አለማየሁ አንበሴ

ኢራፓ ከድርድሩ ሙሉ ለሙሉ ራሱን ማግለሉን አስታወቀ

መኢአድ እና ኢዴፓን ጨምሮ በጋራ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለድርድር የቀረቡ 11 ፓርቲዎች፤ በድርድሩ ቀጣይነት ላይ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጡ ሲሆን ኢራፓ በበኩሉ ከድርድሩ ሙሉ ለሙሉ ራሱን አግልሏል፡፡

አስራ አንዱ ፓርቲዎች ከፀረ ሽብር አዋጁ 4 አንቀፆች እንዲሻሻሉ፣ 6 አንቀፆች ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዙ እንዲሁም 5 የሰብአዊ መብት አያያዝ ድንጋጌዎችን የያዙ አንቀፆች እንዲጨመሩ ሃሳብ አቅርበው የነበረ ሲሆን ኢህአዴግ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን “ይታያሉ” በሚል መቀበሉንና ይጨመሩ ከተባሉትም በተለይ መርማሪዎች በተጠርጣሪዎች ላይ የመብት ጥሰት ሲፈፅሙ በህግ የሚጠየቁበት አንቀፅ እንዲካተት የቀረበውን ጥያቄ መቀበሉን የፓርቲዎቹ ዋና ተደራዳሪ አቶ ሙሉጌታ አበበ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

“የሽብር ድርጊት ለመፈፀም የዛተ” የሚለውን የህጉን ድንጋጌ ጨምሮ የፋክስ፣ ስልክና ሌሎች የግል መልዕክት ልውውጦችን መጥለፍ የሚፈቅደውን አንቀፅ እንዲሰረዝ ከጠየቋቸው መካከል መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሙሉጌታ፤ ኢህአዴግ ሁሉንም እንዲሰረዙ የተጠየቁ አንቀፆች፣ አልቀበልም ማለቱን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሰረዝ ከተጠየቁ አንቀፆች መካከልም ፖሊስ ተመጣጣኝ የኃይል እርምጃ ተጠቅሞ የተለያዩ የምርመራ ናሙናዎችን (አሻራ፣ የሰውነት ፈሳሽ የመሳሰሉ) መውሰድ ይችላል የሚለው እንደሚገኝበት የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፤ ይሄም በገዥው ፓርቲ ተቀባይነት አላገኘም ብለዋል፡፡

በቀረቡለት 16 ያህል የሚሻሻሉ፣ የሚቀነሱና የሚጨመሩ አንቀፆች ጉዳይ ላይ ኢህአዴግ ግልፅ አቋም አለመያዙን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፤ በግልፅ የተቀበሉት የሰብአዊ መብት የጣሰን መርማሪ ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ ማዘጋጀት የሚለውን ነው ብለዋል፡፡

ኢህአዴግ ተጠያቂ የሚያደርገውን ህግ አዘጋጅቶ ለማቅረብ መስማማቱንም አቶ ሙሉጌታ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

ተቃዋሚዎች ለድርድሩ ቀጣይነት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ያወሱት አቶ ሙሉጌታ፤ ኢህአዴግ አዋጁ በህግ ባለሙያዎች የሚሻሻለው ተሻሽሎ፣ የሚጨመረው ተጨምሮ ለድጋሚ ውይይት እስከሚቀርብ በሌሎች አጀንዳዎች ላይ ውይይቱን እንዲቀጥል ቢጠይቅም ይህ ሃሳብ በተቃዋሚዎች ተቀባይነት አለማግኘቱንና የፀረ ሽብር አዋጁ ሳይሻሻልና አጠቃላይ መግባባት ሳይደረስበት ወደ ሌላ አጀንዳ ማለፍ እንደማይፈልጉ ግልፅ አቋም ማንፀባረቃቸውን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አባል እስረኞች ሳይፈቱ ድርድሩን መቀጠል እንደማይችሉ መግለፃቸውንም አቶ ሙሉጌታ አስታውቀዋል፡፡

ከመኢአድ፣ ከመድረክ፣ ከሰማያዊና ከሌሎች ፓርቲዎች 512 ያህል ፖለቲከኞች መታሰራቸውን የሚጠቁም መረጃ እንዳላቸው የገለፁት አቶ ሙሉጌታ፤ ከእነዚህ መካከል እስካሁን የተፈታ አለመኖሩንና ከመኢአድ ብቻ ከታሰሩ 120 አመራሮችና አባላት መካከል አንድ ሰው ብቻ መፈታቱን አስታውቀዋል፡፡

ኢህአዴግም የፀረ ሽብር አዋጁን በህግ ባለሙያዎች አሰርቶ በድጋሚ ለውይይት እንደሚጠራቸው ቃል መግባቱን አቶ ሙሉጌታ ጠቁመዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ኢትዮጵያውያንን ዒላማ ያደረገ የፀረ ሽብር አዋጅ አያስፈልግም፣ ኢትዮጵያ ለአለማቀፍ ሽብርተኝነት የተጋለጠች እንደመሆኑ አለማቀፍ ደረጃ ያለው ህግ ነው መዘጋጀት ያለበት፤ በሽብርተኝነት የተፈረጁ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ድርጅቶች ጉዳይ በወንጀል ህጉ ቢታይ በቂ ነው” የሚሉ የመደራደሪያ ሃሳቦችን አቅርቦ እንደነበር የገለፀው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) በበኩሉ፤ ሃሳቦቹ ተቀባይነት ባለማግኘታቸውና አካሄዱ ውጤት የማያመጣ መሆኑን በመረዳቱ፣ ሙሉ ለሙሉ ከድርድሩ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here