Home ዜና ሰበር ዜና – አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከስልጣናቸው ወረዱ

ሰበር ዜና – አብዲ ሞሃመድ ኡመር ከስልጣናቸው ወረዱ

12189
0

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ፕሬዝድንት የነበሩት አብዲ ሞሃመድ ኡመር

ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው

ኢድሪስ ኢስማኤል ለቢቢሲ ሶማልኛ አረጋግጠዋል።

ከኢድሪስ ኢስማኤል መረዳት እንደተቻለው፤ አብዲ ሞሃመድ ኡመር

ከክልሉ ፕሬዝደንትነታቸው ይነሱ እንጂ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሪ ሆነው ይቆያሉ ብለዋል።

ኢድሪስ ኢስማኤል ጨምረው እንደተናገሩት አህመድ አብዲ ሞሃመድ የቀድሞውን ፕሬዝደንት በመተካት ተሹመዋል።

አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት አህመድ አብዲ ሞሃመድ

አጭር የምስል መግለጫ

አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት አህመድ አብዲ ሞሃመድ

አዲሱ የክልሉ ፕሬዝደንት አህመድ አብዲ ሞሃመድ የሶማሌ ክልል ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ በሞሆን አገልግለዋል።

ከቅዳሜ አንስቶ በጂግጂጋ እና በክልሉ ሌሎች ከተሞች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ የሃገር መከላከያ

ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ክልሉ ገብቶ ሰላም እንዲያስከብር መታዘዙ ከሰዓታት በፊት ይፋ ተደርጎ ነበር።

በስፋት ”አብዲ ኢሌ” በመባል የሚታወቁ አብዲ ሞሃመድ ኡምር

ሰልጣን በፍቃደቸው ወይም ተገደው ስለመልቀቃቸው የታወቀ ነገር የለም።

ባለፉት ቀናት በክልሉ በተከሰተው ሁከት የሰው ህይወት ጠፍቷል እንዲሁም ንብረት ወድሟል።

***

የሶማሌ ክልል የህዝብ ተወካዮች የጋራ ምክር ቤት ባለ7 ነጥብ የአቋም መግለጫ

1 የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በአስቸኳይ ከስልጣን እንዲወርዱ

2 ፌደራል መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰትና ግድያ አስቁሞ

ህዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት እንዲቋቋም

እንዲሁም ወንጀለኞችን እንዲያዙ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ

3 የክልሉ የ2011 በጀት ህዝባዊ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ እንዳይለቀቅ

4 በየ አስርቤት የሚማቅቁ ንጹሃን ዜጎች እንዲፈቱ

5 በኦሮሞና በሱማሌ መሃለ ያሉ ግጭትች እንዲቁሙ

ይህንን ግጭት የሚያስነሱ አካላትን ፌደራል መንግስት ለህግ እንዲያቀርብ

6 የሶማሌ ህዝብ ከዶክተር አብይን ጎን በመቆም ተደምሯል

7 በአሁኑ ሰአት የሶማሌ ክልል ፖሊስ ህዝቡን በማፈን ላይ ነው ይህን ፌደራል መንግስት እንዲያስቂም

***

የኢፌዴሪ መከለከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰላም እንዲያስከብር ትዕዛዝ ተሰጠው

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ህዝብን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በክልሉ እንዲሰማሩ ትዕዛዝ መሰጠቱን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ገለፀ።

ትዕዛዙ የተሰጠው የክልሉ መንግስት ግጭቱንለማረጋጋት ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛል በሚል ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መሆኑም ታውቋል።

መንግስት በክልሉ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ሀዘኑን ገልጿል።

በክልሉ በተፈጠረው ግጭት የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ኮሚቴ መቋቋሙንም የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

Image may contain: 1 person

በጅግጅጋ ግጭት ሸሽተው የተሸሸጉ ሰዎች በከፋ ችግር ላይ ናቸው

ጅግጅጋ

በጂግጂጋ ከተማ ዛሬም የክልሉ ልዩ ኃይልና ከሚፈፀሙ ጥቃቶች ሸሽተው በተሸሸጉ ወገኖች መካከል ግጭት መፈጠሩን የዓይን ዕማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውን የደበቁ አንድ የረድኤት ድርጅት ባልደረባ

ዛሬ ረፋድ ላይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ከተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣

አብያተ ክርስቲያናትና ግብረሰናይ ድርጅቶች የተውጣጡ ተወካዮች እና

የሀገር ሸማግሌዎች ወደ ክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሃመድ ኦማር በማቅናት መወያየታቸውን ገልፀዋል።

በውይይቱ ወቅት ፕሬዚዳንቱ ችግሩ የተፈጠረው የፌዴራል መንግሥት ወታደሮች በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ጨምረውም ቅዳሜ ዕለት በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን ገልፀው፤

ጥፋትና ውድመት ያስከተሉት «የአክራሪ እስልምና ቡድኖች» መሆናቸውንና

ህዝቦች አሁንም በወንድማማችነት እንዲኖሩ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ እንደነገሯቸው አጋርተውናል።

ተወካዮቹ በየአብያተ-ክርስቲያናቱ የተጠጉ ወገኖች በረሃብ እና

እርዛት ውስጥ መሆናቸውን በመናገር የሚቀመስ ምግብ የክልሉ መንግሥት ማደል እንዲጀምር በጠየቁት መሰረት

ዳቦ፣ ተምር እና ውሃ በመኪና ተጭኖ በየአብያተ-ክርስቲያናቱ ተጓጉዟል።

ሆኖም በከተማው ቀበሌ 06 በሚገኘው መሠረተ-ክርስቶስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ የተጠለሉ ወጣቶችና የክልሉ ልዩ ኃይል በምግብ ዕደላው ወቅት መጋጨታቸውን ገልፀዋል።

ከግጭቱ ጋር ተያይዞ የዓይን እማኙ የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በከፈቱት የሩምታ ተኩስ

ሦስት ወጣቶች ተመትተው ሲወድቁ ማየታቸውን ተናግረው

ቢቢሲም በስፍራው ካሉ ሰዎች ይህንን ለማረጋገጥ ችሏል።

የረድኤት ድርጅት ሠራተኛ የሆኑት የዓይን እማኝ እንደሚሉት

የተመለከቱት የምግብ እጥረት አሳሳቢ መሆኑን ሲጠቁሙ

«ጥሬ ማንጎ ለመብላት የሚንሰፈሰፉ ሰዎችን በዓይኔ አይቻለሁ ብለዋል።

የሸሹ ሰዎች ተጠልለውባቸው የሚገኙ አብያተ-ክርስቲኣናትን የተመለከቱ

ሌላ የዓይን እማኝ ደግሞ ነፍሰጡሮችና ሕፃናት በከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ከከተማዋ ለመውጣት ያልቻሉና

ተሸሽገው የሚላስ የሚቀመስ ያጡ ወገኖች የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑንም የዓይን እማኞቹ አክለው ተናግረዋል።

የሚመለከታቸውን የክልሉ ኅላፊዎች በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በሶማሌ ክልል የተለያዩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ ድብደባና ግድያ ተፈፅሟል

 10 የሚበልጡ አብያተ ክርስትያናት ጥቃት ደርሶባቸዋል

በኢትዮጵያ ሶማሌ ሀገረ ስብከት የጅግጅጋ ወረዳ ቤተ-ከህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ኢዮብ ወንድሙ

በክልሉ ሰባት ካህናት መገደላቸውንና ሰባት አብያተ-ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጂግጂጋ ወንጌላዊያን አብያተ-ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ሰብሳቢ ፓስተር ጋሻው ገ/ዮሃንስ

በበኩላቸው እንደተናገሩ ወደ አስር የሚጠጉ አብያተ-ክርስቲያናት የዘረፋ እና እሳት ቃጠሎ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንዶቹ አብያተ-ክርስትያናት ውስጥ በአምልኮ ሥርዓት ላይ የነበሩ

አገልጋዮችና አማኞች ተደብድበዋል።

ሊቀ ካህናት ኢዮብ አክለውም እስካሁን ትክክለኛው ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

ከተቃጠሉት የኦርቶዶክስ አብያተ-ክርስቲያናት ውስጥ በጂግጂጋ ከተማ በ7 ሚሊዮን ብር ወጪ

ተገንብቶ በቅርቡ የተመረቀው የምሥራቀ-ፀሐይ ቅድስት ኪዳነ ምህረት ካቴድራልም ይገኝበታል።

“በዚሁ ግቢ ውስጥ ወደ ሦስት ሰዎች ሞተው እስከሬናቸው ተቃጥሏል፤

አንዱን ጭራሽ መለየትም አልቻልንም። በቅድስት አርሴማም አንድ መሪ ጌታ ሞቶብናል” ብለዋል ሊቀ ካህናት ኢዮብ።

አክለውም የሊቀ-ጳጳሱ መኖሪያም (መንበረ ጵጵስና) በርና መስኮቱ ተገነጣጥለው እያንዳንዱ እቃ መወሰዱንና

ምንም የቀረ ነገር አንደሌለ ነው የተናገሩት።

ሊቀ-ጳጳሱ በወቅቱ ለቤተ-ክርስቲያኒቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ነበሩ።

“መውሰድ የሚችሉትን ወስደው ያልቻሉትን ደግሞ አቃጥለው ነው የሄዱት።”

ከግድያው በተጨማሪ የእርሳቸውንም ጨምሮ የበርካታ ምዕመናን ቤት እየተሰበረ ዘረፋ መፈጸሙንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በክልሉ በተፈጸመው ድርጊት ሳቢያ የሰው ህይወት በመጥፋቱ ሃዘናቸውን መግለፃቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ብፁዕነታቸው ሰባት አብያተ-ክርስትያናት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው የካህናት ህይወት ማለፉንም ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም የሰላማዊ ሰዎች ህይወት ማለፉንና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰው፤ በሁኔታው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል።

ሊቀካህናት ኢዮብ አንድሚሉት በጂግጂጋ ከተማ በሰበካ ጉባኤ አባልነት ሰላሳ ሺህ ምዕመናን ተመዝግበዋል።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሰብአዊ መብት ጥሰት በመኖሩ መንግስት ጣልቃ መግባት አለበት – ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በአሁኑ ሰዓት የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት በመኖሩ

የፌደራል መንግስት ጣልቃ በመግባት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ።

ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ በጅግጅግጋ የሚገኘው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ

ጉዳት እንደደረሰበትና ንብረቶቹም እንደተዘረፉ አስታውቋል።

የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ላይ የደረሰው ጥፋት ሆን ብሎ መረጃ ለማጥፈት የተደረገ እንደሆነም ገልጿል።

ከወራት በፊት የክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች በአካባቢው የሚፈፀመውን

የሰብአዊ መብት ጥሰት መነሻ በማድረግ ምርምራ እንዲደረግላቸው ጠይቀው

ኮሚሽኑ የማጣራት ስራ መጀመሩን በቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ

ለደረሰው ውድመት ዋነኛ ምክንያት ነው ብሏል።

የተቋሙ ኮምፒተሮች የምርመራ ሰነዶች ተሽከርካሪዎች ሳይቀር መዘረፋቸውን ነው የገለፀው።

የተቋሙ መርማሪዎችም ለደህንነታቸው አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጿል።

በክልሉ የሰዎች ተዘዋውሮ የመስራት፣ ሃብት የማፍራት እና

በህይወት የመኖር ህገ-መንግስታዊ መብትም መጣሱን ነው የገለፀው።

በዚህ ምክንያት የፌደራል መንግስት በክልሉ ጣልቃ በመግባት

መፍትሄ እንዲሰጥ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጿል።

ምንጭ – ቢቢሲ አማርኛ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here