ትናንት ምሽት በብሄራዊ ቤተመንግስት ለትግራይ ክልል ተወላጅ አርቲስቶች፣ ባለ ሀብቶች፣ ታዋቂ ሰዎች ፖለቲከኞችና ሌሎች ተጋባዦች ከምሽት 12፡00 ጀምሮ ጠ/ሚ/ሩ ግብዣና ነጻ ውይይት አድርገው ከተናገሩት የተወሰዱ አብይ ጉዳዮች :-

ግብዣ በዛ፤ ድግስ በዛ ለሚሉ ሰዎች

‹ድግሶች ሰብሰባዎች ንግግሮች በዝቷል የሚሉ አሉ። እኛ አዲስ ሃሳብ እንዲጀመር የምናዳምጠዉ መልስ የምንሰጠዉና የምናክመዉ ዜጋ አለን፤ስራ እየተሰራ ነው ፡፡›

የሠራተኛ ቅጥር

‹‹አንዳንድ ባለስልጣናት ሠራተኛ ሲቀጥሩ የራሳቸውን ብሔር ሰው መቅጠራቸው መቆም አለበት፤ ፀሐፊ ትግሬ፤ ሹፌሩ ትግሬ፤ ጋርዶቻቸዉ ሳይቀሩ ትግሬ፤ ይህንን መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ሰራተኞች መቀጠር ያለባቸው በብቃታቸው መሆን አለበት››

በጡረታ ስለተገለሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች

‹የተወሰኑ ባለሥልጣናት ስልጣን ልቀቁ ሲባሉ ሞት የሚመስላቸዉ ሰሞኑን ጡረታ እንዲወጡ ሲደረጉ አብዛኛዎቹ አኩርፈዋል፤ አንዳንዶቹ 20 ዓመት ሌላዉ 15 አመት ከሰሩ በኋላ ለተተኪ ቦታዉን መስጠት አይፈልጉም፡፡

በነገራችን ላይ ከአቶ ታደሠ ሃይሌ በስተቀር ጡረታ ከወጡት ባለስልጣናት መሀከል ብዙዎቹ ደስተኛ አይደሉም ።

ሁሉም የግል ሥራ እንዲያገኙ እያደረግን ነዉ። ስልጣን በቃቹ እኔ እያለሁ አትጠየቁም፤ አትታሰሩ ብዬ ነግሬቸዋለሁ››

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በተመለከተ

‹‹ሰሞኑን የኤርትራዉን መሪ ኢሳያስ አፍወርቂን ለማግኘት በሳዉዲ አረቢያ ሸምጋኝነት የሣዉዲዉ ንጉስ ደዉለዉ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሊያገኛኙኝ ነበር፤ የኘሬዛዳንቱ ስልክ አይመልስም፤ ጥረታች ይቀጥላል።›

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ

በቅርቡ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ባለሀብቶች እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ይለቀቃሉ፡፡

ከእነዚህም መሀከል አቶ አንዳርጋቸዉ ፅጌ መፈታት ላይ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይፈታ አይፈታ በሚል ጭቅጭቆች ነበሩ፤

እኔ አልቀበልም፤ ይፈታል፤ እሱ ኢትዮጲያ ላይ አሲሯል ተብሎ ነዉ አንዳርጋቸዉ ፅጌን በማሰራችን ኢትዮጲያ 11 ቢሊዮን ዶላር በላይ አጥታለች ከእንግሊዝ መንግስት፡፡ ጥላቻን ነው ያተረፍነው፡፡ ምንድነዉ የሱ መታሰር ጥቅሙ? እኔ አልሰማማም፤

የሊቢያ ሰማዕታትን በተመለከተ

‹‹በሚቀጥለዉ ሳምንት ወደ ግብፅ እሄዳለሁ፤ ለዲኘሎማሲ እንዳይመስላቹ በሊቢያ ሀገር የታረዱ ወገኖቻችን አስክሬን ለማምጣት ነዉ።

ይሄ እብድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይበሉ ቅድሚያ የምሰጠዉ ለዜጎቻችን ክብር ነዉ። ሰሞኑን በሄድንባቸዉ አገሮች ዜጎቻችን እንዲያከብሩ እንዲለቁ ጠይቀናቸዉ ተቀብለዉናል።››

ሳዑዲ አረቢያን በተመለከተ

‹‹ሳዉዲ የአንድ አመት ነዳጅ ፍጆታ እንደሚሰጡና የሄድንባቸዉ ሀገራት 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚለግሱን ቃል ገብተዋል ።

ይህ ሁሉ የመጣዉ አንድ ስለሆን ነዉ፤ እኔ በ2 ወር ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ የሰራሁት በ2 ዓመት አልተሰራም፤ ከመመሰጋገን ይልቅ አቃቂር ማዉጣትና መተቸት እናበዛለን።

ዛሬ እንዲህ በነፃነት እንድናወራ እንድንጫወት ነዉ የምጠይቀዉ››

እነ ገብሩ አስራትን በተመለከተ

‹‹አቶ ገብሩ አስራት እና ሌሎች ባለስልጣናት መንግስት አገልግለዉ በክብር ለምን አይሸኙም? ልክ ነዉ፤ እነዚህ ከ20 ወይም ከ21 በላይ አይሆኑም፤ ይህንን ለማድረግ መንግስት በጀት የለውም፡፡

ግን እዚህ ያላችሁ ባለ ሃብቶች እና ሌሎች ግለሰቦች ተሰባስባችሁ እነሱን በክብር ለመርዳት አንድ ሚሊዮን አንድ ሚሊዮን ብር ብታዋጡ እኔ እገኛለሁ››

ዶ/ር ነጋሶን በተመለከተ

‹‹ ብዙዎቻቹ በሚዲያ ሰምታቹሁታል፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ቢሮ ጠራሁት፤ ሲመጣ ዘግይቶ ነዉ ፤ታክሲ አጥቼ ነዉ አለኝ፤ ጫማዉ ጭቃ በጭቃ ነው፤ እንዴ ዶ/ር መኪና የለህም ? ስለው፤ እንኳን መኪና ቤቴ ያፈሳል አለኝ፤

ድርጅታችን ኦህዴድን ሰብስቤ እንዴት ለሀገር የሰራን ሰዉ አናከብርም አልኩ፤ በአስቸኳይ መኪና ተገዝቶ ተሰጠዉ፤››

ሚዲያውን በተመለከተ

‹‹ሚዲያ አሁን በዝቷል ጥሩ ነዉ፤ አንዳንድ ሚዲያዎች ስነ -ምግባር የሌላቸዉ አሉ፤ በተለይ በሽተኛ ሚዲያዎች ያሉ ሲሆን ሚዲያ ነፃ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡

ስነ- ምግባር የጎደላቸዉ ቀለብተኛ ሚዲያዎች አሉ፤ እነሱ በህግ የሚጠየቁበት አግባብ እየተበጀ ነዉ።››

ረመዳንን በተመለከተ

‹ከአፋርና ከሱማሌዎች ጋር የአፍጥር ኘሮግራም ይዣለሁ››

አብርሃም ግዛው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here