባህሎች፣ አለባበሶች ማስተማር ላይ ትልቅ ሥራ መስራት አለባቸው፤ አለብን።

የመንግስት እና መሪዎቻቸችን ሚናም ከፍ ያለ ነው። እንድ ትምህርት ካሪኩለማችን ቢካተት ለዚህ ጠቃሚ ነው ብየ የማስበው በሁሉም ክልሎች አሁን እየተሰጡ ከሚገኙት ቋንቋዎች ማለትም english, አማርኛ እና የክልሉ ቋንቋ ዉጪ አንድ ወይም ሁለት ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በፍላጎት እንዲወስዱ ማበረታት ጥሩ ነው።

ይህ አንድም የሌላው ቋንቋና ባህል embrace አድርጎ ልዩነታችን ሸክም ሳይሆን ጌጥ መሆኑ ያስገነዝባል፡፡ ከዛም ባለፈ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ምንም የቋንቋ ችግር እና የመገለል ስሜት የትኛውም የኢትዮጵያ ቦታ ሄዶ የመስራት ዕድል ይሰጣልም።

ስለሆነም መንግስትና መሪዎቻችን ብሔርተኝነት ከሚያስተጋቡ አብረን የምንኖርበት ፖሊሲዎች ላይ ቢመክሩበት ጥሩ ይሆናል እላለሁ።

አበቃሁ። በጎደለው ላይ ሙሉበት፣ ከተሳሳትኩ አርሙኝ፣ ካጠፋሁ አፉ በሉኝ።

#ኢትዮጵያዊነት_መከባበር_መዋደድ_ይለምልም #GDT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here