ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኽኝ አባተ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቱሪስቶች አገሪቱን ለማስጎብኘትና 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ነበር።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቱሪስቶች መካከል 756 ሺህ 758 ቱሪስቶች ጎብኝተዋታል።

ከዚህም ከ2 ነጥብ 8 የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንና ከታሰበው 75 በመቶ ያህል መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዕቅዱ አንጻር ውጤቱ አመርቂ እንዳልሆነ ገልጸው ለዚህም ባለፉት ጊዜያት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የሰላምና ያለመረጋጋት ችግር ተጽእኖ አሳድሯል ነው ያሉት።

ለተከታታይ ሶስት ዓመታት የጎብኚዎችን ቁጥር አንድ ሚሊዮን ለማድረስ ቢታሰብም በተለያዩ ምክንያቶች እቅዱ ግቡን ሊመታ እንዳልቻለ ይናገራሉ።

የቱሪዝሙን ዘርፍ ይበልጥ ለማሳደግ በመዳረሻዎች ላይ መሰረተ ልማት፣ ሆቴሎችና ሌሎችንም በማልማት ለቱሪስቱ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ ሊጠናከር ይገባል።

ለዚህም ህብረተሰቡ በስራ ዕድል፣ በማልማትና የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ እገዛ በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በ2008 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከጎበኙ 910 ሺህ 128 ቱሪስቶች 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ደግሞ ከ886 ሺህ 897 ቱሪስቶች 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here