በኢትዮጵያ አየር መንገድ የቀድሞ የበረራ አስተናጋጅና ወደ ሌላ ሥራ ተሰማርታ የነበረችውን የስምንት ወር ነፍሰ ጡር በፍልጥ እንጨት ቀጥቅጣ ገድላለች የተባለችው የቤት ሠራተኛ፣ የቀረበባትን ክስ እንድትከላከል ብይን ተሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ብይን እንደገለጸው፣ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችው ወ/ሮ ሔዋን ሳህሌ በሠራተኛዋ ወ/ሪት ታደለች ድንቁ መጋቢት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በግምት ከምሽቱ 12፡30 ሰዓት መገደሏን ከከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ክስ ተረድቷል፡፡

የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ ሠራተኛዋ ሟች ‹‹ትቆጣጠረኛለች›› የሚል ቂም በመያዝ ጨካኝነቷንና ነውረኛነቷን በሚያሳይ ሁኔታ በፍልጥ እንጨት ጭንቅላቷን ደጋግማ በመምታት ገድላታለች፡፡

ተጠርጣሪዋ ሕይወቷ ማለፉን ስታረጋግጥ አስከሬኗን በጓዳ በር ጎትታ በማውጣት በእሳት በማቃጠል በቀይ ማዳበሪያ ውስጥ ከትታ በግቢው ውስጥ በሚገኝ አትክልት ውስጥ በማስቀመጥ በቆርቆሮ ሸፍና እንደነበር በክሱ ተገልጿል፡፡

ተከሳሿ ወ/ሪት ታደለች የወንጀል ድርጊቱን ከፈጸመች በኋላ እጇን ለፖሊስ በመስጠቷ ድርጊቱን እንዴት እንደፈጸመች መርታ ማሳየቷም ተገልጿል፡፡

በሰጠችው የእምነት ቃል ከማረጋገጧም በተጨማሪ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የአስከሬን ምርመራ ውጤትና ባሰማቸው የሰዎች ምስክርነት ቃል ተከሳሽ ድርጊቱን ስለመፈጸሟ እንደ ክሱ ማስረዳት በመቻሉ፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1) ሥር የተደነገገውን መተላለፏን የሚጠቁም በመሆኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 142(1) መሠረት እንድትከላከል በሙሉ ድምፅ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡

የመከላከያ ምስክር ለመስማትም ለግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here