ያረጀ ቂም ይዘን ፤ዘላለም ስንደግም፤
ዓለም ጥሎን ሄደ ፤እኛ ስናዘም።

በወጣንበት በር ፣መልሰን ስንገባ፤
ስንት አደይ ረግፎ ፣ስንት ዘመን ጠባ።

ለኛ አልተሰጠም ወይ በይቅርታ መንፃት?
ስለ ፍቅር ሲባል ፣ያለፈን ቂም መርሳት።

መሪው ምረት የለሽ ፤ተመሪው ቅጥ ያጣ፤
በእንቧለሌ መንገድ ፣ማን አርነት ይውጣ ?።

እንዴው የሞኝ ዘፈን ሁል ጊዜ አበባዬ፤
ክፈል ትለኛለች ፤እኔን ያለዳዬ።

እንዴው ልክፈልስ ብል፣ በየትኛው ቁና ፣
መስፈሪያዋም ዐፈር ፣ሰፋሪው ጋር ሆና።

በመንታ ፊት ኑሮ ፣ቀን ይመላለሳል፤
እጅ እየሻከረ ፣እርፍ ይለሰልሳል።
በክንድ አዝል ሃገር ፣ሠው ከእንጨት ይረክሳል፤
እልፍ እየተለፋ ፣እፍኝ ይታፈሳል።

የትልቅ ፀብ ይሆን ፣ያማልዕክት እርግማን፣
መድረስ የተሳነን ፣እንዲህ ባገር አማን ።

ኧረ ምን መዓት ነው ? እንዴት ያል መለከፍ ?
ወንዙን ውሃ በላው ፤እኛ ስንጣለፍ ።
እንቧለሌ ስንዞር፣ ክቡን እንደምጣድ፤
ለእንጀራ እስከመቼ እሣት ላይ እንጣድ ።

ነቅቶ እየቀደመ ፣ኑሮን ካላደሰው ፣
ፀዳሉ ይረግፋል፤የቀንም እንደሰው።

ምስጋና :– ለኑረዲን ዒሣ ይሁን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here