Medical errors rank behind heart disease and cancer as the third leading cause of death in the U.S., Johns Hopkins researchers say.

በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አልፎ አልፎ ውስብስብ ስህተቶች ሲፈጸሙ ይስተዋላል፡፡ ከስህተቶቹም መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው የታካሚው ኅልፈተ ሕይወት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ኅልፈቱ በበሽታው? ወይስ ከተደረገለት ሕክምና ጉድለት ነው? የሚለውን ለማወቅ ወይም ለመለየት የሚያስችል ምርመራ ማካሄድ ግድ ይላል፡፡ ይህ ዓይነቱንም ምርመራ የሚያካሂደው የተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች የተወከሉበት አካል ነው፡፡

ምርመራውም ያስፈለገው የተከሰቱት ስህተቶች በሚመለከተው አካል ከመጣራቱ አስቀድሞ እንደ ማንኛዎቹም ወንጀሎች ሊታዩ የማይገባ መሆኑን በማጤን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አንድ ታካሚ በተሰጠው ሕክምና ፈውስ አላገኘም ወይም ሕይወቱ አለፈ ማለት የግድ የሙያ ሥነ ምግባር ግድፈት፣ አለበለዚያም የሙያ ብቃት ማነስ አለ ተብሎ ሊወሰድ የማይገባ መሆኑን በመገንዘብም ጭምር ነው፡፡ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት በሚስተዋልባት ኢትዮጵያ ውስጥ በሕክምናው ዘርፍ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ሊያስቸግር ይችላል፡፡

ይህም ሆኖ ግን የሕክምና ባለሙያዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ የሕግና የሥነ ምግባር ቁጥጥር ሥርዓት ማስፈለጉ ዕሙን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ተጠሪነቱ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የነበረ የሕክምና ሙያ ሥነ ምግባር ኮሚቴ በ1994 ዓ.ም. እንደተቋቋመ፣ የተካሄደውን የመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ተከትሎ ደግሞ የሥነ ምግባር ኮሚቴው ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንደሆነና በ2006 ዓ.ም. ይኼው ኮሚቴ እንደ አዲስ ተደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱ አይዘነጋም፡፡

ኮሚቴውም ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ 60 የሙያ ሥነ ምግባር ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ቀርበውለታል፡፡ በእነዚህም ቅሬታዎች አቤቱታዎች ላይ ትንተና ሠርቶ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የቀረቡትም ቅሬታዎች ዓይነት ሞት 39፣ የአካል ጉዳት 15፣ ሌሎች የክፍያና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስድስት ናቸው፡፡

ቅሬታዎቹን ወይም አቤቱታዎቹን ያቀረቡት ታካሚ/ቤተሰብ 20፣ ፖሊስ/ፍርድ ቤት 19፣ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ 11፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አምስት፣ ሌሎች ባለሙያዎች ወይም ሌሎች ግለሰቦች አምስት መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ቁጥጥር ሰነድ ያሳያል፡፡

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የሕክምና ባለሙያዎች በሥራቸው ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለሚፈጽሟቸው ስህተቶች የሚጠየቁበት መንገድ አግባብ እንዳልሆነ፣ ያሉትም የመያዣ ቅደም ተከተሎች ላይ ችግሮች እንዳሉ የሕክምና ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ሕክምና ማኅበር ታኅሣሥ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ዓመታዊ ሜዲካል ኮንፈረንስና ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይህ ጉዳይ ተነስቶ ታዳሚዎችን በሰፊው አወያይቷል፡፡

በዚህም ውይይት ላይ የማኅበሩ አባላት ከሆኑት ከእነዚሁ ታዳሚዎች መካከል አንዳንዶቹ የጤና ሙያተኛው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ስህተት ሊፈጥር እንደሚችል ስህተቱን ግን ፖሊሶችና የሜዲካል ሌጋል ቲም (የሕክምና የሕግ ቡድን) ወይም ኮሚቴው የሚያዩበት ዕይታዎች የተለያዩ እንደሆኑና ጉዳዩም ሳይጣራ የጤና ባለሙያው ክብሩና ሰብዕናውን በሚያጎድፍ መልኩ እጁ በካቴና ታስሮና በፖሊስ ተይዞ መሄዱ ከሞራል አኳያ አንገት እንደሚያስደፋ ተናግረዋል፡፡

ሌላው ችግር አንድ ሕክምና ተቋም የጤና ሙያተኛን የሚቀጥረው ከመንግሥት የተሰጠውን የሙያ ምዝገባ ፈቃድና የትምህርት ደረጃውን በማገናዘብ ሲሆን፣ ነገር ግን ሙያተኛው በፈጠረው የቸልተኝነት ችግር የተነሳ ተቋሙ ለሦስት ከዛም ከፍ ሲል ለስድስት ወራት መዘጋቱ አግባብነት እንደሌለው አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ‹‹የጤና ባለሙያው በሥራ ላይ እንዳለ አንዳንድ ችግሮች ወይም ስህተቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የተጎጂ ወገኖች ፍትሕ አካላት ዘንድ ቀርበው ክስ ይመሠርታሉ፡፡ ሙያተኛውም ወዲያው ለእስር ሲዳረግ ማየቱ የተለመደ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ አንድ ሰው ጥፋተኛ ነው የሚባለው ሕግ ፊት ቀርቦ ጥፋቱ ከተረጋገጠበት በኋላ ነው፡፡

ከሕክምና ሙያ አንጻር ደግሞ ችግሩን ወይም ስህተቱ የሚታየው በጤና ሙያ ሥነ ምግባር ኮሚቴ እንደሆነና ኮሚቴውም በተሠራው ሥራ ላይ ስህተት ወይም ጥፋት ተፈጽሟል ብሎ ሳይወስን ዕርምጃ እንዲወሰድበት መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኮሚቴው ውስጥ በአባልነት የታቀፉት ሙያተኞች የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑ፣ የረዥም ዘመን አገልግሎት፣ ልምድና የሙያ ክህሎት ያላቸው መሆን እንደሚገባው ከተሰነዘሩት አስተያየቶች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ሕክምና ማኅበር ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ወንድወሰን አሰፋ (ዶ/ር) ‹‹ሕጉ እንደ አዲስ መቀረጽ አለበት ወይም በዚህ ዙሪያ ጉባዔ ተዘጋጅቶ፣ ጥናቶች ቀርበው፣ ችግሩን መስመር የሚያስይዝና ሁሉንም ያካተተ አንድ የሕክምና ሕግ መውጣት እንዳለበት ከመጠየቅ አልቦዘንም፤›› ብለዋል፡፡

ማኅበሩ በሜዲካል ሌጋል ዙሪያ ብቻ ሳይሆን የግሉን ዘርፍ አጠቃላይ ሕክምና አገልግሎት ሊያሻሽሉ ይችላሉ ብሎ ባመነባቸው ሐሳቦች ዙሪያ ለረዥም ጊዜ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የተነጋገረበት የጋራ ሰነድ እንደነበር፣ ሰነዱ ግን ሳይፈረም ሚኒስትሩ ከሰተብርሃን አድማሱ (ዶ/ር) ከሥራቸው እንደተሰናበቱ በምትካቸው የተሾሙትም ሚኒስትር ጉዳዩን ያዩታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕግ ባለሙያ ወይዘሪት ሊዲያ እንቁባህሪ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው በሰጡት መልስ፣ ‹‹አንድ የጤና ሙያተኛ በሥራ አጋጣሚ የፈጠረው ስህተት እንዴት ነው መታየት ያለበት፣ በማንስ ነው የሚዳኘው ከሚሉትና በሌሎችም ተዛማጅ ሒሶች ላይ ከፍትሕ አካላት ጋር ለመወያየት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የጤና ሙያተኞች ሥነ ምግባር ኮሚቴ የተዋቀረው በሕግ አግባብ ሲሆን፣ ሙያተኞችን የሚመድበው ግን ሚኒስቴሩ መሆኑን፣ ምደባውም የሚካሄደው በቅድሚያ የሙያ ማኅበራቱ ከመረጧቸውና ብቃታቸው ከታየ በኋላ መሆኑን የሕግ ባለሙያዋ ገልጸው፣ የሚሾሙት/የሚመደቡትም ሐኪሞች በሙያቸው በተለይ በእያንዳንዱ ስፔሻላይዜሽን ትልቅ ደረጃ የደረሱና ከፍተኛ ክህሎት ያላቸው እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ጥፋተኛው ሙያተኛው ሆኖ እያለ ተቋሙ ለምን እንዲዘጋ ይደረጋል? የሚለውም ጥያቄ አግባብነት ያለው መሆኑን አመልክተው፣ ሙያተኛው እንደ ሙያተኛ፣ ተቋሙ ደግሞ እንደ ተቋም መታየት ወይም መዳኘት እንዳለበት፣ ሁለቱም ላይ ክፍተቶች ከታዩ ግን ሁለቱም ተጠያቂ መሆናቸው እንደማይቀር ወይዘሪት ሊዲያ ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here