ብሄራዊ ስሜትንና ሃገራዊ አንድነትን የሚሰብኩ የሙዚቃ ግጥሞችን በመጻፍ የሚታወቀው ገጣሚ ቢኒያም ሃይለስላሴ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።

ቢኒያም ከመቶ በላይ ግጥሞችን የጻፈ ሲሆን፥ ሃገራዊ ህብረ ቀለምን በስነ ግጥም ውበት በመስጠት ይታወቅ ነበር።

ልክ እንደ ብሄራዊ መዝሙር ሁሉ ስለ ሃገር የሚጻፉ ግጥሞች ደግሞ ከብዙዎች አዕምሮ አይጠፋም።

ከነዚህ መካከል ብሄር ብሄረሰቦች፤ ከፍ ከፍ እንበል የሚሉት ግጥሞች ይገኙበታል።

ብሄራዊ ስሜትን ከመቀሰቀስ ባለፈ የሙዚቃ ግጥሞቹ አሸናፊነትንም የሚያነሳሱ ናቸው።

ቢኒያም በተለይም አባይ ወይስ ቬጋስ ለሚለው ፊልም ማጀቢያነት የሰጠውና በጎሳዬ የተዜመው ኢትዮጵያዬ የሚለው ግጥሙ እንዲሁም በዚያው ፊልም ማዲንጎ የተጫወተው አባይ ወይስ ቬጋስ ተወዳጅ ስራዎቹ ናቸው።

ከግጥም ስራዎቹ ባሻገርም በተለያዩ ትያትር ቤቶች አሻራውን ያሳረፈው ቢኒያም፥ በሀገር ፍቅር ትያትር በስራ አስኪያጅነት እና እስከ ህልፈቱ ድረስ ደግሞ በራስ ትያትር ስራ አስኪያጅ ሆኖ በማገልገል ላይ ነበር።

ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ገጣሚ ቢኒያም የቀበር ስነ ስርዓቱ ዛሬ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here