ከሰባት ዓመት በፊት በየዓመቱ ሲከናወን የነበረው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር በቢሾፍቱ ከተማ ዳግም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  አስታወቀ፡፡

ከዚህ ቀደም በውድድሮች መደራረብና የበጀት እጥረት ምክንያት የተቋረጠው ውድድሩ በአሁኑ ጊዜ የጎዳና ላይ ሩጫ ካለው ተፈላጊነት አንፃር ዳግም መመለስ እንዳስፈለገም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው የጎዳና ላይ ውድድር ለብዙ አትሌቶች ተመራጭ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፡፡

ከ2003 ዓ.ም. በኋላ ተቋርጦ የነበረው ውድድር ለአራተኛ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲከናወን የክልል፣ የከተማ አስተዳደርና የክለብ አትሌቶች፣ እንዲሁም በጎዳና ውድድሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡

በሁለቱም ጾታ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡

ውድድሩ ተተኪ የረዥም ርቀት ተወዳዳሪ አትሌቶችን ለማፍራት ከነባር የርቀቱ አትሌቶች ልምድና የውድድር ዕድል እንዲያገኙ፣ ወቅታዊ ብቃታቸውን እንዲፈትሹበት ለማስቻል ዓላማ ያነገበ ነው ተብሏል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከውድድሩ ጎን ለጎን ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሄድም አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here