በቻይና ከ140 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በእስር ቤቶች ይገኛሉ

በታንዛያ እስር ቤቶች የሚገኙ 200 ኢትዮጵያውያንን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ የበጀት እጥረት ማጋጠሙ ተሰማ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከታንዛኒያ መንግሥት ጋር በመደራደር 96 ኢትዮጵያውያን እስረኞችን ወደ አገራቸው እንዲገቡ ማድረግ ቢቻልም፣ ቀሪዎቹን 200 እስረኞች ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ ግን እስካሁን አልተቻለም፡፡

እስረኞቹ በሞያሌ የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው በኬንያና በታንዛኒያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲሉ የተያዙ ናቸው፡፡

የታንዛኒያ መንግሥት እስረኞቹን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ቢሆንም፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበትን የትራንስፖርት ወጪ የሚሸፍን ባለመገኘቱ በያሉባቸው እስር ቤቶች እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ያለውን የትራንስፖርት ወጪ የሚሸፍነው ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ነበር፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ለዚህ ዓመት የያዝኩት በጀት ጨርሻለሁ ብሏል፡፡

ስለዚህ እ.ኤ.አ. በ2019 የሚለቀቀውን በጀት ጠብቄ በዕቅድ አከናውናለሁ ብሏል፤›› ያሉት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎች ድጋፍና ክትትል ባለሙያው አቶ አስቻለው ከበደ ናቸው፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በታንዛኒያ ከተከፈተ ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያውያኑ ከእስር እንዲፈቱ ያደረጉትን ጥረት በበጀት ጉዳይ መስተጓጎል የለበትም፡፡

አይኦኤም በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢጠየቅም መፍትሔ ማግኘት ባለመቻሉ አቅም ያላቸውን የእስረኞችን ቤተሰቦች በስልክ በማግኘት ትኬት ቆርጠው እንዲልኩ የማድረግ እንቅስቃሴ ለመጀመር ታስቧል፡፡

ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ዘላቂ መፍትሔ መሆን አልቻለም፡፡ ‹‹ቤተሰቦቻቸው ትኬት መክፈል ስለማይችሉ ነው በባህር የሚሄዱት፤›› የሚሉት አቶ አስቻለው፣

አብዛኞቹ ወላጆች ትኬት የመግዛት አቅም እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ ከዚህም በላይ አብዛኞቹ አድራሻም ሆነ ተያዥ የሌላቸው ስለሆኑ፣

ቤተሰቦቻቸውን አፈላልጎ ማግኘት ከባድ መሆኑን፣ ከ14 ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎች ከእስረኞቹ መካከል እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

‹‹ያለን አማራጭ ሁለት ነው፡፡ አንደኛ አይኦኤም በጀት አጠጋግቶም ቢሆን የራሱን ሕግ ጥሶ እንዲረዳን መለመን ነው፡፡

ከዚያ ውጭ ለዜጎች የሚቆረቆሩ አገር በቀል ድርጅቶችና አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች የቻሉትን ያህል እንዲረዱን ማድረግ ነው፡፡ አንድ ሰው የሁለት ሰው ትኬት ቢችል ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡

ቅድሚያ ለሕፃናትና ለሴቶች እየሰጠን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የበጀት ችግር ያጋጠመው ለአየር ትኬት ወጪ መሆኑን፣ ቀሪውን የጉዞ ሰነድ ወጪዎች በውጭ ጉዳይና በኢሚግሬሽን በኩል መሸፈኑን፣

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመነጋገር የትራንስፖርት ወጪውን መቀነስ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደታሰበም አቶ አስቻለው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ እስረኞችን የማስፈታት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ አስቻለው፣ ባልተለመደ ሁኔታ በሩቅ ምሥራቋ ቻይና ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እየተንገላቱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ዕድል አግኝተሃል ወይም አግኝተሻል ተብለው ከኢትዮጵያ እየተጠሩ የሚሄዱ ወጣቶች አደጋ እያጋጠማቸው ነው ያሉት አቶ አስቻለው፣

በቻይና ፈጽሞ የሌሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ስም እየጠቀሱ የትምህርት ዕድል እንዳገኙ በማድረግ ኢትዮጵያውያን ወደ ቻይና የሚልኩ ደላሎች በዝተዋል ብለዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ ባገኙዋቸው የትምህርት ዕድሎች በቻይና በሚገኙ ኮሌጆች እየተማሩ የሚገኙትንም ቢሆን ‹‹እየተማርክ መሥራት ትችላለህ/ሽ፡፡ ያልፍልሃል/ሻል፤›› በማለት

እያባበሉ በሕገወጥ የዕፅ ዝውውር እንዲሰማሩ የሚያደርጉም ደላሎች በቻይና የኢትዮጵያውያኑን ሕይወት እያመሰቃቀሉት ይገኛሉ፡፡

የታሰረ ነገር እየሰጧቸው ይህንን እዚያ ጋ አድርስልኝ  የሚቀበል ሰው አለ እያሉ ሳያውቁት ተማሪዎቹ ዕፅ በማዘዋወር ተግባር ውስጥ እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው፤›› የሚሉት አቶ አስቻለው፣

ይህንን የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን አስቀድመው ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና የሚሄዱ ዜጎችን ስምና የኋላ ታሪክ በማጥናት እንደሚያጠምዷቸው ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ሲነሱ ጀምሮ እንደሚከታተሏቸው የሚናገሩት ባለሙያው፣ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዕፅ አዘዋዋሪዎች ‹‹ከእንጀራ ውጪ የማይበላ ወንድም አለኝ፡፡

እባክሽ ይህንን አድርስ/ሽለት ብለው የተወቀጠ ጫት የተወሸቀባት የእንጀራ ጥቅሎች ይሰጧቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

ሳያውቁት በዚህ ተግባር ውስጥ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በቻይና እስር ቤቶች እየተንገላቱ መሆናቸውን፣

በአሁኑ ወቅት በቻይና ውስጥ ከ140 በላይ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዳሉ፣ ሁሉም ለትምህርት የሄዱ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

በቻይና ሕግ ጫት ይዞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ይፈረድበታል፡፡

እስካሁን ጥቂት የማይባሉት እንደተፈረደባቸውና ቀሪዎቹ በፍርድ ሒደት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

ለትምህርት የሚወጡት ኢትዮጵያውያን ከቻይና ለመመለስ የትኬት ወጪ እንደማይቸገሩና አቅሙ እንዳላቸው፣

ነገር ግን ከኢትዮጵያ ከመውጣታቸው በፊት የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን በሚገባ አጣርተው የትኛው ዩኒቨርሲቲም እንደሚቀበላቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸው አቶ አስቻለው አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሳይፈረድባቸው እንዳይታሰሩ፣ የሰብዓዊ መብታቸው እንዳይጣስ፣ ከተፈረደባቸውም በላይ እንዳይታሰሩ ኤምባሲው ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here