የስኳር ኮርፖሬሸን በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን የስኳር እጥረት ለማረጋጋት ከውጭ ተገዝቶ የገባው 700 ሺህ ኩንታል ስኳር ተከፋፍሎ ማለቁን ተናገረ፡፡

ለመጭው ጊዜ አምስት ፋብካዎች ስኳር ማምረት ስለጀመሩ የአቅርቦት ችግር አይኖርብኝም ያለው ኮርፖሬሽኑ ለመጠባበቂያ ግን አንድ ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ ለማስገባት የግዥ ሂደት ተጀምሯል ብሏል፡፡

በቅርቡ ከውጭ ተገዝቶ ይገባል የተባለው 1 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለመጭው ክረምት መጠባበቂያ እንደሚሆን በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሸገር ተናግረዋል፡፡

በዚሁ አመት የስኳር ፋብሪካዎች ከ6.9 ሚልየን ኩንታል በላይ ስኳር እንደሚያመርቱ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም መናገሩ ይታወሳል፡፡

ፋብሪካዎች ማምረት ከጀመሩ ለመጠባበቂያ ከውጭ መግዛት ለምን አስፈለገ ስንል ጠይቀናቸዋል፡፡ የስኳር ምርት ለአየር ንብረት ችግር ተጋላጭ ስለሆነ ምናልባት በዝናብ ማጠር ወይንም መብዛት ምክንያት የፋብሪካዎች ስራ ሊስተጓጎል ይችላል ብለዋል አቶ ጋሻው፡፡

“እንዲህ ያለው ነገር ተከሰቶ ዳግም የስኳር እጥረት እንዳይፈጠርም ኮርፖሬሽኑ ለመጠባበቂያ 1 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ከውጭ ገዝቶ ማከማቸቱን መርጧል” የሚል መልስ ሰጥተውናል፡፡

አቶ ጋሻው እንዳሉት አሁን አምስት የስኳር ፋብሪካዎች ማምረት ጀምረዋል፡፡ ወንጂ ሸዋ፣ መተሃራ ፣ ፊንጫ፣ ተንዳሆና ከሰም የስኳር ፋብሪካዎች ማምረት በመጀመራቸው በቅርቡ የስኳር አቅርቦት ችግር እንደማይኖርም አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡

እጥረቱን ለማረጋጋት ከዚህ ቀደም ከውጭ ተገዝቶ የገባው 700 ሺህ ኩንታል ስኳር ግን ሙሉ በሙሉ ተከፋፍሎ እንዳለቀ ሰምተናል፡፡

(ትዕግስት ዘሪሁን)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here