ዛሬ ከሰዓት ከኤርዶጋን ብዙ ተጠብቆ ነበር። የተጠበቀው ግን አልሆነም። የዓለም ዋና ዋና መገናኛ ብዙኃን ካሜራቸውን ወደ ቱርክ የእንደራሴዎች ምክር ቤት የማዞራቸውም ምክንያት ይኸው ነበር፤ ኻሾግጂ።

ፕሬዝዳንት ጣዪብ ኤርዶዋን በዚህ ደረጃ እንዲጠበቁ ያደረጉት ራሳቸው ናቸው።

ከሰሞኑ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “ማክሰኞ ጠብቁኝ፤ የጀማል ኻሾግጂን ግድያ ጥሬ ሐቅ ምክር ቤት ተገኝቼ አፍረጠርጠዋለሁ” አሉ።

እንደተጠበቀው ግን አዲስ ሐቅ ይዘው አልተገኙም። ያም ኾኖ ጠንካራ የሚባል ንግግርን አድርገዋል።

ግድያው በደንብ ታስቦበትና ታቅዶ ስለመፈጸሙ ለእንደራሴዎቻቸው ተናግረዋል።

ሳዑዲ እንደምትለው ኻሾግጂን አፍኖ ለመውሰድ ሳይሆን ለመግደል 15 መቺ ግብረ ኃይል ኢስታንቡል መግባቱን፤ ኢስታንቡል ቤልግሬድ ጫካ አካባቢ ጥናት ማድረጉን አብራርተዋል።

“ታስቦበት መደረጉን ቅንጣት ታህል አንጠራጠርም፤ ጠንካራ መረጃም አለን” ብለዋል ኤርዶዋን።

ፕሬዝዳንቱ ድርጊቱን በቱርክ ምድር የተፈጸመ ዘግናኝ ወንጀል ነው ካሉ በኋላ ቱርክ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ትፈልጋለች ብለዋል።

“ለምን መቺ ግብረ ኃይል በዚያን ቀን ኢስታንቡል መጣ? ይህን ገዳይ ግብረኃይል ማን ላከው?

የኻሾግጂን ሬሳ ምን አደረጋችሁት? ለአገሬው ሰው ሬሳውን ሰጥተናል ብላችኋል፤ ለማን ነው የሰጣችሁት? ሲሉ በማያሻማ መልኩ ጠይቀዋል።

በዚህ አጋጣሚ አንካራ በዚህ አሰቃቂ ወንጀል የተሳተፉትን በሙሉ ተላልፈው እንዲሰጧት ትፈልጋለችም ብለዋል።

ኤርዶዋን በመጨረሻም ለእንደራሴዎቻቸው እንዳረጋገጡት “ቱርክ እውነቱ እስኪወጣ ፍለጋውን ማንም አያስቆማትም” ብለዋል።

የወንጀል ምርመራ ባለሞያዎች እንደሚሉት የኻሾግጂ ሬሳ ተቆራርጦ ከሆነና በአሲድ አልያም በእንሰሳት እንዲበላ ከተደረገ ፍለጋው ከንቱ ሊሆን ይችላል።

ሪያድ ያዘጋጀችው የኢንቨስትመንት ፎረም በጋዜጠኛው ኻሾግጂ ግድያ ምክንያት በርካታ የዓለም መሪዎችና ባለሀብቶች ላለመገኘት ቢዝቱም ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ቀናት ይካሄዳል ተብሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here