ከሚያብዱት ጋር ከማበድ ይልቅ ከአጥሩ ዘለቅ ብለው አይተው ትውልድን የሚያስጠነቅቁ ሰዎች፣ ሁለት ዓይነት ዕጣ ፈንታ አላቸው፡፡ ወይ እንደ ኖኅ አልያም እንደ ዮናስ፡፡

ኖኅ በምድር ላይ ሊመጣ ያለውን የጥፋት ውኃ ዐውቆ ትውልዱን ለ120 ዓመታት ያህል አስጠነቀቀ፡፡

የዚያ ዘመን ሰዎች (ሰብአ ትካት) ግን ‹ሆዴ ይሙላ ደረቴ ይቅላ እንጂ ሌላው ነገር ሁሉ ምን አገባኝ› ብለው ሲላቸው እርስ በርሳቸው መዋጋት፣ ፋታ ሲያገኙም መብላትና መጠጣት ሆነ ሥራቸው፡፡

የአባታቸው የአዳም ትዝታው ሳይጠፋ ከሁለትና ከሦስት አባቶች ተወልደው አንዱ ሌላውን ለማየት ተጠየፈ፡፡ ከፊሎቹ ጦር ሰብቀው ዘገር ነቅንቀው ነጋ ጠባ ውጊያ ሆነ ኑሯቸው፡፡

ከፊሎቹ ደግሞ የሚሆነውን ሁሉ እንዳላየና እንዳልሰማ አልፈው አሥረሽ ምቺው ሆነ ተግባራቸው፡፡

የሚዋጉትን ላየ በሀገር ጤና ያለው ያለ አይመስልም፤ የሚጨፍሩትን ላየ በሀገር ችግር ያለ አይመስልም ነበር፡፡

ኖኅ በዚህ መካከል ተነሥቶ ሁለቱንም ሲያስጠነቅቅ የሚሰማው አላገኘም፡፡ እየመጣ ያለው መዓት ሊፈስ የተዘጋጀው ቁጣ አስቀድሞ ታይቶት ነበር፡፡

የመንገዳቸው መጨረሻ ገደል፣ የጉዟቸው መዳረሻ እልቂት መሆኑን ተረድቶት ነበር፡፡ ሰሚ ግን አላገኘም፡፡

የሮምን ታሪክ የጻፉ ሊቃውንት ሮም ከመውደቋ ዐሠርት ዓመታት ቀድመው የነበሩ ሮማውያን ሀገራቸው ታላቋ ሮም እየወደቀች መሆኑን ለአፍታም ጠርጥረው አያውቁም ነበር ይላሉ፡፡

የባቢሎን ታላላቆችና ታናናሾች የነቢዩ ዳንኤልን ማስጠንቀቂያ ለመስማትና ከጉዟቸው ገታ ብለው ለማስተዋል ፈቃድ አልነበራቸውም፡፡

ታላቋ ባቢሎን ትወድቃለች ብለው ለአፍታም ጠርጥረው አያውቁም፡፡

ድንገት ግን በ539 (ቅልክ) በአንድ ሌሊት፣ ያውም ባቢሎናውያን ቅልጥ ባለ  ግሥ ላይ እያሉ፤ የፋርሱ ቂሮስ ከተማቸውን በእጁ አስገባት፡፡

የታላቋ ባቢሎንም ክብር በዚያው ሌሊት ተጠናቀቀ፡፡

ኖኅ 120 ዓመታት ተናግሮ ሰሚ አላገኘም፡፡ ዘመኑ ሲረዝም ውድቀቱ የቀረ እየመሰላቸው ይበልጥ ተዘናጉ፡፡

እርሱም የሚሰማው ቢያጣ ለእርሱና ለቤተሰቡ መርከብ አዘጋጀ፡፡ ከእንስሳት ሁለት ሁለት አስገብቶ መርከቡን ዘጋ፡፡ 120 ዓመት ተናግሮ ቤተሰቡን ብቻ ነው ያተረፈው፡፡

በ120 ዓመቱ መጨረሻ ግን የተፈራው የጥፋት ውኃ መጥቶ ዓለምን አጥለቀለቃት፡፡ ስምንት ሰው ብቻ ሲተርፍ ዓለም በንፍር ውኃ ጠፋ፡፡

ከክርስቶስ ልደት በፊት በ8ኛው መክዘ የነበረው ነቢዩ ዮናስ በዘመኑ ልዕለ ኃያል ወደነበረችው ወደ አሦር ዋና ከተማ ወደ ነነዌ ተላከ፡፡

የሀብት ብዛት የሥልጣን ትዕቢትና ጥጋብ የነፋቸው ነነዌያውያን ለያዥ ለገራዥ አስቸግረው ነበር፡፡

ራሳቸውን እንደ ምርጥ ዘር እየተመለከቱ፣ ሁሉ ለእኛ ሁሉም ወደ እኛ አሉ፡፡ ከዚያ በፊት በምድር ላይ ተሠርቶ የማያውቅ ግፍ በከተማቸው ውስጥ ይሠራ ነበር፡፡

ዮናስ ወደ አሦር ሄዶ ለሦስት ቀናት ያህል የነነዌን ጥፋት እየተነተነ ሕዝቡ እንዲመለስ አስተማረ፡፡

ዮናስ ዕድለኛ ነው፡፡ 100 ሺ የነነዌ ሕዝብ በዙፋን ላይ ካለው ንጉሥ በወፍጮ እግር እስካለቺው አገልጋይ ድረስ አሜን ብለው ተቀበሉት፡፡

ከጥፋቱ መንገዳቸው ተፀፅተው ተመለሱ፡፡ መዓቱም በሦስት ቀን ሱባኤ ተመለሰላቸው፡፡

ማኅበረሰባዊ ዕብደት የሚያስከትለው ቀውስና ጥፋት ታይቷቸው እንደ ኖኅና እንደ ዮናስ የሚያስጠነቅቁ ሰዎች ዕጣ ፈንታቸው ሁለት ነው፡፡ የሚረዳቸው ካገኙ እንደ ዮናስ ሕዝቡን ያተርፋሉ፡፡

የማይረዳቸው ሕዝብ ከገጠማቸው ደግሞ እንደ ኖኅ ራሳቸውን ያተርፋሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ትርፍ ባተረፉት ሰው መጠን አይመዘንም፡፡

ኖኅ ያተረፈው ራሱንና ቤተሰቡን ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በልዩ ሁኔታ እሰማቸዋለሁ ካላቸው ሦስት የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን(ኖኅ ኢዮብና ዳንኤል፣ ሕዝ.14÷14) መካከል አንዱ ነው፡፡

ለምን የተባለ እንደሆን የእርሱ ድርሻ መናገርና ማስጠንቀቅ እንጂ እንዲሰሙና እንዲጠነቀቁ ማድረግ አይደለምና፡፡

በዓለማችን ላይ እውነትን ተናግረው አንዳንዴም ከማኅበረሰቡ በተቃራኒ ቆመው የሚያስጠነቅቁ ሰዎች፣ የሚያመሳስላቸው ጠባይ፣ ራሳቸውን በሰማዕያኑ ቁጥር አለመለካታቸው ነው፡፡

እዚህ ባይሰሙ እዚያ፣ ዛሬ ባይሰሙ ነገ እንደሚሰሙ ያውቃሉ፤ ያምናሉ፡፡ ፈጽመው የሚሰማቸው ቢያጡ እንኳን እንደ ኖኅ ራሳቸውን ያተርፋሉ፡፡

ድርሻቸውን ተወጥተዋል፤ ያቅማቸውንም አድርገዋልና በአካለ ሥጋም ሆነ በዐጸደ ነፍስ ፀፀት የለባቸውም፡፡ እንዲያውም ሕዝቡ በኋላ ይፀፀታል፡፡

የሰማይ መስኮቶች የምድርም ቀላያት ተከፍለው፣ የጥፋት ውኃው ምድርን ሲያጥለቀልቃት፣ የኖኅ ዘመን ሰዎች ባለመስማታቸው ተፀፅተው ነበር፡፡ አልጠቀማቸውም እንጂ፡፡

የዛሬ 600 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ እየጠሠራ ያለው ግፍ አይቶ ዝም ማለት ያልፈለገው እጨጌ ፊልጶስ ከሕዝቡም ከነገሥታቱም ጋር ተጋጨ፡፡ እውነቱን ለመስማት ፈቀደኞች ጥቂት ነበሩ፡፡

የገዛ ገዳሙ እንኳን እምቢ አለቺው፡፡ መጠጊያ ከለከለቺው፡፡ እርሱም እውነትን ይዞ ተሰድዶ ደቡብ ጎንደር ስማዳ ደብረ ዕንቁ ገባ፡፡ እዚያም ዐረፈ፡፡

እርሱ ካረፈ በኋላ ግን እርሱ የተናገረው እውነት መሆኑን ነገሥታቱም ሕዝቡም ገባቸው፡፡ ባለመስማታቸው መከራውን ተቀበሉት፡፡

በመጨረሻም ባረፈ በ140 ዓመቱ በዐፄ እስክንድር ዘመን፣ ዐጽሙ ከደብረ ዕንቁ ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር ተመለሰ፡፡

ደራሽ ውኃ እንደ ፈረሰኛ ሲወርድ፣ እኔ እየነጎድኩ ለምን እርሱ ይቆማል ብሎ የቆመውን ዛፍና ድንጋይ ሁሉ እየገነደሰና እየነቀለ እንደሚወስደው ሁሉ፤

ማኅበራዊ ዕብደት ተከሥቶ ሁሉም ቀልቡን ጥሎ ሲከንፍ፣ ቆም ብሎ የሚያስተውልን ሰው ጠርጌ ካልወሰድኩህ ብሎ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡

እንዲያ ባለው ዘመን አቋምና እምነትን አጽንቶ፣ ለነፋሱ ቅጠል ለወፍጮውም እህል እንዳለመሆን ያለ ከባድ ፈተና የለም፡፡

እንዲህ ባለው ጊዜ በርታና ጩኽ፤ እውነቱንም ተናገር፡፡ ከቻልክ እንደ ዮናስ ሕዝብ ታተርፋለህ ካልቻልክ ግን ቢያንስ ራስህን ታወጣለህ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here