“ለምንድነው ይህን ሁሉ ሕዝብ ከ’ቆሻሻ’ ሃገራት ይዘን የተቀመጥነው?” ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሕግ አውጭዎች ጋር በነበራቸው ውይይት መናገራቸውን ዋሽንግተን ፖስት የተሰኘው ጋዜጣ ዘገበ።

ይህን ያሉት ከሄይቲ፣ ከአልሳልቫዶር እንዲሁም ከአፍሪካ ሃገራት የሚመጡ ግለሰቦችን በተመለከተ ንግግር ሲያደርጉ ነበር።

ዋይት ሃውስ ሁኔታው መፈጠሩን አልካደም፤ ሌሎች የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃንም ጉዳዩን እየዘገቡት ይገኛል።

“አንዳንድ የዋሽንግተን ፖለቲከኞች ስለሌሎች ሃገራት ሲከራከሩ ይደመጣሉ። ትራምፕ ግን ሁሌም ስለ አሜሪካውያን ነው የሚከራከሩት” ሲሉ የዋይት ሃውስ ቃል-አቀባዩ ራጅ ሻህ መግለጫ ሰጥተዋል።

አክለውም “ትራምፕ እየታገሉ ያሉት ለስደተኝነት ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እና ወደ አሜሪካ የሚመጡ የሌላ ሃገራት ዜጎች ለሃገራችን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበርክቱ ለማድረግ ነው” ብለዋል ቃል-አቀባዩ።

ትራምፕ ሃሙስ ዕለት ከዴሞክራቲክ እና ሪፐብሊካን ፓርቲዎች የተውጣጡ ሕግ አውጪዎች ጋር ስደተኞችን በተመለከተ የጋራ መስማማት ላይ ለመድረስ በተደረገ ውይይት ላይ ነው ይህን ንግግር ያሰሙት።

ዋሽንግተን ፖስት ጨምሮም ትራምፕ “አሜሪካ ስደተኞች መቀበል ያለባት እንደ ኖርዌይ ካሉ ሃገራት ነው” ብለው እንደሚያስቡ ዘግቧል።

ኒው ዮርክ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ ከሦስት ሳምንታት በፊት ባወጣው ዘገባው “የሄይቲ ዜጎች ሁሉም ኤድስ አለባቸው” ሲሉ ወርሃ ሰኔ ላይ መናገራቸውን አስታውቆ ነበር።

ትራምፕ አሁን ላይ ያሰሙት ንግግር ግን ከብዙዎቹ ዘንድ ወቀሳ እንዲያስተናግዱ አድርጓቸዋል።

ኤላያህ ከሚንግስ የተሰኙ ዴሞክራት በትዊተር ገፃቸው “ይህ ይቅር የማይባል የፕሬዚደንቱና የቢሯቸውን መግለጫ በእጅጉ እቃወማለሁ” ሲሉ አስፍረዋል።

ብቸኛዋ ትውልዷ ከሄይቲ የሆነው አሜሪካዊቷ ሪፐብሊካን የኮንግረስ አባል ትራምፕ ለዚህ “ክፉ፣ ከፋፋይ እና አስተዋይነት ለጎደለው” ንግግራቸው ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ቢሆንም የትራምፕ ዋይት ሃውስ ስለሁኔታው ቀጥተኛ የሆነ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

አሁን ላይ አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የሌሎች ሃገራት ዜጎች ከሃገር የመባረር እጣ ሊጠብቃቸው እንደሚችል እየተዘገበ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here