ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ አቃቤ ህግ ክስ ሊመሰርትባቸው የነበረው የእነ ጥላሁን ጌታቸው የምርመራ መዝገብ በድጋሚ ለመርማሪ ፖሊስ አስረከበ።

አቃቤ ህግ በእነ ጥላሁን ጌታቸው የምርመራ መዝገብ ላይ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆበት የነበረ ሲሆን፥ ሆኖም ግን በምርመራ መዝገቡ ላይ መሟላት ያሉባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው ነው መዝገቡን በድጋሚ ለፖሊስ ያስረከበው።

መርማሪ ፖሊስም አቃቤ ህግ እንዲሟላ የጠየቀውን የቦምቡ ፍንዳታ ጉዳይ፣ የተጎጂዎችን ቃል እና የተጠርጣሪዎቹን የስልክ ልውውጥ የድምፅ ማስረጃ ለማካተት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል።

በዛሬው እለት የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተረኛ 1ኛ የወንጀል ችሎት የተጠርጣሪ ጥላሁን ጌታቸው እና የብርሃኑ ጃፋርን ጉዳይ ተመልክቷል።

በችሎቱም አቃቤ ህግ “ከዚህ በፊት ክስ ለመመስረት ጊዜ የተሰጠኝ ቢሆንም፤ ክስ ለመመስረት አጠቃላይ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ቃል ለማካተት እና

ከሰኔ 12 2010 ዓ.ም እስከ ሰኔ 16 2010 ዓ.ም የተደረገውን የስልክ ልውውጥ

ከዚህ በፊት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ቢሮ ያላከተተው ስለሆነ፤ ይህ ተካቶ እንዲቀርብ ለመርማሪ ፖሊስን ጠይቄያለሁ” ሲል ለፍርድ ቤቱ አሳውቋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ “አቃቤ ህግ የጠየቀውን አሟልቶ ለማቅረብ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ” ሲል ጠይቋል።

የአቶ ብርሃኑ ጃፋር ጠበቃ በበኩላቸው ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱን በመቃወም፤

ከዚህ በፊት መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቅቄያለሁ በማለት ካስረከበ በኋላ አሁን ላይ ጊዜ ሊሰጥ አይገባም በማለት ተጠርጣሪው በዋስ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪው ቦምብ በመኪና ጭነው አቅርበዋል በሚል በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ)

አስደግፈው የሚዘግቡ ሚዲያ ሚዛናዊ ዘገባ እንዲዘግቡ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲሰጥም ጠይቀዋል።

2ኛ ተጠርጣሪ አቶ ጥላሁን ጌታቸው በአስተርጓሚያቸው በኩል፥ “በተደጋጋሚ ለምርመራ እየተባለ ተጨማሪ ጊዜ ሊጠየቅ አይገባም፤

በታሰርኩበት ማረፊያ ቤት ነፃነት የለኝም፤ ለህክምና ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል በስልክ ስለምጠራ ስልክ ባለመኖሩ ህክምና መከታተል አልቻልኩም” ብለዋል።

ስለዚህ በነፃ እንዲወጡ አሊያም በዋስ ሊለቀቁ እንደሚገባም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሎስ እና አቃቤ ህግ በጋራ ዋስትናውን እንደሚቃወሙ ገልፀዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፤

ከመዝገቡ ውስብስብነት አንፃር የኢትዮ ቴሌኮም የድምፅ ማስረጃ እና የተጎጂዎች ቃል እንዲሟላ ለፖሊስ ተጨማሪ የ7 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

የተጠርጣሪ ጥላሁን ጌታቸውን ህክምናን በመተመለከተ ፖሊስ ህክምናውን እየተከታተለ እንዲያደርስ

እንዲሁም ማንኛውም ሚዲያ የተጠርጣሪዎችን የችሎት ውሎ በሚዛናዊነት እንዲዘግቡም አዟል።

በተያያዘ ዜና ባሳለፍነው ቅዳሜ ፍርድ ቤቱ እነ አብዲሳ ቀነኒን ጨምሮ የ5ቱ ተጠርጣሪዎች የተጠናቀቀው

የምርመራ መዝገብ በተመሳሳይ የተጎጂዎች አጠቃላይ ጉዳት እና የኢትዮ ቴሌኮም ማስረጃ እንዲሟላ የ7 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ሰጥቷል።

FBC በታሪክ አዱኛ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here