ሰውየውን አለማድነቅ አይቻልም። አለማመስገንም የሚሆን አይደለም።

ንግግራቸው እንደማር ይጣፍጣል። የታመመ ልብን ያክማሉ። የጥላቻ መንፈስን ያጠፋሉ።

ፍቅርን ይዘራሉ። መልካምነትን ያበቅላሉ።

ከኢትዮጵያዊነት ንግግርና ስነ ስርአት በተጨማሪ ጎንደር ላይ ጃኖ፤ ባህርዳር ላይ ፊደላችን ያለበትን ከረቫት አድርገው ህዝቡን ከራሳቸው፤ ራሳቸውን ከህዝቡ አቀራርበዋል።

መልካምና ብሩህ ጅማሮ ነው። ይበል።
.
ሰውየው ተችዎቻቸውን ይሰማሉ። ደጋፊዎቻቸው አይተቹ ቢሉም ሰውየው ግን ለተቺዎቻቸው መልስ አላቸው።

እንዲህ ይላሉ “ቃል ይተክላል ቃል ይነቅላል፤ ቃል እንደቀላል ነገር አትዩት፤ ከቃል በኋላ ተግባር ይመጣል፤ አያለሁ እሰማለሁ ቃል ቃል ብቻ ይባላል። ግን ተግባርም አለኮ።

የሃይማኖት አባቶችን አልፈታንም? ይህ ተግባር አይደለም? ተፈቱ የሚለውን ዜና መስማት ቀላል ነው። ለማስፈታት ያለውን መከራ ግን የሄደበት ያውቀዋል።

” ሰውየው ይሰማል ያያል። ከዚህ በፊት “ቂጡን ብንወጋው፣ ጣቱን ብንቆርጠው፣ ወራዳ፣ ውሻ፣ ሌባ፣ ገረድ” እያሉ የሚመሩ መሪዎች ነበሩን።

አሁን ግን “ቆንጥጡኝ፤ አባ ጸልዩልኝ፤ የደሃ ገበሬ ልጅ ነኝ፤ ኦሮሞ ነው ብላችሁ አታስቡኝ ይልቁንስ እጄን ስማችሁ ሙርቁኝ” የሚል መሪ አግኝተናል።

“ሺህ አመት ንገስም ቢባል በአንደበቱ ደፍሮ “አይ ይቅርብኝ” የሚል መሪም አግኝተናል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here