ማናችንም … መልካም በመሆን ክፉ አይገጥመንም! ለደግነትም በመኖር ዋጋና ትርፍ አናጣም። ለቅንነት በመትጋት አንወድቅም! የደገፈን ባይኖርም የምንደግፈው አንጣ! ሰውነት ለሰው ዘብ በመቆም ይገለፃልና!

የሰዎችን ልፋት ለመረዳት የሰነፈች ነፍስ አትኑረን። ልባችንም ለምስኪኖች ጥረት የመራራት ወኔ አትጣ! የታታሪዎችን ሙከራ ለማበርታት እንበርታ! ነገ … የእኛን መገኛ ቦታ በውል አናውቅም።

የዛሬ በጎ ተግባራችን ነው የነገ መልካም ስንቃችን። በመሆኑም ሰዎች ካሉበት አዳጋች ህይወት ወደተሻለ የኑሮ አማራጭ የሚያደርጉትን ጉዞ እናግዝ። ሰዎች የሚያስፈልጉንን ያህል እኛም ለሰዎች እናስፈልጋለን!

ለሰዎች ጥሩ አለመሆን ለራስ ክፉ እንደመሆን ነው። ሰዎችን ማገዝ ባንችል እንኳ በድካማቸው ለማትረፍ ከመጣር እንታቀብ! መርዳት ባንችል አንጉዳቸው! ማንሳት ቢያቅተን አንጣላቸው! ማስደሰትን ብንቸገር አናስከፋቸው!

… “እንቁላሉ ስንት ስንት ነው?” ስትል ጠየቀቻቸው።
“አንዱ 4 ብር ነው ” ልጄ በማለት መለሱላት እማማ።
“አምስቱን እንቁላል በ10 ብር ልወሰደው?” ስትል ደግማ ጠየቀች።

“አይጎዳኝም ብለሽ ነው ልጄ?” በማለት ደከም ባለ ድምፅ መለሱላት። “ከፈለጉ ይሽጡ! ካልፈለጉ ደግሞ ይቀራል!” አለች ጠንከር ባለ ድምፅ። እማማም ትንሽ አሰቡና ቀና ብለው አይተዋት…

“እስካሁን ምንም አልሸጥኩም። ባያዋጣኝም እንደ ገድ ልቁጠረውና ልሽጥልሽ። በይ እንዳልሽ። የፈለግሺውን ያህል እንቁላል በፈለግሺው ዋጋ ውሰጅ” ሲሉ ባዘነ ድምፅ ተናገሩ።

ዘንቢሏን አውጥታ 5 እንቁላሎችን በመምረጥ ወሰደች። ከበርካታ የ 100 ብር ኖቶች መካከልም 10 ብር አውጥታ ወረወረችላቸው። ተጎድተው ሳለም አመሰገኗት።

እሷ ግን እየተጣደፈች ወደሚያምረው ዘመናዊ መኪናዋ ውስጥ ገባች። የአሸናፊነት ስሜት ተሰምቷታል። ከንቱነቷ አልገባትም!

መኪናዋ ውስጥ ለነበረች ወዳጇ የፈፀመችውን ተረከችላት። ተሳሳቁ። ወደ አንድ ዘመናዊ ሬስቶራንት አመሩ። ገብተው ተቀመጡ። የሚፈልጉትን አዘዙ። ትንሽ በልተው ብዙ አስተረፉ።

ሂሳብ መጣላቸው። ቢሉ ላይ 1,420 ብር ይላል።

ከቦርሳዋ 1,500 ብር አውጥታ ሰጠች። መልስ አልተቀበለችም። ሌሎች ብሮች ጨምራ ለሬስቶራንቱ ባለቤት ቲፕ ሰጠችው።…ላለው ይጨመርለታል… ወጥተው ሄዱ።

ስለምን… ባጣው ላይ ጨክኖ ላለው የሚጨምር ትርጉም አልባ አዘኔታን ወደድን!? … “ድጋፉ … ከችግኙ ይልቅ ለዛፉ ያስፈልገዋልን!?” ይህ ድርጊት ለሬስቶራንቱ ባለቤት እንግዳ አይደለም።

ለብዙዎች ጥቂት አገልግሎት ሰጥቶ በብዙ ሲያተርፍበት ኖሯል። እሱ… የሬስቶራንቱ ባለቤት ነው። ቢሰጥ እንጂ አይሰጠውም። የሚደግፍ እንጂ የሚደገፍ አይደለም። ለእኔ ቢጤዋ…

ምስኪን እንቁላል ሻጭ ግን ይህ ድርጊት አሳዛኝና ልብ ሰባሪም ጭምር ነው። የሆነውን ማየት ባትችልም እኛ የሆነውን ያነበብነው ተነክተናል ብዬ አምናለሁ። መነካት በጎ ነው። ላለመነሳሳት መነካቱ ነው ፀያፉ!

ግን ለምንድን ነው… ምስኪኖች ላይ የበላይነታችንን በማሳየት ለመርካት የምንጥረው?! የእኛን እርዳታ ለማይፈልጉትስ ቸርና ደግ ሆነን ለመታየት ስለምን ጠብ እርግፍ እንላለን?

ለሚፈልጉን ሰዎች እርቀን ለማይፈልጉን ሰዎች ቅርብ የምንሆነውስ በምን ሰበብ ይሆን? የሚፈልጉንን ገፍተን የማናስፈልጋቸውን ስንፈልግ ለምን እንባክናለን!? …

በሰከነ ልቦና እናስብ! ድጋፋችንን ለሚገባው ግለሰብ ብቻ እንስጥ! ለምናስፈልጋቸው ውድ አንሁንባቸው።

ደስታህን ታሰርቀዋለህ እንጂ አትሰረቅም!

ለማዘን ካሉን ሰበቦች ይልቅ ለመደሰት ያሉን ምክንያቶች ይበልጣሉ። ደስታችን ማንም የማይነፍገን የውስጥ ሀብታችን ነው። የሰው ልጅ ሀሴቱ ከውስጡ እንጂ ከውጪ አይመነጭም።

በረባ ባልረባው መጨናነቅን ስናቆም የደስታችንን ዕድሜ እናረዝማለን። የደስታችንን ቁመት የምናሳጥረው የሀዘናችንን ስፋት ስንጨምር ነው። ሰላማችን ነሱን አንበል።

የሰላማችን ዘብም ሆነ ዘራፊ እኛው ራሳችን ነን። ሰላማችንን ለሚያረክስ ሳይሆን ደስታችንን ለሚያነግስ ጉዳይ እንገዛ። ደስታችንን ለመንሳት አቅም ያለው ነጣቂ የለም።

እኛጋ ያለው አቅም ሌሎችጋ ካለው ሀይል ይልቃል። ብርታታችንን እንመርምር። ደስታችንን የምንሻ ከሆነ ራሳችንን መሆን እንጀምር። ትክክለኛው ደስታ ሌሎችን ባለመሆን ይገኛል።

ሰላምን መጎናፀፍ ከዳዳን ውስጣችንን እንከተል። የማንም ሰው ጅራት ከመሆን እንታቀብ።

እኛነታችንን በፅናት እናቁመው። ማንነታችንን በብርታት እናኑረው። የማንንም ትከሻ አንደገፍ።

የግላችንን ምርኩዝ እንፍጠር። በራሳችን ጌጥ እንመር። ተለጣፊነትን አናብዛ። …

እስኪ .. መስከረም 24 በ “ሳሬም” ኢንተርናሽናል ሆቴል ባከበርነው የሁለተኛ ዓመት “ሐዋዝ” የጥበብ ምሽታችን ላይ የምንጊዜም ምርጡ ፎቶግራፈር አብርሃም ሳላስበው በድንቅ የካሜራ ዕይታው ለማስታወሻነት ካስቀረልን አስገራሚ ፎቶዎች መካከል ጥቂቱን እነሆ ጀባ ልበላችሁ…

በዚህ አጋጣሚ የ “ሐዋዝ” ልዩ ውበት ፈጣሪ የሆነ ወንድሜ አብርሽን ብታደንቁልኝ ደስተኛ ታደርጉኛላችሁ!!

የዘወትር ጨዋ ታዳሚዎቻችንም በዚሁ አጋጣሚ አክብሮታችን ይድረሳችሁ!!

ህዳር 27/2011 እንገናኝ!
“ሐዋዝ” የጥበብ ምሽት
ዋና አዘጋጅ :- ከፈለኝ ዘለለው (አሞዛ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here