የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር ይህ ነው፡፡ ነባሩ አስተሳሰብ፣ አሠራርና መዋቅር አዲሱን ለውጥ ሊሸከም አልቻለም፡፡ ለሺ ዓመታት ያህል ወጥነትን ስናስተናግድ ኖረናል፡፡

ባለፉት መቶ ዓመታት ደግሞ በየዓይነቱን(ውጥንቅጥን) ለማስተናገድ አራት ጊዜ ሞክረናል፡፡ በልጅ ኢያሱ ዘመን፣ በ1966 ዓ.ም.፣ በ1983 ዓ.ም. እና በ1997 ዓ.ም.፡፡ አራትም ጊዜ ከሽፎብናል፡፡

አምስተኛውን ባለፈው ዓመት ጀመርነው፡፡ ያለን አማራጭ ሁለት ነው፡፡ እንደለመድነው ሾተላይ ሆነን ማክሸፍ፣ ያለበለዚያ ደግሞ ለአዲሱ የወይን ጠጅ አዲስ አቁማዳ ማዘጋጀት፡፡

አዲሱን የወይን ጠጅ በአሮጌ አቁማዳ ማስቀመጥ ችግሩ ምንድን ነው? የወይን ጠጁ ሲብላላ ከአቁማዳው ተፈጥሯዊ ቦታ በላይ ይጠይቃል፡፡ አቁማዳውም አዲስ ስለሆነ እየተለጠጠ ይሄዳል፡፡

የወይኑ የመብላያ ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ አዲሱ አቁማዳ የሚገጥመው ተግዳሮት ሁሉ ተሸክሞ እስከ ጽንፍ ይጓዛል፡፡ የወይኑ ሂደት ሲያበቃም አቁማዳው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሶ ደርቆ ይቆማል፡፡

ከዚህ በኋላ አይለጠጥም፡፡ ወይኑን መምጠጥ አይችልም፡፡ ጠጥቶ ጠጥቶ ይጠግባል፡፡

በዚህ ዓይነት መንገድ አገልግሎ የመጨረሻ ደረጃ የደረሰ አቁማዳ ውስጥ አዲስ የወይን ጠጅ ማስቀመጥ አቁማዳውን ከልኩ በላይ እንዲሠራ ማስገደድ ነው፡፡፡

መለጠጥና አዲሱን ሂደት መሸከም ስለማይችል ይተረተራል፡፡ በዚህም ሁለቱም ይጎዳሉ፡፡

ፓርላማው፣ መንግሥት፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ሚዲያ፣ የእምነት ተቋማት አደረጃጀት፣ የሕዝቡ ሥነ ልቡና፣ አሠራርና ቋንቋ የድሮ አቁማዳዎች ናቸው፡፡

አንድ ወጥ አስተሳሰብ፣ አደረጃጀት፣ ፓርቲ፣ መንግሥት፣ እምነትና ሐሳብ በነበረን ጊዜ የተዘጋጁ አቁማዳዎች፡፡ ይህን ውጥንቅጥ ሊሸከሙ አልቻሉም፡፡

አቁማዳው ምንም ያህል አዲሱን የወይን ጠጅ የመያዝ ፍላጎት ቢኖረ፤ ምንም እንኳን የአዲሱ የወይን ጠጅ ተቃዋሚና ጠላት ባይሆን፤ አዲሱን የወይን ጠጅ ግን ሊሸከመው አይችልም፡፡

ፍላጎት እንጂ ዐቅም የለውምና፡፡ እርሱም ይቀደዳል፤ ወይን ጠጁም ይፈሳል፡፡

በየዕለቱ በሚከሠቱት አሳዛኝ ክሥተቶች ማዘንና መቆዘም አቁማዳውን አያድሰውም፡፡ እንዲያውም የበለጠ ያስረጀዋል፡፡ የሚሻለው ለአዲሱ የወይን ጠጅ የሚሆን አዲስ አቁማዳ ማዘጋጀት ነው፡፡

ከለውጡ ጋር የሚሄዱ አዳዲስ መዋቅሮች፣ አስተሳሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ባሕሎች፣ ልማዶች፣ የሚዲያ ቅርጾችና የሕዝብ አመለካከቶች ያስፈልጉናል፡፡

ይህ አሁን የሚታየው ሁሉ በአዲሱ የወይን ጠጅና በአሮጌው አቁማዳ መካከል የተፈጠረው ተፈጥሯዊ ተቃርኖ ውጤት ነው፡፡

ተቃርኖውን መፍታት የሚቻለው በሁለት መንገድ ነው፡፡ ለአሮጌው አቁማዳ የሚሆን የድሮ ወይን መፈለግ፤ ወይም ለአዲሱ ወይን የሚሆን አዲስ አቁማዳ ማዘጋጀት፡፡

በነበርንበት መንገድ እንሂድ ካልን የመጀመሪያው ምርጥ አማራጭ ነው፡፡ ጣዕም የሚቃኘው ዕለት ዕለት አዲስ ነገር በሚሻው የሰው ልጅ ልቡና ነው፡፡

የጣዕም ልኬቱ እየተቀየረ ወይኑ ባለበት ከኖረ ቅርስ እንጂ ሕይወት አይሆንም፡፡ እየቆየም የሰው ልቡና ይለወጥና ወይኑንም አቁማዳውንም ይተወዋል፡፡

ሁለተኛው የተቃርኖ መፍቻ ለአዲሱ የወይን ጠጅ የሚሆን አዲስ አቁማዳ ማዘጋጀት ነው፡፡ ለአዲስ አስተሳሰብ የሚሆን አዲስ የልቡና ውቅር(mind-sets) ማዘጋጀት፡፡ አሁን ያለን ትግል ይህ ነው፡፡

አሮጌውን አቁማዳ በአሮጌው የወይን ጠጅ ሞልተው ያንን እየተጎነጩ እርጅናቸውን መግፋት የሚፈልጉ አሉ፡፡ አዲስ የወይን ጠጅ ጥለው ነገር ግን ለወይኑ የሚሆን አቁማዳ ያላዘጋጁም አሉ፡፡

አሮጌው ወይን የተሻለ ደኅንነትን፣ ሰላምን፣ ጸጥታንና ዕድገትን ያስመዘገበ መስሎ የሚታየው ለወይኑ የሚሆን ተስማሚ አቁማዳ ስላለው ነው፡፡ አዲሱ የወይን ጠጅ ያጣው ነገር ቢኖር ለእርሱ የሚስማማውን አቁማዳ ነው፡፡

በአቁማዳ እጦት አዲሱ ወይን እዚህም እዚያም ፈስሶ ይታያል:: የወይንን ወግ ሳያይ በአያያዝ ችግር እየተደፋፋ ነው፡፡
እንፍጠን፡፡ ለአዲሱ የወይን ጠጅ አዲስ አቁማዳ እናዘጋጅ፡፡ ያለበለዚያ ባለጌ እንደጣለው ጠጅ፣ አዲሱ የወይን ጠጅ ወግና ማዕረግ ሳያይ ተደፋፍቶ መቅረቱ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here