በቤኒሻንጉል ክልል የዞን፣ የወረዳ አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች ላይ በተከፈተ ተኩስ የ4 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ ከ75 ሺ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

በበሎይ ጅጋንፎይ ወረዳ ስር ሳይ ዳለቻ ቀበሌ ግጭት የነበረ ሲሆን በግጭቱም 75 ቤቶች ተቃጥለዋል ብለዋል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አበራ ባይታ።

በዚሁ ወረዳ ጅጋንፎይ ቀበሌ በጭበጭ በምትባል አካባቢ ላይ ቤቶች መቃጠላቸውን ጠቅሰው ሌሎች ቀበሌዎችም ላይ ተመሳሳይ ግጭቶች መከሰሰታቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ተናግረዋል።

የተፈናቀሉት ሰዎች ከቤንሻንጉል ብቻ ሳይሆን ክልሉን ከሚያዋስኑት የኦሮሚያ ቀበሌዎችም እንደሆነ የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ሳስጋ ወረዳ ዱራበሎ፣ ካምፕ፣

በሎበሬዳ፣ ስምንተኛ ከሚባሉት ቀበሌዎች በስጋት ምክንያት ወደ ነቀምትና በሎበሬዳ ወደሚገኙ ማዕከሎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮቹ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉ ደግሞ የነቀምትና አካባቢዋ ነዋሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ ነው።

ቢቢሲ ያነጋገረው ኤርጋማ ታምራት ብርሃኑ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን እስካሁን ለ1000 ተፈናቃዮች ምግብና መጠጥ እያቀረቡ እንደሆነ ተናግሯል።

”ሙሉ የቤተሰቡ አባላት ልጆቼንም ጨምሮ ምግብ እያቀረብንላቸው ነው። ባለቤቴ ምግቡን ትሰራለች፤ እኔ ደግሞ አንዳንዴ ምሳ እንኳን ሳልበላ ወንድምና እህቶቼን እያስተናገድኳቸው ነው።” ይላል።

ይሁን እንጂ አሁንም በመንግስት በኩል ትልቅ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውና የወለዱ እናቶች እንኳን ልጆቻቸውን ይዘው ቀዝቃዛ የሲሚንቶ ወለል ላይ እየተኙ ነው በማለት ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ያብራራል።

በተጨማሪም የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ወይም ቄሮዎች እርዳታ እያደረጉላቸው እንደሆነና እነሱ ሰብስበው ያመጡላቸው ልብስ ባይኖር ለብሰውት እንኳን የሚያድሩት ነገር እንደሌላቸው ነግሮናል።

የአርጆ ደዴሳ ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞችም ከደሞዛቸው በመቀነስ 500 ሺ ብር፣ በነፍስ ወከፍ ከሚሰጣቸው በመቀነስ 62 ኩንታል ስኳር መለገሳቸውንና ፋብሪካው ደግሞ

ተጨማሪ የ100 ሺ ብር ድጋፍ ማድረጉን የህዝብ ተሳትፎና ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ፋንታሁን ተናግረዋል።

የምስራቅ ወለጋ የአደጋ መከላከልና ቁጥጥር ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዱኛ ገለታ በበኩላቸው ከክልልና ከፌደራል መንግስት ድጋፎች ቶሎ እንዲያገኙ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስም ከፌደራል መንግስት 800 ኩንታል ስንዴ እንደደረሳቸውና እርዳታ የጫኑ ተጨማሪ 8 ተሽከርካሪዎች በመንገድ ላይ መሆናቸውን አክለዋል።

የምግብ ዘይትም ቢሆን ለተፈናቃዮች እየታደለ እንደሆነና የተለያዩ እርዳታ የሚሰጡ ኮሚቴዎች ተቋቁመው የህክምና እርዳታ ለተፈናቃዮቹ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

”የምስራቅ ወለጋና የነቀምት ህዝብ እያደረገው ያለው ድጋፍ ትልቅ ነው፤ እስካሁን ድረስ ያለነው ህዝቡ አንዱ ለአንዱ የመድረስ ባህሉ ከፍተኛ ስለሆነ ነው።” ብለዋል ተፈናቃዮቹ።

ያነጋገርናቸው በወለጋ ዩኒቨርስቲ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችም ከእራሱ አልፎ ለሌሎች የሚኖረው ህዝብ በሁሉም መልኩ ህይወታችንን እየታደገልን ነው ብለዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here