ክቡር ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ለሚዲያ አካላት

ሰኔ 22/ 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተጠራው የፕሬስ ኮንፈረንስ ላይ ያደረጉት የንግግር ጽሑፍ

ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ፡-

ጥሪያችንን ተቀብላችሁ እዚህ የተገኛችሁ ጋዜጠኞችና የሜዲያ ተቋማት ተወካዮች
የአማካሪ ጉባኤው አባላት
እንዲሁም ሌሎች እንግዶች

በመጀመሪያ ጥሪያችንን አክብራችሁ ስለተገኛችሁ በራሴና በተቋሜ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።

በዛሬው እለት እዚህ የተገናኘንበት ዋና አላማ ስለሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ መቋቋሙን በሚመለከት ለሕዝብ መረጃ እንዲደርስ ለማድረግና የጉባኤዉን አባላት ለሕዝብ ለማስተዋወቅ ነው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፥

“የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ” (Legal and Justice Affairs Advisory Council) ተብሎ የሚጠራ ምክር ቤት መቋቋሙን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፓርት መግለፃቸው ይታወቃል።

የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤው 13 አባላት ያሉት ሲሆን፥ ዋና ተግባሩ፤የሙያ እውቀትና ክህሎትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሕግና ፍትሕ ስርአታችንን ለማሻሻል የሚያስችሉ የለውጥ ሃሳቦችን ለመንግስት ማቅረብ ነው።

ሕግ ራሱን የቻለ ልዕልና ያለው ተቋማቱም ለፍትሕ የታመኑ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሕግ መሣሪያ፣ የፍትሕ ተቋማትም የገዥዎች ዱላ፤ እየሆኑ ከሄዱ ነገሮች መበላሸታቸው አይቀሬ ነው፡፡

ይህን ለመለወጥ የፍትህና የዲሞክራሲ አስተዳደር ስርኣቱን በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና የሚኖራቸውን ህጎችና ተቋማትን በህዝብ አመኔታ የሚጣልባቸው ‹ገለልተኛና ዘመን-ተሻጋሪ ተቋማት› እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።

እንደሚታወቀው የሕግና ፍትሕ ስርአቱ ለሕግ የበላይነት መጠናከር፥ በሕገመንግስቱና ሃገራችን በተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች እውቅና የተሰጣቸውን የሰው ልጆች መብት መረጋገጥ፥

ለሰላምና ዴሞክራሲ መዳበር፥ ለኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መፋጠን፥

ለምላሽ ሰጪ መንግስታዊ የሕዝብ አስተዳደርመጠናከር፤እጅግ ከፍተኛና ተተኪ የማይገኝለት ሚና ይጫወታል።

ነገር ግን የሕግና ፍትሕ ስርአታችን አሁን ባለበት ሁኔታ ይህን ሚናዉን በሚገባ እየተጫወተ አይደለም። ይህም በተለያዩ መንገዶች እየተገለጸ ነው።

አንዳንድ ሕጎቻችንን፤ ለአብነት ያህል የጸረሽብር ሕጉ፥ የበጎአድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሕግ፥

የሚዲያ ሕግ እና የመሳሰሉት ሕጎች ላይ ማህበረሰቡ በተለያዩ ጊዜያት በሕጎቹ ይዘትና አፈፃፀም ዙሪያ የተለያዩ እሮሮዎችን ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወቃል።

አንዳንዶቹ እንዲያዉም የሃገራችንን መልካም ገፅታ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ፊት እንዳበላሹ በተለያዩ ጊዜ በተደረጉ ግምገማዎች ተገልጿል።

ዜጎች በፍትሕ ተቋማት በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ እሮሮ ሲያሰማ እንደነበር ይታወቃል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት የሕግ የበላይነትና ፍትሕ ከተነጣጠሉ፥

ሕግ የጭቆና መሳሪያ ይሆናል። እንዲህ አይነት ችግርን ለመፍታት ሰራተኛና አመራርን መቀየር ብቻ በቂ አይደለም።

ችግሩን መሰረታዊ በሆነ መልኩ አይፈታውም። የችግሩን መሰረታዊ ምክንያት ከምልክቶች፥ ማስታገሻን ከመድሃኒቱ፥ መለየት ያስፈልጋል።

እንዲሁም የሕግና ፍትሕ ስርአቱን የተለያዩ ንኡስ ስርአቶችና ተዋንያን ያላቸውን ተመጋጋቢነትና ግንኙነት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ችግሮችን ቅደም ተከተል በማስያዝ፥

በአጠቃላይ የሕግና ፍትሕ ስርአቱ ወደ ማያቋርጥ የለውጥ አዙሪት ውስጥ እንዲገባ፥ የማሻሻያ እርምጃዎችን ተቋማዊ በሆነ መልኩ መተግበር ያስፈልጋል።

ልብ ሊባል የሚገባው፤ እስካሁንም ድረስ በሕግና ፍትሕ ስርአቱ ብዙ የለውጥ ስራዎች ተሰርተዋል። ነገር ግን አተገባበራችን ያዝ ለቀቀ እየሆነ፥

አንዱ የለውጥ ስራ ተቋማዊ ቅርጽ ሳይዝ ሌላ እያመጣን፥ እና የስርአቱን ውስብስብነት ግምት ውስጥ በማስገባት አይደለም። እንዲሁም ረጅም ልምድ፥

ብቃትና፥ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላችዉን ባለሙያዎችን እና ማህበረሰቡን በበቂ ሁኔታ አሳትፈን፥

በተገቢው ልክ መረጃና ሙያን መሰረት አድርገን፥ መፍትሄዎችን በበቂ ሙያዊትንተና ለይተን አልተገበርንም።

በመሆኑም ይሄ የአማካሪ ጉባኤና በጉባኤው መመስረትየሚጀምረው የማሻሻያ ፕሮግራም ከእስካሁኑ ስራዎቻችን ልምድ በመመስረትና ውስንነቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት፥ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ብለን እንጠብቃለን።

አማካሪ ጉባኤው በጽህፈት ቤት በሚደራጁ የሙሉጊዜ ስራተኛ ባለሙያዎች ይታገዛል።

የጉባኤው አባላት ጥብቅ መመዘኛዎችን መሰረት ባደረገ መልኩ ተመርጠዋል።

መመዘኛዎቹ የተለያየ የትምህርት ዝግጅትን፥ የስራ ልምድን፥ የሕይወት ተሞክሮን ከግንዛቤ ዉስጥ ያስገቡ ናቸው።

የአማካሪ ጉባኤው በመጀመሪያ ስብሰባው ሰብሳቢዉን መርጦ እና የአሰራር ደንቡን በማጽደቅ ወደ ስራ የሚገባ ይሆናል።

እስከዛው ድረስ በጊዜያዊ ጽህፈት ቤቱ ስር አምስት የስራ ቡድኖች ተዋቅረው የመነሻ ስራዎችን እያከናወኑ ነው።

በመቀጠል የጉባኤውን አባላት አስተዋውቃለሁ።


1. ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ
2. ፕሮፌሰር ዘካሪያስ ቀነዓ
3. ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ

4. አቶ ሰለሞን አረዳ
5. አቶ ማሞ ምህረቱ
6. ዶ/ር በላቸው መኩሪያ

7. አቶ ሊቁ ወርቁ
8. አቶ ታደለ ነጌሾ
9. ወ/ሮ መሰረት ስዩም

10. ወ/ሮ ሰምሃል ጌታቸው
11. አቶ አሊ መሃመድ
12. አቶ ታምሩ ወንድምአገኘሁ
13. ዶ/ር ዘውድነህ በየነ

የጉባኤውን አባላት አስመልክቶ ሙሉ መረጃ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በአማካሪዉ ጉባኤ ድረገጽ ይፋ እናደርጋለን።

ለጊዜው ግን እያንዳንዱን አባል አስመልክቶ፥ አጭር መግለጫ ከአማካሪ ጉባኤው ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት ማግኘት እንደምትችሉ እየገለጽኩ፥ ጥሪያችንን አክብራቹ ስለመጣቹ በጣም አመሰግናለሁ።

ሁሉንም አገልጋይ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የሕግና ፍትሕ ስርአት ለመገንባት የሚያስችሉ የማሻሻያ እርምጃዎችን በጥናት በመለየት መንግስትና ሕዝብን ለመደገፍ ላሳያችሁት በጎፈቃደኝነት በእኔና በመንግስት ስም ላመሰግናቹ እወዳለሁ።

ለአማካሪ ጉባኤው ስኬትን እመኛለሁ። መንግስት አስፈላጊዉን ሁሉ ድጋፍ ያቀርባል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ መንግስት ያለውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት አረጋግጥላችኋላው።

አመሰግናለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here