መስከረም 2011 ዓ.ም. የተሰበሰበው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፣

መንግሥት የሕግ የበላይነትንና የዜጎችን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት ማንኛውንም ሕጋዊ፣ የማያዳግምና ተገቢ ዕርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ዝግጅትና አቋም ላይ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ሕገወጥ የሥርዓተ አልበኝነት እንስቃሴዎችን በመገምገም፣ መንግሥት ሥርዓተ አልበኝነትን ከዚህ በኋላ የሚታገስበትና የሚሸከምበት ትከሻ የለውም ብሏል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ለዜጎች ሕይወት ዋስትና ለመስጠት መንግሥት ማንኛውንም ሕጋዊና የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቆ፣ ይህ ዕርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲልም አክሏል፡፡

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ልዩነትን ለማስፋትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ጠይቋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውንና ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መገኘታቸውን ያስታወቀው ምክር ቤቱ፣ ‹‹በዚህም መላው ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአገሩ ተስፋ እንዲሰንቅና በአገሩ መፃኢ ዕድል ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንዲነሳሳ አድርጓል፤›› ብሏል፡፡

ነገር ግን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ከሕግ የበላይነት ውጪ የማይታሰብ አለመሆኑን አስገንዝቦ፣ ‹‹በለውጥ ውስጥ እንደ መሆናችን መጠን መንግሥት ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ

ሆደ ሰፊነትን ቢያሳይም፣ ይህንን እንደ አቅመ ቢስነት የተመለከቱ የጥፋት ኃይሎች የወጣቱን ስሜት በማነሳሳት የሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱና እየተበራከቱ መጥተዋል፤›› ብሏል፡፡

መሰንበቻውን በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን፣ ይህንን ብጥብጥ በተለያዩ አካባቢዎች ለማስቀጠልና በሶማሌ ክልልና በሌሎች አካባቢዎች የከሸፈባቸውን

ዕቅድ በሌላ ሙከራ ለመቀጠል፣ እንዲሁም በመስከረም መጨረሻ የሚካሄደውን የኢሕአዴግ ጉባዔ ለማደናቀፍ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

‹‹ሁከቱ ከላይ እንደሚመስለው በትንንሽ ችግሮችና ልዩነቶች የሚነሳ ሳይሆን በታቀደ መንገድ የሚከናወን፣ ድብቅ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውና ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ወይም ግጭቶች ሲከሰቱ

እነሱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የማባባስና አገራችንን የማያባራ ግጭት ሰለባ በማድረግ ለውጡን ለማሽመድመድና ለመቀልበስ የሚደረግ ሴራ አካል ነው፤› ሲል ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

በተለይ ወጣቱ በስሜት እየተገፋፋ፣ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ዘራፊዎች መሣሪያ እየሆነ አፍራሽ ወደ ሆነ ድርጊት መምጣቱን መረዳት ይኖርበታል ያለው ምክር ቤቱ፣ ‹‹አውቆም ይሁን ሳያውቅ በሕገወጥ

ድርጊት የሚሳተፍ ወጣትና ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን አውቆ ከጥፋት ድርጊቱ እንዲሰበሰብ መንግሥት ያሳስባል፤›› ብሏል፡፡

‹‹የጥፋት ኃይሎች በሚያደርጉት የመጨረሻ መፍጨርጨር ለጊዜው የታወከው የሕዝብ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ መንግሥት እያረጋገጠ፣ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ የደኅንነት ስሜት ተሰምቶት መንቀሳቀስና መኖር እስኪችል ድረስ፣ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፤›› ሲልም አስታውቋል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ወንጀሎቹን በማቀነባበርም ሆነ ለተቀነባበሩ ወንጀሎች መሣሪያ ሆኖ የተገኘ ሰውም ሆነ በማንኛውም ደረጃ በወንጀል የተሳተፈ አካል፣ ከሕግ ሊያመልጥ እንደማይችልና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ምክር ቤቱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

‹‹በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ልዩነትን በሚያሰፉና ብጥብጥን በሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ የምታደርጉ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃችሁን መሰብሰብ ይኖርባችኋል፤›› ያለው ምክር ቤቱ፣

‹‹በመጨረሻም አሁን ከጀመርነው የሰላምና የዴሞክራሲ የለውጥ መንገድ ማንም ኃይል ሊያደናቅፈን እንደማይችል ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፤›› ሲል መግለጫውን ቋጭቷል፡፡

የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትላቸው ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትር፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም፣

የክልል ፀጥታና ደኅንነት ኃላፊዎች፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አባላት ናቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደግሞ በጸሐፊነት ይሳተፉበታል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here